“በዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ከ442 ሚሊዮን ብር በላይ በግንባታ ዘርፍ ብቻ በግለሰቦች ተመዝብሯል” – ከሰሞኑ ግምገማ መድረክ (የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ዘገባ)
ነሐሴ 21 2015ዓም
በዎላይታ ሶዶ ዩንቨርሲቲ ለአራት ተከታታይ ቀናት ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ከዋና ኦዲተር መ/ቤቶች የተውጣጣ የአመራሮችና የባለሙያዎች አጣሪ ኮሚቴ ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር ያካሄደውን ሰፊ የግምገማና የውይይት መድረክ የተለያዩ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መጠናቀቁ ተገልጿል።
“በዚሁ መድረክ በዩኒቨርሲቲው ጎልቶ የወጡ ብልሹ አሠራሮች፣ የሀብት ምዝበራዎች፣ አምገነናዊ ሥርዓቶች፣ ወዘተ በስፋት ተገምግሟል” ስል በውይይት መድረኩ የተሳተፉ አንድ ከፍተኛ አመራር ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አስረድተዋል።
በዚህ የግምገማ መድረክ ከተነሱ የሀብት ምዝበራዎች መካከል በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተደረገው የሀብት ብክነት ከዚህ በታች ቀርቧል።
“በዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አማካይነት የሚገነቡ ግንባታዎች የክዋኔና የፋይናንስ ኦዲት በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በገለልተኝነት በተደረገው ምርመራ 442,018,766.60 ብር አላአግባብ መባከኑንና መመዝበሩን የሚያሳይ ተጨባጭ መረጃ ለመድረኩ ተሳታፊዎች ከፌደራል በመጡ አመራሮች ቀርቧል” ስሉ ታማኝ ምንጫችን ገልጸዋል።
በዎላይታ ሶዶ ከተማ ውስጥ የኦሞቲክ ምርምር ማዕከል ምንም ዓይነት ግንባታ ሳይካሄድ ከ81 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መሆኑ፣ በጋንዳባ ዋናው ካምፓስ እና በኦቶና ካምፓስ የምርምር ላብራቶሪ ለመገንባት ተብሎ አንዳች ነገር ሳይሠራ ከ112 ሚሊዮን ብር መዘረፉ እንዲሁም በቦዲቲ የቴክኖሎጂ ልህቀት ማዕከል ግንባታ ከ49.9 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ አለአግባብ መባከኑም በፌደራል ኦዲት መስሪያቤት የተረጋገጠው ሰነድ ለመድረኩ መቅረቡን አስረድተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በ2015 በጀት ዓመት ብቻ በአራት የግንባታ ፕሮጀክቶች (የመምህራን መኖሪያ፣ ማራጫሬ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ማስተማሪያ ሆቴል፣ ስፖርት ማዘውተሪያ እና በዳውሮ ታርጫ ካምፓስ የመማሪያ ክፍል፣ የመምህራን መኖሪያና ላቦራቶሪ ግንባታ ፕሮጀክቶች) ከኮንትራክተሮች ጋር ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ (የዩኒቨርሲቲው ፕረዚዳንት) እና ዶ/ር ተክሌ ሌዛ (የዩኒቨርሲቲው ም/ፕረዚዳንትና የአስተዳደርና ልማት ዘርፍ) ቀጥታ ድርድር በማድረግ በልዩነት (Variation) እና በተጨማሪ (Supplementary) ስም ከ199 ሚሊዮን ብር በላይ እንደተመዘበሩ ከስፍራው ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ከደረሰው ተጨባጭ መረጃዎች ለማረጋገጥ ችለናል።
በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ለሚገነባው የነዳጅ ማደያ ከ40 ሚሊዮን ብር አለግባብ በትርፍነት እንዲከፈል መደረጉንም ከደረሰን ሰነድ ለማወቅ ተችሏል።
ከዚህ በፊት በወርሃ መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲን የኦዲት ግኝት በተመለከተ ከፌደራል ኦዲተር ኃላፊዎች፣ ከዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ጠንከር ያለ ውይይት ያደረገው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲን የኦዲት ግኝት አስመልክቶ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉን በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል።
ከእነዚህ ውስጥ “እስካሁን ድረስ የእርምት እርምጃ የተወሰደባቸው ነገሮች የሉም፤ የዩኒቨርሲቲው ፕረዚዳንት በማንአለብኝነት በሕዝብና በመንግስት ሀብት ላይ ጉዳት እያደረሰ እንዲቆይ የትምህርት ሚኒስትር ድኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ እና አንዳንድ የዩኒቨርሲቲው ቦርድ አመራሮች በጥቅም ትስስር ለፕረዚዳንቱ ሽፋን እየሰጡ እንደቆዩ ከትምህርት ሚኒስትር እና ከዩኒቨርሲቲው የወጡ ተጨባጭ የሰውና የሰነድ መረጃዎች እያረጋገጡ የሚመለከታቸው አካላት በዩንቨርሲቲው ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ ለምን በአስቸኳይ አይወስዱም” የሚሉ ድምፆች እየተደመጡ መሆኑንም የመረጃ ምንጫችን አክለው አስረድተዋል። ባለፈው ሣምንት ከቀን 15/12/2015 ዓ.ም ሰኞ ዕለት ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ከዋና ኦዲተር መ/ቤቶች የተውጣጣ የአመራሮችና የባለሙያዎች አጣሪ ኮሚቴ ከዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ጋር ሰፊ የግምገማና የውይይት መድረክ የተነሱ ሀሳቦች “አብዛኞቹ በአስተዳደራዊ እርምጃ የሚስተካከሉ ሳይሆን ከፍተኛ የህግ ጥሰት የተፈፀመበት ስለሆነ በቅርቡ ሌላ የፌደራል ገለልተኛ ቡድን ተዋቅሮ በየዘርፉ የተፈፀሙ ጥሰቶች ላይ እርምጃ እንዲወሰድበት” በሚል መጠናቀቁንም ገልጸዋል።