የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዕድሜ ጠግቦ አርጅቶ ይሞታል ወይስ ዕድሜው ባጭር ይቀጫል?
በዶ/ር መድህን ማርጮ (ነሐሴ 3 2015ዓም)
አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዕድሜ ጠግቦ አርጅቶ ይሞታል ወይስ ዕድሜው ባጭር ይቀጫል? የሚለውን ለማየት ቢያንስ 2016 ዓ/ም የክልሉን አያያዝ ማየት የሚጠይቅ ይመስላል፡፡ አሁን ላይ ግን በርካታ የከራረሙ የደኢህዴን በሽታዎ እንዲሁም በደ/ብ/ብ/ሀ/ክ/መ ወቅት ያልነበሩ ከባድ አዳዲስ ፈተናዎችና በትይዩ ሊፈጠሩ የሚችሉ ውስን የሆኑ ተስፋዎች ይዞ እንደ ክልል ለመቆም እየተውተረተረ ይገኛል፡፡
አዲሱ ክልል ከደኢህዴን የወረሰው ትልቁ በሽታ አመራሩ ነው፡፡ በተላይ የበላይ ከፍተኛ ሹማምንት ወደ ሌሎች ክፍልፋይ አዳዲስ ክልሎች የሔዱት ከመሔዳቸው ውጭ የተቀሩት ፍጥጥ ብለው የአዲሱን ክልል ከፍተኛ የአመራር ወንበር ለመቀራመት እያንዣበቡ ሲሆን ይህ ለአዲሱ መዋቅር ከፈተናዎች ሁሉ የከፋ ፈተና ነው፡፡ በዚያ ላይ የዘር መሳሳብ ከአሁኑ ትኩረት ስቦ እየተስተዋለ ነው፡፡ ከፍተኛው የፊት አመራርነት ቦታ ከየትኛውም ነጥብ የበለጠ መተኮር ያለበት ተፈላጊ መስፌርት ከፍ ያለ የሞራል ስብዕና እነ በዚያ ዓይነት ስብዕና ላይ የተገነባ መልካም ስም ነው፡፡
ከአሁን በፍት በመልካምነት የተወደሰ ስብዕናና ሚዛናዊነት የጎደለው ሰው ከየትኛውም ብሔር ወደ ር/መስተዳደርነት ከመጣ የፕሮጀክቱን ዕድሜ እንደሚቀስፈው ግልፅ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህንን በተመለከተ በድርጅትም ሆነ በህዝብ ደረጃ በግልጽና በድፍረት መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ እያንዳንዱ ብሔር የራሱ ተወላጅ ሆኖ ቀደም ሲል በታማኝነት ብሔሩን ያላገለገለ አንድ ሹም ለአዲስ ከፍታ ዕጩ እንደማያደርገው ሁሉ ከራሱ ብሔር ውጭም ሆኖ በመልካም ስም የማያስታውሰውን ግለሰብ በአዲሱ መዋቅር ቁልፍ አመራር ሆኖ ቢመጣ ህዝቡ አሁን ባለው ሁኔታ ግለሰቡን ከቦታው ማንሳት ሳይሆን መዋቅሩን ወደ ማፍረስ እንደሚያተኩር ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ እያወራሁት ያለው ስለብሔረሰብ ሳሆን ስለግለሰቦች ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ባለፉት 5 ዓመታት ውስጥ ከሌላ ማንም ጋር ችግር የለብንም ግን ከወላይታ ጋር መደራጀት እንፈልግም ብለው በአደባባይ የተናገሩት ግለሰቦች እንዲሁም አንድ የወላይታ ተቋም ውስጥ ድገንት ከአሁን በፊት ረብሻ ስለተፈጠረ ያ ተቋም ይዘጋና ሰልጣኝ ወደ ሌላ የኢትዮጵያ ክፍል ይዛወር የማለት ያህል ለአከባቢውና ለህዝቡ ሚዛናዊነት የጎደለው ስሜት ሲያንጸባርቁ የነበሩት ግለሰቦች የክልሉ ቁንጮ አመራር ቦታ ላይ ቢመጡ ህዝቡ እነኚህ ዓይነት ሰዎች የራሴ ብሎ ለመቀበል እጅግ ከባድ ይሆናል፡፡ ከወላይታም እንዲሁ አንዱን ወይም ሌላ ብዙ ማህበረሰብ ሚዛናዊነት በጎደለው ሁኔታ ያስቀየመ ግለሰብ ያንን መልካም ያልሆነ ስም ተሸክሞ የአዲሱ ክልል ቁልፍ አመራር ሆኖ ቢሾም ያ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ስለዚህ ሹመት ላይ ከወትሮው የበለጠ እጅህ ከፍኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡
ከዚህ ሌላ አዲሱ ክልል በፊት ያልነበረ አንድ ግዙፍ አዲስ ፈተና ይዞ ነው የመጣው፡፡ የክልሉ ቢሮዎች 6ቱም ዞኖች እንደ ፀበል በመረጨታቸው ምክንያት ያንን ተከትሎ በዓመት የሚረጨው የክልሉ ሥራ ማስኬጃ ወጪ በግምት ከአንድ ዞን ዓመታዊ ጠቅላላ በጀት የሚተናነስ አይመስለኝም፡፡ ይህን እንግዲህ የ2016 ዓ/ም ሥራ ውሎ ዓበል፤ ነዳጅ ወዘተ ወጭ ስናይ በተጨባጭ እንደርሰበታለን፡፡ ይህ ማለት የልማት ለልማት መዋል ይችል የነበረው ገንዘብ ያለአግባብ በካድሬ ውሎ-አበል ይባክናል ማለት ነው፡፡ ከሴክተሮቹ ወጭ ባሻገር ቢዎቹ 6 ቦታ መሰራጨታቸው በጉዳይ አፈጻጸም ላይ የሚያሳድረው መንዛዛት በተለይ አበል-የለሽ ምስኪን የግል ባለጉዳዩች ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ ጊዜያቸውንና ኪሳቸውን የሚዳስስ በመሆኑ እነዚህ ባለጉዳዮች በምሬት ደም-ግፊታቸውና የሰውነታቸው ሙቀት ብቻ ሳይሆን በክልሉ global warming ሁሉ ክፍ ሊደርግ ይችላል፡፡ እነዚህን ፈተናዎች ግን መሻገር ከቻለ አዲሱ ክልል ከፈተናዎች ትይዩ መፍጠር የሚችለው ውስን ተሰፋዎች ስላሉ ስለነሱ በሌላ ጊዜ እንመለሳለን፡፡