የራሱ ማንነት ፣ ባህልና ታሪክ የሌለው ሕዝብ እና ሥር የሌለው ዛፍ አንድ ናቸው!

Wolaita Today

በአምደማርያም ማጬ

የደኢህዴን ካድሬች የወላይታ ሕዝብ ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክ እንዲቀበር ያደረገው የቀድሞ ስርዓት ነው ይሉናል፤እውነቱን እንናገር ከተባለ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ማስተዳደር ከጀመረበት ከ1983ዓ.ም ጀምሮ በወላይታ ውስጥ የተሰራው አበይት ስራ ቢኖር የወላይታ ሕዝብ ማንነት፣ ወግ፣ ልማድ፣ ባህል፣ በዓላት ማጥፋት ነበር፡፡

 

የወላይትኛ ቋንቋም ለማጥፋት ተሞክሯል፡፡ በተለይ በወላይታ ህዝብ እልህ አስጨራሽ ትግል የተቀበረው #ወጋጎዳ; ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፤ ደኢህዴኖች ቢያድበሰብሱትም ሀቅ ተሸፍና አትቀበርም፤ ደኢህዴን ወለድ በሆነው የቋንቋ ትርክት #ወጋጎዳ; መዘዝ ብዙዎች ተሰደዋል፣ ከስራ ገበታቸው ተፈናቅለዋል፣ ታስረዋል፣ መምህራንን ከወላይታ ለማራቅ  በተጠነሰሰው ሴራ ሁለት መምህራን ወደተመደቡበት ሲጓዙ በመኪና የመገልበጥ አደጋ ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ብዙ ቤተሰቦች ለችግር ተዳርገዋል፡፡ በርግጥ ቋንቋ ያድጋል፤ የአፍ መፍቻ ቋንቋውን እንዳይጠቀም መዋቅራዊ በደል ሲፈፀምበት የአፍ መፍቻ ቋንቋው ሊሞት ሁሉ ይችላል፤ ለዚህ ጋፋትኛ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ በተለይ በአስተዳደራዊ የመዋቅር ሸፍጥ አስታኮ በወላይታ ህዝብ ላይ ከደረሰው የኢኮኖሚ ማህበራዊንና የስነልቦና ውድቀት የተነሳ ከገጠር እስከ ከተማ ያለው የወላይታ ተወላጅ ወላይትኛና አማርኛ ቀላቅሎ ይናገራል፡፡ አዲስ “ወላማርኛ” ቋንቋ ተፈጥሯል ማለት ያስችላል፤ ሌላ ቋንቋ ማወቅ ባልከፋ የወርቁ ፍቺ ሌላ ነው፡፡

 

በደኢህዴን ሆነ በቀደሙት አገዛዞች ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ስሰራ የነበረው ጉዳይ ቢኖር ” ባህል አልባ የሆነ፣ ጉራማይሌ ቋንቋ ያለው መፍጠር ነበር፡፡ አንድ ብሔረሰብ ማንነትን፣ ባህልን፣ የራሱን ታሪክ የጣለ እንደሆነ እንዲሁ ሕዝብ ነው የሚባለው፤ ለዚህም ሳይታክቱ የሚሰሩ ወዝቶዎች ሞልተዋል፤ ህዝብን የተስፋ ምግብ እየመገቡ ላያሸግሩ ሸክም የሆኑ ሆድ አደር የደኢህዴን ካድሬዎች፡፡

በወላይታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የህዝብ ጫና ስለበረታ የወላይታ ባህል ተኮር መነቃቃቶች ይታያሉ፡፡ አገዛዞች ለረጅም ዘመን ሲያፈርሱት የነበረውን በአጭር ግዜ መመለስ የማይቻል መሆኑ እሙን ነው፡፡ “የአክሱም ሀውልት ለወላይታው ምኑ ነው” ተብሎ በህዝብ እንደራሴዎች ጉባኤ ሲዘባበቱም ሆድ አደር የደኢህዴን ካድሬዎች ሆነ የሀውልት አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ አፈጉባኤው የወላይታ ተወላጅ አፉ ለሆድ ሲል ተለጉሟል፤ በፋሽስት ሙሶሊኒ ትእዛዝ ከአክሱም ተዘርፎ ለ66 ዓመታት ያክል በባዕድ አገር ኢጣሊያ ሮም ውስጥ የኖረው ባለ 24 ሜትር ቁመት፣ 160 ቶን ክብደትና ከ1,700 ዓመት በላይ ዕድሜ ጠገብ ሀውልት ተመልሷል፤ የወላይታ ባህልም ከተሰራበት የፈለገውን ያህል ግዜ ቢወስድም ወደነበረበት መመለስ ይቻላል ብሎ መስራት አስተዋይነት ነው፡፡ አሁን በሶዶ ከተማ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ለታይታ እና የአንድ ሰሞን ሞቅታ ሆኖ እንዳይቀር ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

ነገረ ስራችን እንደ ደረቅ ባሕር ዛፍ ቅጠል እሳት አይሁን፤ እንደ “ቦርቷ ቦንቋ” ይሁን !!!