አቶ በቀለ ገርባ ከኦፌኮ መልቀቃቸውን እና በአሜሪካ ጥገኝነት መጠየቃቸውን ተናገሩ

28 ነሐሴ 2023 (የቢቢሲ ዘገባ)

ለረዥም ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በግል እና በፓርቲ ደረጃ ተሳታፊ የነበሩት አቶ በቀለ ገርባ ከፓርቲያቸው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በመልቀቅ በአሜሪካ ጥገኝነት መጠየቃቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ።

አቶ በቀለ ለቢቢሲ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ “በሰላማዊ መንገድ ለመታገልም ሆነ በግል በነጻነት መኖር” አሳሳቢ በመሆኑ በሄዱበት በአሜሪካ ለመኖር ጥገኝነት መጠየቃቸውን ገልጸዋል። የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ምክትል የሆኑት አቶ በቀለ፣ በውጭ አገር ሆነው ሥልጣኑን ይዘው መቀጠለቸው ጠቃሚ ስላልሆነ እራሳቸውን ከፓርቲው ለማግለል መወሰናቸውንም ተናግረዋል።

አቶ በቀለ ገርባ ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ ተፈጥሮ የነበረውን ሁከት ተከትሎ በቁጥጥር ሥር ውለው ለ18 ወራት በእስር ላይ ቆይተው ከተለቀቁ በኋላ ወደ አሜሪካ ተጉዘዋል። አቶ በቀለ ከእስር ከወጡ በኋላ ወደ አሜሪካ ሲጓዙ ዓላማቸው የእርሳቸውን ከእስር መለቀቅ ሲጠይቅ ለነበረው የዳያስፖራ ማኅብረሰብ ምስጋና ለማቅረብ እንጂ በዚያው የመቅረት ዕቅድ እንዳልነበራቸው ጨምረው ተናግረዋል።

“ወደዚህ አገር ከመጣሁ አንድ ዓመት ከሦስት ወር ሆኖኛል። መጀመሪያ ስንመጣ የነበረኝ ዕቅድ በውጭ ከሚኖረው ሕዝባችን ጋር ተገናኝተን፣ አንደኛ ከእስር እንድንለቀቅ ላደረጉት ትግል ለማመስገን ሁለተኛ ደግሞ ወደፊት ምን ማድረግ አለብን የሚለው ላይ ለመወያየት ነበር” ብለዋል።

አቶ በቀለ አሜሪካ በቆዩባቸው 15 ወራት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በመቀየሩ “ወደዚያ አገር መመለሱ አስፈላጊ መስሎ አልታየኝም” ብለዋል። ወደ አገር እንዳይመለሱ ያደረገቸው በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ሁኔታን ሲያስረዱም “በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ከመጣበት ወዲህ በተለይ ደግሞ ያለፈው ዓመት እጅግ አደገኛ ነው” ብለዋል።

“ከአንድ ዓመት ወዲህ ያለው በጣም የሚያሳዝን ነው። ሰዎች ከእስር ቤት እየተወሰዱ ይገደላሉ፣ የፈለገ አካል ሰው ይዞ ያስራል፣ የሰዎች አድራሻ ይጠፋል፣ ሰው ከመሬቱ ይፈናቀላል፣ ኦሮሞ ድንበሩ ተሰብሮ ቤቱ ይቃጠላል፣ በሕይወት እያለ በቁሙ በእሳት ይቃጠላል፣ እራሱ በቆፈረው ጉድጓድ ውስጥ ተገድሎ እንዲቀበር የሚደረግም አለ።”

የፖለቲካ ፓርቲዎች ጽሕፈት ቤት ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚባልበት መልኩ ተዘግተዋል የሚሉት አቶ በቀለ፤ በዚህ ምክንያት በአገሪቱ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማድረግ አይቻልም ብለዋል።

“በዚህ ሁኔታ ውስጥ በሕይወት እንኳ መቆየት አሳሳቢ የሆነ ደረጃ ላይ ተደርሷል። ሁለተኛ ደግሞ ወደዚያ አገር በመመለስ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ስለማይቻል እና የማመጣው ውጤት ስለማይኖር እዚሁ ለመቆየት ወስኛለሁ።”

አቶ በቀለ ከዚህ ቀደም ወደ አገር ቤት በተመለሱበት ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወደነበራቸው የመምህርነት ሥራ መመለስ እንዳልቻሉ ሲያስረዱ፣ “ከእስር ቤት እንደወጣሁ ዩኒቨርሲቲው እድሜህ 60 ዓመት ሞልቷል በማለት ጡረታ አስወጥቶኛል” ብለዋል።

“ከእስር ቤት እንደወጣሁ ደብዳቤ ላኩልኝ። 60 ዓመት ስለሞላህ ጡረታ ወጥተሃል አሉኝ። ጡረታዬን ለማስከበር ያደረኩት ጥረትም ሳይሳካ ቀርቷል። ዕድሜ ልኬን ስለፋበት የነበረውን ሳላገኝ ቀርቻለሁ። በዚህም ባዶ እጄን በሰው አገር ለመቅረት ተገድጃለሁ።”

አቶ በቀለ ገርባ ወደ ኢትዮጵያ ቢመለሱ ለሕይወታቸው አስጊ መሆኑን አሁን ባሉበት አገር ማሳወቃቸውን እና የጥገኝነት ማመልከቻቸውን ማስገባታቸውንም ለቢቢሲገልጸዋል።