እውነት የህግ የበላይነትን የማስከበር ሞራል አለህ?!

በራፍኤል አዲሱ

ነሐሴ 27 2012ዓ.ም

መልስህ “አዎን” ከሆነ የህዝቡን ህገመንግስታዊ የክልል አደረጃጀት ጥያቄ ያነሱ በዎላይታ ህዝብ ምክር ቤት የተሾሙ የፊት አመራሮችን: የመብት ታጋዮችንንና ነጋዴዎችን እንዲሁም የተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን አንዴ ከ’ህወሓትና ኦነግ ሸኔ’ ጋር አሲረዋል ብለህ ክስ መስርተህ ስታበቃ: አላስኬድ ሲልህ ክስህን በ’ሙስና ወንጀል’ ቀይረህ ከማጉላላትህ በፊት:-

ከ2010-2011 ዓ. ም. ሀዋሳ ላይ በብሔር ተኮር ጥቃት ቤቶችን ‘mark’ አስደርገው በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሀን ዜጎችን የገደሉ: ያስገደሉ: በአስርት ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ያደረጉ: በተከታታይ የንግዱን ማህበረሰብና የግለሰቦችን ንብረት በእሳት እንዲቃጠል ያደረጉትን ለህግ አቅርብ: ሀገሪቱ በምትመራበት ህግም ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ አድርግ::

በ2010 ዓ.ም. ሻሸመኔ: ዝዋይና ሌሎች አከባቢዎች ላይ ለተገደሉ: ለተፈናቀሉና ንብረታቸው ለወደመባቸው ሰዎች ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦችን ወደ ህግ አቅርብ ተገቢውን የህግ ቅጣትም እንዲያገኙ አድርግ:: በእነዚህ ብሔር ተኮር ጥቃቶች ንብረታቸው ለወደመባቸው ሰዎች ተገቢው ካሳ እንዲያገኙ አድርግ::

በ2011 ዓ.ም. በፌዴራል ኦዲት ቢሮ ሰራተኞች ከደቡብ ክልል አመታዊ በጀት ከ7ቢሊየን ብር በላይ የዘረፉ ግለሰቦች (በወቅቱ ከፍተኛ የክልሉ መንግስት ባለስልጣናት የነበሩ) በፌዴራል ፖሊስ ተይዘው ሲያበቁ ኋላ ላይ ደብዛው እንዲጠፋ የተደረገበትን የሙስና ወንጀል ተከታትለህ ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡና የህዝብ ሀብትም እንዲመለስ አድርግ::

ከነሐሴ 3, 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በነበረው ሳምንት ወቅት በዎላይታ በመንግስት ወታደሮች ሰላማዊ ህዝብ ላይ ለተደረገ ጭፍጨፋ ተጠያቂ የሆኑ የቀድሞው የደቡብ ክልል ባለስልጣናትን (የክልሉ ምክር ቤት አባል ከሆኑ ያለመከሰስ መብታቸው በምክር ቤቱ ተነስቶባቸው) በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ አድርግ: ለሰሩት ወንጀልም በሀገሪቱ ህግ መሰረት ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ አድርግ::

ይህን ስታደርግ ያኔ ከላይ መግቢያው ላይ የጠቀስኳቸው አካላት ወንጀለኛ ከሆኑ በየትኛውም በሀገሪቱ ስልጣን ያለው ፍርድ ቤት እነዚህን ግለሰቦች የመክሰስ መብትህን አከብርልሀለው:: ከዚህ ውጭ ግን የህዝብን ድምፅ ለማፈን: ህገመንግስታዊ መብትና ስልጣኑን በሀይል ለመጨፍለቅ የሚደረግ በፖለቲካ ፍላጎት የተመሰረተና (politically motivated) ብሔር ተኮር (ethnicly targeted) የክስ ሂደት የትም የማያደርስ የከሰረ ፖለቲካ ስርዓት በትር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል::

ይህች ሀገር ከህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ይልቅ ለፖለቲካ ፓርቲ ህልውና በቆሙ: በሙስና እጃቸው በተጨማለቀና: በስልጣን ጥማት በሰከሩ ባለስልጣናት የሀገሪቱን ህግ ለእነሱ በሚመች መልኩ ብቻ እያጣመሙ በሚተገብሩበት አካሄድ አንድ እርምጃ እንኳ ወደፊት መሄድ እንደማትችል ይልቅ ወደ መፍረስ ጫፍ እየገሰገሰች እንደሆነ ማን በነገራቸው::

Wolaita Today
Wolaita Today