“ልጄ ታስሮ ወደሚገኝበት ቦታ እንጀራ ይዤለት ስሄድ አጣሁት . . . የልጄ አስክሬን በሸራ ተጠቅልሎ ሜዳ ላይ ተጥሎ አገኘሁ” ሲሉ በምዕራብ ኦሮሚያ ልጃቸው በጸጥታ ኃይል የተገደለባቸው እናት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ወጣት ለሊሳ ተፈሪ በምዕራብ ወለጋ ዞን የገንጂ ወረዳ ነዋሪ ነበር። ከሁለት ሳምንት በፊት በአካባቢው ተሰማርቶ በሚገኘው የመንግሥት ኃይል በቁጥጥር ሥር ከዋለ ከሁለት ቀናት በኋላ ሞቶ መገኘቱን የለሊሳ ቤተሰቦች ይናገራሉ።
ግንቦት 2/2012 ዓ.ም ከገበያ ስፍራ በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋለው ለሊሳ ከሁለት ቀናት በኋላ ማለትም ግንቦት 4 አስክሬኑ ሜዳ ላይ ተጥሎ መገኘቱን ወላጅ እናቱ ወ/ሮ ጫልቱ ሁንዴሳ እና አባቱ አቶ ተፈሪ ዱጉማ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ለሊሳ ትዳር ለመመስራት በዝግጅት ላይ እንደነበረ እና እጮኛውን ለማግኘት በወጣበት ወቅት መያዙን የቤተሰብ አባላቱ ይናገራሉ። የለሊሳ ተፈሪ እናት ወ/ሮ ጫልቱ ሁንዴሳ እንደሚሉት ከሆነ፤ ለሊሳ አዲስ አበባ ከተማ የምትገኝ እህቱ ጋር ይኖር እንደነበረ እና ወላጆቹ ወደሚኖሩበት አከባቢ ከተመለሰ ሁለት ወራት አልሆነውም።
በቀጣዩ ዓመት ለማግባት አቅዶ የነበረው ለሊሳ፤ በጉዳዩ ላይ ከእጮኛው ጋር ለመመካከር ገንጂ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ባለ የገበያ ቦታ ቀጠሮ ይዞ እጮኛውን ለመግኘት እንደወጣ አለመመለሱን ይናገራሉ ወ/ሮ ጫልቱ ይናገራሉ።
“ቀኑ ሰንበት ነበር። ከእሷ ጋር እያወራ ገበያ ላይ ያዙት። ታስሮ ይገኘበታል ወደተባለው ቦታ እንጀራ ይዤለት ስሄድ ከዚያ አጣሁት። ‘ማንን ነው የምትፈልጉት?’ ሲሉ ጠየቁኝ ‘ለሊሳ ተፈሪ’ ብዬ ስመልስላቸው ‘እሱ ከዚህ ወጥቷል’ አሉኝ።”
ወ/ሮ ጫል ልጃቸው የት እንደተወሰደ ደጋግመው ሲጠይቁ በአንድ የጸጥታ አባል ተመነጫጭቀው እና ‘አጸያፊ ስድብ’ ተሰድበው መባረራቸውን ይናገራሉ። ከዚህ ቀደም ለሊሳ ታስሮም ሆነ ጥፋተኛ ተብሎ ተከሶ እንደማያውቅ ወላጆቹ ይናገራሉ። አሁን ተይዞ በነበረበት ወቅትም ወደ ፍርድ ቤት አለመወሰዱን ይናገራሉ። ለምን እንደተሳረም ከሚመለከተው አካል የተነገራቸው ምንም መረጃ የለም ይላሉ።
“ፍርድ ቤት ሳይቀርብ፣ ጥፋተኛ ሳይባል፣ ሞት ሳይፈረድበት በመንግሥት ጦር ተገደለ” ይላሉ ወላጅ አባቱ አቶ ተፈሪ ዱጉማ። እናቱ እንደሚሉት ለሊሳ ‘ቻይና ካምፕ’ ተበሎ በሚጠራው ቦታ ታስሮ እያለ፤ ለሊሊሳ ምግብ ይዘው የሄዱ ወጣቶችን “ወታደሮች ‘እሱ ሸኔ ነው’ ብለው አበረሯቸው።” ወላጅ እናቱ ግን ልጃቸው የሸኔ አባል ስለመሆኑ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ይናገራሉ።
በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ ዞኖች እንዲሁም በደቡብ ኦሮሚያ ጉጂ እና ቦረና አካባቢዎች ታጠቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን መንግሥት ‘ሸኔ’ ሲል ይጠራቸዋል። እነዚህ ታጣቂዎች የቀድሞ የኦነግ ጦር አባላት ነበሩ ሲሆን መንግሥት እና የአገር ሽማግሌዎች የቡድኑ አባላት ትጥቅ ፈተው ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ ለማስገባት ያደረጉት ተደጋጋሚ ጥረት ሳይሳካ መቅረቱ ይታወሳል።