የህዝብ ሉአላዊነት፣ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እና የኢፌዲሪ ህገ-መንግስት

ሕዳር 1 2015ዓም (ክብረአብ ደምሴ)

ሉአላዊነት የማይገደብና የማይጠየቅ የመንግስት የመጨረሻው ሥልጣን ማለት ነው፡፡ ባለፈው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የሉአላዊነት ሥልጣን ባለቤቶች ነገሥታት ነበሩ፡፡ እነዚህ ነገሥታት ውሰን የሌለው የመጨረሻ ፈላጭ ቆራጭ ሉአላዊ የሥልጣን ባለቤት ነበሩ፡፡ ከኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ድምፅ ይልቅ የእነዚህ ነገሥታት ድምፅ /ቃል/ ተደማጭነት ፣ የመጨረሻ ፍርድ የመስጠትና ሕግ የማመንጨት ኃይልም፣አቅምም ነበራቸው፡፡ የንጉሱን ሉአላዊ ሥልጣን በመቀማት ደርግ በብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ስም የህዝብን ሉዓላዊ ሥልጣን በቁጥጥር ሥር በማድረግ ፋሽስታዊ አምባገነን ሥርዓት አነገሠ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለረዥም ዘመናት በአምባገነኖችና በነገሥታት ተወስዶባቸው የነበረውን የሥልጣን ባለቤትነት ለማስመለስ እልህ አስጨራሽ ትግልና መስዋዕት በመክፈል የደርግ አምባገነናዊ እና ፋሽስታዊ መንግስትን ግንቦት 2ዐ,1983 ዓ.ም. ከሥልጣን በማወረድ ዲሞክራሲያዊና ህገ-መንግስታዊ ሥርዓት ለመገንባት በቅተዋል፡፡ በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ብሄር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የመጨረሻ የሥልጣን ባለቤት ለመሆን በቅተዋል፡፡

የህግ የበላይነት ተከብሮ ማንኛውውም ህግና የመንግስት ሥልጣን ከህዝብ የሚመነጭ መሆኑ ህዳር 29,1987 በፀደቀው የኢትዩጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት ተረጋግጧል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤቶች መሆናቸውን፣ ህገ መንግስቱ የሉአላዊነታቸው መግለጫ እንደሆነ እና ሉአላዊነታቸውም የሚገለፀው በኢፌዲሪ ህገ-መንግስት መሰረት በሚመርጧቸው ተወካዬቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት መሰረት እንደሚሆን በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 8 ተደንግጐ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ በመሆናቸው የማይጣሱና የማይገፈፋ መሆናቸውንና የዜጐች እና የህዝቦች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የተከበሩ መሆናቸውን የኢፌድሪ ህገ-መንግስት በአንቀፅ 1ዐ በዝርዝር ተቀምጦ ይገኛል፡፡

አምባገነናዊና በንጉሳዊ የአገዛዝ ሥርዓቶች የሥልጣን ሉአላዊነት የሚገለፀው የሥልጣን ቁንጮ ወይም ባለቤት የሆነው ፖለቲካዊ ሀይል ወይም ግለሰብ ሥልጣኑን ከህዝብ በላይ በማሳረፍ ነው፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን ደግሞ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ህዝብ የሥልጣን ባለቤት በሆነበት ዳግም ህዝቡ መሪዎቹን /አስተዳዳሪዎቹን/ ራሱ በቀጥታ በመምረጥና ሳይፈለግ ሲቀር ዳግም ከስልጣን ማውረድ የሚችልበት አሰራር ተፈጥሯል፡፡

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 1ዐ መሰረት ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ተደንግገው ይገኛሉ፡፡ በህገ መንግስቱ መሰረት፡-

“ሰብአዊ መብት” ስንል ሰው ሰብአዊ ፍጡር በመሆኑ ብቻ ሰብአዊ ፍጥረትነቱ እስካልተቀየረ ድረስ “የሚያገኘው” ሳይሁን “የሚኖረው” መብት ወይም ሰው ሆኖ በመወለዱ ብቻ ማንኛውም ቅድሙ ሁኔታ ሳያስፈልግ የሚኖሩት መብቶች ማለት ነው፡፡

“ዲሞክራሲያዊ መብት” ስንል ዳግም አንድ ሰው ወይም የህብረተሰብ አካል የማህበረሰቡ አባል በመሆኑ ዲሞክራሲ በሰፈነበት ሥርዓት ውስጥ የሚያገኛቸው መብቶች ናቸው፡፡

የኢፌዲሪ ህገ-መንግስት ለኢትዮጵያ ብሄር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብቶችን በአንቀፅ 39 ላይ ደንግጓል፡፡ ማንኛውም የኢትጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በቋንቋቸው የመናገር፣ የመፃፍ፣ ቋንቋቸውን የማሳደግ፣ እና ባህላቸውን የመግለፅ፣ የማዳበርና የማስፋፋት እንዲሁም ታሪካቸውን የመንከባከብ፣ ራስን የማስተዳደር እንዲሁም የራስን እድል በራስ የመወሰን እስከመገንጠል መብታቸው በህገ-መንግስቱ የተረጋገጠ ነው፡