የሸፍጥ ጉድጓድ ማን እንደሚቀበርበት አይታወቅምና ሴረኞች እንዲህ አርቃችሁ አትቆፍሩ!!!

Wolaita Today

በአሸናፊ አይዴ

August 09, 2020

ህግ በዚህች ምድር ለሚኖር ሰው ሁሉ በሰላም ለመኖር ዋስትና ነው፤ ለዚህም ነው “ሰው ሁሉ በህግ ፊት እኩል ነው” የሚል አስተሳሰብ በአለም መንግስታት ሁሉ ተቀባይነት ያገኘው፡፡

ነገሩ እንደመንግስታት ባህሪና እንደሀገራት የዕድገት ደረጃ አተገባበሩ ቢለያይም፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካን ወሰድን ብንመለከት ከማንኛውም የፖለቲካ ተጽኖ ነጻ የሆነ የዜጎች መብትና ጥቅም የሚያስከብር የፍትህ ስርዓትና ገለልተኛ ተቋም ፍርድ ቤት አለ፡፡ ዜጎችም ያለአንዳች መሸማቀቅና አፈና ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት በነጻነት ለማስፈጸም ፅኑ እምነት አላቸው፡፡ ባለስልጣን፣ሀብታም፣ደሃ፣የተማረ፣ያልተማረ…ወዘተ ሁሉም ያለአንዳች ልዩነት በእኩልነት ዳኝነት ያገኛሉ፡፡

በተቃራኒው የደሃ ሀገራትና አምባገነን መንግስታት የፍትህ ሥርዓት የዓለም መርሆ የሆነውን “ሰው ሁሉ በህግ ፊት እኩል ነው” የሚለውን ከበለጸጉ ሀገራት ብድርና እርዳታ ለማግኘት ሲሉ በህጋቸው ያሰፍሩና አተገባበሩ ግን የመንግስትንና የፓርቲ ተልዕኮ የሚፈጽም ተቋማዊ ቅርጽና ይዘት፣ አደረጃጀትና አሰራር እንዲሁም አመራር እንዲኖረው ይደረጋል፡፡

ወደ ዋናው ጉዳይ ልመለስና ሰሞኑን በሀገራችንም ሆነ በዎላይታ የመንግስት ባለስልጣናት ህግ በማስከበር ስም ራሳቸው ህግ አክብረው በማስከበር ፈንታ የፓለቲካ፣ የአስተሳሰብና የአመለካከት ልዩነት የሚራምዱ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ለማደን ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ የዚህ ተግባር ማሳያ የሚሆነው ሰሞኑን የዎላይታን ህዝብ የክልል ጥያቄ በሚያቀነቅኑ ግለሰቦች ላይ መልኩን እየቀያየረ በፈራሹ ደቡብ ክልል ፀጥታ ቢሮ ትዕዛዝ በዎላይታ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ዛቻ፣ ማስፈራሪያና አፈና ነው፡፡

የዬላጋ አሰፋ አየለ ቤት ብርበራና የእስር ትዕዛዝ ዙሪያ የታዩ ነገሮች የፍትህ ስርዓትና ፍርድ ቤቶች የዜጎችን መብትና ጥቅም ከማስከበር ይልቅ የፖለቲካ ተልዕኮ ስራ እየሰሩ መሆናቸውን በሚከተለው መልኩ በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡

  1. በኮሮና ምክንያት “ፍርድ ቤቶች ዝግ ናቸው” በሚል የብዙ ዜጎች ዳኝነት የሚሹ ጉዳዮች በስብሰው እያሉ፣ ዜጎች እስር ቤት እየታጎሩ ባሉበት፣ የግለሰብ እስር መዝገብ የሚይዝ ዳኛ መሰየም፣
    2. ቅዳሜና እሁድ ፍርድ ቤቶች ዝግ ናቸው፤ ወንጀል እየሰራ እጅ ከፊንጅ ያልተያዘን ሰው ለማሳሰር ዳኛ በመሰየም መዝገብ እንዲይዝ በማድረግና ተከፋይ የውሸት ምስክሮችን በማስፈረም የእስርና የብርበራ ማዘዣ በባለስልጣን ትዕዛዝ ማሰጠት፤
    3. ቤት ሲፈተሽና ሲበረበር ተከሳሽ ግለሰብ ከሀገር መጥፋቱ በህግ ሳይረጋገጥ በኮሮና ወቅት የተከሳሹን ባለቤትና ልጆች በማዋከብ “ቤቱን እናሽጋለን፣ ቤቴሰብም እናስወጣለን” እያሉ ለስራ የሄደው ተከሳሽ እስኪመጣ እንኳን ሳይጠብቁ፣ “ታዛቢ አቁመናል” በሚል በምርመራ ከተጠቀሱ ቁሶች ባለፈ ሌሎች ነገሮችን ጭምር ለመውሰድ መጋጋጥ…ወዘተ የህግ የበላይነት ወደ ጎን ተትቶ የፖለቲካ ትዕዛዝ በመሆኑ ፍርድ ቤቶችና የፍትህ ስርዓት ለባለስልጣናት እንጂ ለዜጎች ዋስትና አለመሆኑን ያሳያል፡፡
    ያም ሆነ ይህ ዬላጋ አሰፋ አየለ ንህፁ ህዝቡን የሚወድ፣ ለእውነት የቆመ፣ ያመነበትን ጉዳይ በነጻነት በግልጽ የሚያራምድ፣ ሀሳቡን በነጻነት የሚገልጽ የህዝብ ልጅ ነው፡፡

ዬላጋ አሰፋ አየለ የዎላይታን ህዝብ የማንነትና የክብር አርማ የሆነውን የዎላይታ ባንድራ እያውለበለበ፣ ዎላይታን ህዝብ የህልውና ጉዳይ የሆነውን የክልል ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በጽኑ የሚታገል የህዝብ ልጅ ነው፡፡ ኢ-ፍትሃዊና ኢ-ህገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ የጠበቃ አሰፋ አየለ ቤት መበርበርና የዜጎች እንግልት የወላይታ የለጋን የበለጠ ትግል ያዘጋጃል፡፡

“መብሰሉ ላይቀር ማገዶ ፈጀ” ዓይነት እንዳይሆንባቸሁ የወላይታን ህዝብ የክልል ጥያቄ መልሱ፤ ግልገል ካድሬዎችም እንደ ጌቶቻችሁ ወላይታን መልሶ ማዬት እፍረት እንዳይሆንባችሁ ከክፉዎች ክፉ ሥራ ጋር አትተባበሩ፤ ወላይታ ክልል መሆኑ አይቀርም፤ ከማንም ጋር በጋራ በክልልነት ወላይታ አይደራጅም፡፡

ወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት