በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገው 3 ሺህ 410 የላብራቶሪ ምርመራ 46 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 701 መድረሱን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ተደሰ ባወጡት ሪፖርት አስታውቀዋል። ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች መካከል 45 ኢትዮጵያውያን፤ አንዷ የእስራዜል ዜጋ ሲሆኑ እድሜያቸው ከ12 እስከ 79 ዓመት የሆኑ 29 ወንዶችና 17 ሴት ናቸው።
ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 8 ሰዎች ደግሞ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የሌላቸው፣ 34 ሰዎች የውጭ የጉዞ ታሪክ ያላቸው እንምዲሁም 4 ሰዎች በበሽታው ከተያዘ ሰዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆኑን አስታውቀዋል።
ቫይረሱ በምርመራ ከተገኘባቸው ሰዎች ውስጥ 13 ሰዎች ከአዲስ አበባ ሲሆኑ፥ ከእነዚህም መካከል 8 ሰዎች የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የታወቀ ግንኙነት የሌላቸው፣ 4 ሰዎች በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው እንዲሁም 1 ሰው ደግሞ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው ናቸው።
3 ሰዎች ከትግራይ ክልል (ሁሉም የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያላቸውና በለይቶ ማቆያ የሚገኙ)፣ 15 ሰዎች ከአማራ ክልል ክልል (ሁሉም የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያላቸውና በለይቶ ማቆያ የሚገኙ)፣ 11 ሰዎች ሶማሌ ክልል (ሁሉም የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያላቸውና በለይቶ ማቆያ የሚገኙ) እንዲሁም 4 ሰዎች የውጭ የጉዞ ታሪክ ያላቸውና የድንበር ተሻጋሪ መኪና አሽከርካሪዎች መሆናቸውን ዶክተር ሊያ ገልፀዋል።
በተጓዳኝ ህመም ምክንያት በፅኑ ህክምና ላይ የነበረች እና በትናንትናው ዕለት የኮሮና ቫይርስ በምርምራ የተገኘባት የ32 ዓመት የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነች ኢትዮጵያዊ ትናንት ለሊት ህይወቷ አልፏል ይህም በአጠቃላይ በሀገራችን በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 6 ደርሷል።
በሌላ መልኩ በትላንትናው ዕለት 8 ሰዎች (2 ሰዎች ከደቡብ ክልል እና 6 ሰዎች ከአዲስ አበባ) ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን፥ በአጠቃላይ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 167 ደርሷል።
በ 24 ሰዓታት ውስጥ የተደረጉ የላቦራቶሪ ምርመራ ናሙናዎቹ ከተለያዩ ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ከጤና ተቋማት፣ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ካላቸው ሰዎች እንዲሁም በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ካሉ ሰዎች ተወድስ የተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል። ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ እስካሁን ለ87 ሺህ 264 ሰዎች ምርመራ የተደረገ ሲሆን፥ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 701 ደርሷል።