Wolaita Today

በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ አራት ዞኖች በተለይም በምዕራብ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች ውስጥ ‘በመንግሥት ጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ግድያዎች እየተፈጸሙ ነው’ የሚሉ ተደጋጋሚ እሮሮዎች ከነዋሪዎች ይሰማል።

ከእነዚህ መካከል በምዕራብ ወለጋ ዞን ላሎ አሰቢ ወረዳ ኬሌዬ ቢርቢር በምትሰኝ ቀበሌ ውስጥ ተገደሉ የተባሉት የአራት ልጆች እናት ይገኙበታል። ወ/ሮ አምሳሉ ጉደታ የአራት ልጆች እናት ሲሆኑ ሐሙስ ግንቦት 13 2012 በእርሻ ሥራቸው ላይ ሳሉ በመንግሥት ጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች በጥይት ተመትተው መገደላቸውን ባለቤታቸው አቶ ሚረቴ ኢማና ይናገራሉ። “ጥላብኝ የሄደችው ህጻናት ‘እናታችን መቼ ነው የምትመጣው’ እያሉ ይጨቀጭቁኛል” ይላሉ አቶ ሚረቴ ኢማና።

በተመሳሳይ መልኩ በምዕራብ ወለጋ ዞን የገንጂ ወረዳ ነዋሪ የነበረው ወጣት ለሊሳ ተፈሪ ከሁለት ሳምንት በፊት በአካባቢው ተሰማርቶ በሚገኘው የመንግሥት ኃይል በቁጥጥር ሥር ከዋለ ከሁለት ቀናት በኋላ ሞቶ መገኘቱን ቤተሰቦቻቸውን ቢቢሲ ዘግቦታል።

ቢቢሲ የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊን በስልክ አግኝቶ ማነጋገር ችሎ ነበር። የቢሮ ኃላፊ አቶ ጅብሪል ሞሐመድ በመንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች ላይ የሚቀርበው አቤቱታ ሐሰት ነው። ይህ ክስ መሠረተ ቢስ ነው ይላሉ።

“ጸረ-ሰላም ኃይሎች ራሳቸው ገድለው መንግሥት ላይ ማሳበባቸው የተለመደ ነው” ያሉት አቶ ጅብሪል፤ “እኛ ሰላማዊ ዜጋ ገድለን አናውቅም፤ የጸጥታ መዋቅሩም ሰላማዊ ሰው አይገድልም። ለሚሞቱ ሰዎች መነሻውም መጨረሻውም ሸኔ ነው” ይላሉ።

የአስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊው ለግድያዎቹ ሸኔን ተጠያቂ የሚያደርጉበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ “የመጀመሪያው መንግሥት እና ህዝብ የሰጣቸውን ሰላማዊ ትግል ‘አንቀበልም’ በማለት የደህንነት ችግር ፈጥረዋል። ሁለተኛው ደግሞ ህዝብ ወደ ሚኖርበት ገብተው፣ ህዝብ መካከል ሆነው ወደ ጸጥታ አስከባሪዎች ይተኩሳሉ” ብለዋል። በዚህም ምክንያት ንጹሃን ዜጎች እየተጎዱ መሆኑን ጨመረው ያስረዳሉ።

አቶ ጅብሪል ለግድያዎቹ ሸኔ ተጠያቂ ስለመሆኑ የሚያቀርቡት ሌላኛው መከራከሪያ፤ በዚህ ሁኔታ ንጹሃን ዜጎች ሲጎዱ የመንግሥት ኃይል ሰው ገደለ ብለው በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ይለጥፋሉ፤ አባላቶቻቸው ሲገደሉም ‘ንጽህ ዜጋ በመንግሥት ኃይል ተገደለ’ ይላሉ”።

አቶ ሚረቴ እንደሚሉት ባለቤታቸው የበቆሎ ማሳ ውስጥ እያለች በተተኮሰባቸው ጥይት ተመተው ህይወታቸው አልፏል።

“የአንድ ዓመት ህጻን የእናቷ አስክሬን አጠገብ ቁጭ ብላ እንዳለች ነው የባለቤቴን አስክሬን ያነሳሁት” በማለት በሃዘን ተውጠው ይናገራሉ። ባለቤታቸው በጥይት ተመትታ ስትገደል በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ተመልክተዋል ይላሉ አቶ ሚረቴ። አቶ ሚረቴ እንደሚሉት ከሆነ ከባለቤታቸው ግድያ አንድ ሳምንት በፊት፤ እርሳቸውም በመንግሥት ጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ድብደባ ተፈጽሞባዋል።