Wolaita Today

በኢትዮጵያ እስካሁን 49 የጤና ባለሙያዎችና 16 ድጋፍ ሰጭ ሠራተኞች ኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ አስታውቀዋል።

ባለሙያዎቹ በአብዛኛው በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ተቋማት ውስጥ እያገለገሉ የነበሩ ናቸው ተብሏል።

ሚኒስትሯ መንግሥት የጤና ተቋማት ሠራተኞች ለቫይረሱ ያላቸውን ተጋላጭነት ለመቀነስ ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ ሕብረተሰቡ ራሱን በመጠበቅ በጤና ባለሙያዎቹ ላይ የሚደርሰውን ጫና እንዲቀንስም ጥሪ አቅርበዋል።

ዶ/ር ሊያ የጤና ተቋማት ሠራተኞች የወረርሽኙን ሥርጭት ለመግታት እያደረጉ ያለውን ጥረት አመስግነዋል።

ትናንት የጤና ሚኒስትሯ በሚቀጥሉት 4 ወራት ለጤና ተቋማት ብቻ 131 ሚሊየን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዎች (ማስኮች) እንደሚያስፈልጉ ተናግረው ነበር።፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የእነዚህ የህክምና ግብዓቶች እጥረት መኖራቸውን የጠቀሱት ዶ/ር ሊያ፤ እንደ አገርም በርካታ ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።