ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከየዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን) የተሰጠ መግለጫ

በሀገራችን ለWolaita6ኛ ሀገራዊ ምርጫ ዝግጅት እየተደረገ የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ድርጅታችንም በተቋቋመ በአጭር ጊዜ አደረጃጀቱን በማጠናከር ፣ በዎላይታና በተለያዩ ሀገሪቱ አከባቢ ደጋፊዎችንና አባላትን በማነቃነቅ የምርጫ ዝግጅት ሥራ ጀምሮ ባለበት ወቅት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ሀገራዊ ምርጫ በተያዘለት ጊዜ ለማካሄድ እንደማይቻል መግለፁን ተከትሎ ንቅናቄያችን በሌሎች ድርጅታዊ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።

ሀገራችን የተጋረጠባትን በአንድ በኩል ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ደቅኖ የሚገኘውን ወረርሽኝ የመከላከል ጉዳይ ፤ በሌላ በኩል ሀገራዊ ምርጫ በተቀመጠው የጊዜ ሠሌዳ ባለመደረጉ ምክንያት ሀገሪቱን እየመራ ያለው መንግስት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሀገሪቱን የማስተዳደር ጊዜ ገደብ የሚያበቃ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሊፈጠር የሚችለውን ህጋዊ ቅቡልነት ያለው መንግሥት አልባነት ምን ዓይነት ዕልባት ሊበጅለት ይገባል በሚሉ ጉዳዮች ላይ የድርጅታችን አመራር አካላት በሰፊው ሲመክርበት ቆይቷል። አልፎም የዎላይታ ሕዝብ የራሱን ክልላዊ መስተዳድር ለመመስረት ያቀረበው እጅግ ሠላማዊ፣ ፍትሐዊና ህገ-መንግሥታዊ ጥያቄ ምላሽ ሳይሰጥ መቆየቱ እጅግ የሚያሳስብና መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ሊመለከተው የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ተመልክተናል፡፡ ከተጠቀሱ ሁኔታዎች በመነሳት ንቅናቄያችን ቀጥሎ የተመለከቱ ባለ 3 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

  • ከኮሮና ቫይሬስ ወረርሽኝ ጋር በተገናኘ የድርጅታችን አመራር አካላትና አባላት በየማህበራዊ መሠረታቸው አቅማቸው በፈቀደ መጠን ሲያደርጉ ለነበረው በጎ ተግባር ዎብን ላቅ ያለ ምስጋና ያያቀርባል። ከዚህ በፊትም በተሰጠው መግለጫ እንዳሳሰብነው የበሽታው ስርጭት ይበልጥ እየተስፋፋ በመጣበት በዚህ ወቅት በህብረተሰቡ ዘንድ እየታየ ያለው መዘናጋት ተጋላጭነታችንን በመጨመር ለወረርሽኙ መስፋፋት ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑ ግንዛቤ ተወስዶ ሁሉም ዜጋ የወረርሽኙን ሥርጭት ለመግታት የሚረዱ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በአግባቡ በመተግበር ራሱንና ማህበረሰቡን ከአደጋ ለመከላከል ለሚደረገው ርብርብ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ዎብን በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል።
  • በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሀገራዊ ምርጫ መራዘሙ የዜጎችን ሕይወት ከአደጋ ለመታደግ የተወሰነ እርምጃ መሆኑን በቅንነትና በሆደ ሰፊነት እንረዳለን፡፡ ሆኖም ሀገራዊ ምርጫ በጊዜ ባለ መደረጉ ምክንያት ሀገሪቱን እያስተዳደረ የሚገኘው መንግስት የሥልጣን ጊዜ ገደቡ የሚያበቃ በመሆኑ ለሚፈጠረው የመንግሥት ክፍተት ዕልባት በመስጠት ረገድ ሀገሪቱ ውስጥ ካሉ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በመተማመን ላይ የተመሠረተ ውይይት በማድረግ መፍትሔ ከመመፈለግ ይልቅ ገዥው ፓርቲ ባቀረባቸው አማራጮች ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ እየተከሄደበት ያለው ሁኔታ ዘላቂ መፍትሔ ያመጣል ብሎ ንቅናቄያችን አያምንም፡፡ በመሆኑም በዚህ ወሣኝ ምዕራፍ ድርጅታችን ዎብንን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የሚሳተፉበት ፍትሐዊና ግልፅ የሆነ የምክክር መድረክ እንዲፈጠርና በሚቀርቡ ሐሳቦች ላይ በመተማመን ላይ የተመሠረተ ውይይት ተካሂዶ ስምምነት በተደረገባቸው ጉዳዮች ላይ የሕዝብ አስተያዬት ተሰጥቶ የመጨረሻ ዕልባት የሚሰጥበት ሁኔታ እንዲመቻች አበክረን እንጠይቃለን፡፡
  • የወላይታ ሕዝብ ላለፉት ሁለት ዓመታት እጅግ ሠላማዊ በሆነ መንገድ የራሱን ክልላዊ መስተዳድር የመመስረት ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ከቀበሌ እስከ ዞን ምክር ቤት ድረስ ባሉ የህዝብ ምክር ቤቶች የፀደቀው የሕዝቡ ጥያቄ ለክልሉ ምክር ቤት ቀርቦ ምላሽ በመነፈጉ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ መልስ እየተጠበቀ ይገኛል፡፡ በጉዳዩ የሀገራችን ጠቅላይ ሚኒስቴርና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙባቸው በተለያዩ የሕዝብ መድረኮች የወላይታ ሕዝብ በክልል ለመደራጀት ያስፈለገበትን ዋና ዋና ምክንያቶችን በግልፅ በማስቀመጥ ሕዝቡ በጨዋነት፣ ሕግን በመከተልና ፍፁም ሠላማዊ በሆነ መንገድ የቀረበው ሕገ-መንግሥታዊና ፍትሐዊ የሆነ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ እንዲሰጠው በአንክሮ አሳውቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሠላም አምባሳደር የተባለው በጠቅላይ ሚኒስቴሩ የተቋቋመው ኮሚቴ በወላይታ ሶዶ ባዘጋጀው የሕዝብ መድረክም የዎላይታ ሕዝብ ፍላጎት የራሱን ክልላዊ መስተዳደር መስርቶ መተዳደር እንዲሚፈልግ በግልፅ አስቀምጧል፡፡ ሆኖም ኮሚቴው በየአከባቢው የተደረጉ የሕዝብ መድረክ ሪፖርቶችን በሚያቀርብበት ጊዜ አንዳንድ የተለየ ተልዕኮ ያነገቡ የኮሚቴው አባላት የወላይታ ሕዝብ ከጠየቀው ባፈነገጠ መልኩ ተዛብቶ እንዲቀርብ ማድረጋቸውን ለመረዳት ችለናል፡፡ በዚህም ምክንያት ከዎላይታ የተወከሉ የሠላም አምባሳደር ኮሚቴ አባላት ከኮሚቴው ራሳቸውን ማግለላቸውን ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ካቀረቡት ማመልከቻ ለመረዳት ችለናል፡፡

ይሄን ሁኔታ ስናጤነው ሕዝቡ በሰከነና በሠላማዊ መንገድ ላቀረበው ጥያቄ በሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት ከተቀመጠው ድንጋጌ በተፃረረ ሁኔታ ፖለቲካዊ ውሳኔ ለመወሰን እየተከሄደበት ያለው ዝንባሌ በአከባቢው የሠላም ዕጦት እንዲከሰት ዓይነተኛ ምክንያት እንደሚሆን ከዚህ በፊት በዎጋጎዳ አስተዳደር ወቅት ተከስቶ የነበረው ሁኔታ እማኝ ነው፡፡ አካሄዱ ሕዝቡ በሕገመንግሥት፣ በሕግና በመንግሥት የሚኖረውን እምነት በመሸርሸር ለማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮሚያዊ ቀውስ መከሰት ምቹ መደላድል የሚፈጥር በመሆኑ የዎላይታ ሕዝብ በሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት የራሱን ክልላዊ መስተዳድር ለመመስረት ያቀረበው ጥያቄ ተገቢ ምላሽ እንዲሰጠው አበክረን እንጠይቃለን፡፡

በዚህ ሂደት አንዳንድ የአጎራባች አከባቢዎች ልሂቃንና የከሰሩ ፖለቲከኞች በሕዞቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን አብሮነትና መልካም ጉርብትና በመካድ የግላቸውንና የቡድናቸውን ጠባብ ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ በወላይታ ሕዝብና በአጎራባች ሕዝቦች መካከል ጥላቻ ከመዝራት ዕኩይ ተግባራቸው እንዲታቀቡ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡ በሕዝቦች መካከል የነበረው ዘመን ተሻጋር መስተጋብር ከልህቃንና ከጥቂት ቡድንተኞች ፍላጎትና ጥቅም ይልቅ የሚዘልቅ መሆኑን በመገንዘብ ከጥፋት ተግባራቸው በመመለስ ለሠላም ግንባታ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ (ዎብን)

ግንቦት 12 2012 ዓ.ም

ወላይታ ሶዶ