በእስራኤል የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በትምህርት ቤቶች መቀስቀሱን ተከትሎ 7ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎችንና መምህራን ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ መደረጉን ባለሥልጣናት አስታወቁ፡፡ ከ40 በላይ ትምህርት ቤቶችም ተዘግተዋል፡፡ ሆኖም መንግሥት አጠቃላይ መዋለ ህጻናትና ሌሎች ትምህርት ቤቶች ተከፍተው እንዲቆዩ ወስኗል፡፡ በቅርቡ በእየሩሳሌም ጂምናሺያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በስፋት የታዩ ሲሆን 130 የሚሆኑት ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ቫይረሱን ያዛመተው አንድ የኮቪድ -19 ታማሚ መምህር እንደሆኑ ዘግበዋል፡፡ በትምህርት ቤቶችና በሌሎች ተቋማት ወረርሽኙ መቀስቀሱም በአገሪቷ ሁለተኛ ዙር ወረርሽኝ እንዳይቀሰቀስ ስጋት ፈጥሯል፡፡
ማክሰኞ እለት የጤና ሚኒስቴር 116 አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን ያስታወቀ ሲሆን፤ ይህም በአንድ ወር ውስጥ የታየ ከፍተኛ ጭማሬ ነው ተብሏል፡፡
በእስራኤል እስካሁን 17ሺህ 342 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 290 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ በአገሪቷ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ቤት ውስጥ የመቀመጥ ገደብ የተጣለው ቀደም ብሎ ሲሆን ባለፈው ወር አጋማሽ ጀምሮ ግን ቀስ በቀስ ገደቦቿን እያላላች ነው፡፡
በዚህም መሰረት ትምህርት ቤቶች፣ ቢሮዎች፣ ሱቆች፣ ምግብ ቤቶች እና የባህር ዳርቻዎች እንዲከፈቱ ፈቅዳለች፡፡ (ምንጭ፡- ቢቢሲ አማሪኛ)