ኢትዮጵያንና ህዝቦችዋን ለማዳን…

Wolaita Today

በስምዖን ሄልሶ

ነሐሴ 27 2012ዓ.ም

ኢሃዲግ/ብልጽግናም ሆነ ወደ ፊትም ድንገት ሥልጣን ቢይዙ በብሔር የተደራጁ ወይም ሶሻሊዝም ቀመስ ፓርቲዎች የሥልጣን መሠረታቸው ሁለት ነገሮች ብቻ ናቸው። የመሬት ሥሪትና የመንግሥት ሥራ።

እነዚህ ሁለት ነገሮች የመንግሥት ወይም የፓርቲ ሃብት ሳይሆኑ የህዝብ፥ ማለትም የእያንዳንዱ ሰው፥ የእኛ የኢትዮጵያውያን ሃብቶች ናቸው።

ሃብታችንን በግርግር የፖለቲካ መሪ ነን ብለው ለተሰለፉ ሥራ አጥ ሌቦች አሳልፈን በመስጠት ሥቃያችንን የጨመርን፥ ሃገር እንድትፈርስ፣ ህዝብ እንዲተላለቅ የፈቀድን እኛው ነን። መፍትሔውም አጭር። ሃገርና ህዝብ እንዲድን ፖለቲከኞች ሃብቶቻችንን እንዲለቁ ማስገደድ ያስፈልጋል።

ከእጃችን የቀሙትን ሃብት በመጠቀምና ላሻቸው በማደል ሌላውን ህዝብ በሙሉ ቀፍድደው በመያዝ እርስ በርስ እያባሉ ሥልጣናቸውን የሚያደላድሉበትን መሥመር ካልዘጋን ሰቆቃችን የሚቀጥል ይሆናል።

የህዝብ ሞኝነት እና የፖለቲከኞች የሥልጣን ጥማት እየከፋ ሲሄድ ምናልባትም ኢትዮጵያ ተፈረካክሳ ሃያ ሁለት ሃገር ሆናም አሁን አሉ የሚባሉ የህዝብ ጥያቄዎች አይመለሱም።

በመጀመሪያ የመንግሥት ሥራ በፖለቲካ ወገንተኝነት የሚታደል ችሮታ ሣይሆን ብቃቱ ያለው ማንም በግልጽ መሥፈርት ተወዳድሮ የሚያገኝበት ሥርዓት የግድ ነው። ፖለቲከኞች ይህን መከልከል ሲፈልጉ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ ተማሪዎችን አባል መለመሉ። የአባል ብዛት ደግሞ ሃይላቸውን ያበዛላቸዋል። ዘልቀን ስናስበው ግን ሁሉ አባል ከሆነ ሰጡ የተባለው ችሮታ ሃይል ያካበቱበት መሠሪ መንገድ ብቻ ሳይሆን አባል የተባለው በነጻነት እንዳያስብ ነጻነቱን የተቀማበት ክፉ ምክር ነው። በውድድር ቢሆንም ውጤቱ ተመሣሣይ ይሆን ነበር።

“ራስን በራስ” የተባለው ፈሊጥ እንኳ ግማሽ መፍትሔ ብቻ እንደሆነ ያለፉት ሠላሳ ዓመታት አስተምረውናል። ብቃትን መሠረት ያደረገ ያልተማከለ አሠራር ብቻ እንዲመጣ ግፊት እናድርግ።

መሬትን ለመንግሥት ሰጥቶ ህዝብን የመንግሥት ጭሰኛ ያደረገው የመሬት ሥሪት ግን ዋነኛው ሃገር አፍራሽ ማነቆ ነው። ይህ ሥሪት በኢሃዲግ መቃብር ላይ እንጂ በምንም እንደማይቀየር ሲነግሩን የነበረው በከንቱ አልነበረም። ምንኛ ቁልፍ የማታለያ ሥልት እንደሆነ ልናውቅ ይገባን ነበር። መሬትን የመሰለ የራሳችን አንጡራ ሃብት ለጥቂት ፖለቲከኞች ጥቅም አሳልፈን ሰጠን። መሬቱን የሚቸበችበው የፖለቲካ ተሿሚው ነው። “የብሔርህ መሬት ተበላ” እያሉ እያነሳሱት እርስ በርስ የሚገዳደለው ግን ተራው ወጣት። እንደምን ተበላን ወገኖች?

ጥቂት የህዋሃት ባለሥልጣኖች ባደረጉት ዘረፋ ትግሬ በሙሉ በሌብነት ተፈረጀ። ምንም ጠብ ያላለላቸው እልፍ ትግሬዎች ተጠሉ። የመኖር ዋስትናቸው አጥተው በገዛ ምድራቸው አንገታቸውን ደፍተው እንዲሄዱ ተደረገ። ዘራፊው ግን ባማረ ቤቱ በሰላም ይንፈላሰሳል።

ተረኛ ተጠቃሚ ሳይሆን ተረኛው አንገት ደፊ ኦሮሞ ነው። ዛሬ ባያስተውል የፖለቲከኞች ሸፍጥ ነገ ግልጽ ይሆናል። ለጥቂት የኦሮሞ ልጆች የተቃመሰ የመንግሥት ሥራ እና መሬት ሚሊዮኖች ኦሮሞዎችን አንገት ማስደፋቱ አይቀሬ ነው። አይተነዋል። ይሆናል።

ይህ እንዳይሆን መሬትንና የመንግሥት ሥራን ከፖለቲከኞች ተፅዕኖ ነጻ ማውጣት ግድ ነው። አርሶ አደሩ የያዘው መሬት ሃብቱ እንደሆነ ይደንገግ። የመንግሥት አይደለም። የእርሱ የራሱ ነው። መንግሥት የሚባለው መብቱ ቀረጥ ብቻ ነው እንጂ የሃብት ምንጮች ሁሉ የህዝብ ናቸው። የእያንዳንዱ ግለሰብ ናቸው። ማንኛውም መሬት ይሸጥ ይለወጥ። ይህ ግድ ነው። ከብሔርህ ውጭ ይገዛብሃል ብሎ ማስፈራራት ይቅር። ፖለቲከኛው ቀምቶ ለእናቱ ልጅ አልነበረም የሸጠው። ለቻይናና ለህንድ ባለሃብቶች እንጂ። ያውም በዝርፊያ ያክል ኢምንት ገንዘብ።

ገዢውም ሌላ ብሔር መሆኑ ቀርቶ ግብጻዊም ሆነ ጣሊያን ቢሆን በቂ ገንዘብ ለአርሶ አደሩ እስከ ሰጠ ድረስ መብቱ ሊጠበቅ ይገባል። ገበሬ ወይም የከተማ ባለ ንብረት ያልያዘውን መሬት በመንግሥት ሃብትነት ለጊዜው ለባለ ሃብት እስኪተላለፍ ድረስ ፖለቲከኛ ይጋጠው።

ሥራ እና መሬት “መንግሥት ነን” ከሚሉ ዘራፊ ፖለቲከኞች እጅ ካልወጡ በቀር ሰቆቃችን በሰፊው ይቀጥላል፤ ብንገነጣጠል ስንኳ አይቀርልንም፤ እንቅጩን ልንገራችሁ።