ይህንን ጽሁፍ ለማዘጋጀት ካሰብኩ ቆይቻለሁ፡፡ የጊዜ አለመመቻቸት የሌሎች አጀንዳዎች ሽሚያ እና በኮሮና ምክንያት በአብዛኛው ትኩረቴን ሰብአዊነት ላይ ማድረግ ወስኜ ስለነበረ አዘግይቼዋለሁ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በሶሻል ሚዲያ አታሚዎች የልማት ባንክ የወላይታ ዲሰትሪክት አጁታ በሚባል መካከለኛ አቅም ያለው ጠጠር አምራች ላይ እንዲሁም በወላይታ ነጋዴዎች ላይ ተጽእኖ አድርጓል ብሎ መዘገቡን ሳይ ይህ ጉዳይ መነሳቱ ላይቀር ወላይታ ላይ ያሉ ባንኮች በወላይታ የእድገት እና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ላይ ስላላቸው ሚና እንዲሁም የኢትዮጵያ ባንኮች ዛሬአዊ እውነታ ምን ይመስላል የሚሉትን እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች እዳስሳለሁ ፡፡ ይህ ጽሁፍ ለዲጂታል አንባቢ ታስቦ እና ባንኮች በኢትዮጵያ እና በተለይ በወላይታ ያላችውን የፖሊቲካል ኢኮኖሚ ሚና እና የሚያሳድሩትን ተዘዋዋሪ ፖለቲካዊ ተጽእኖ እንድምታውን ለመጠቆም ስለሆን ሙያው ያላቸው ሰዎችም ሆኑ መላዉ አንባቢ ይህንን ከግንዛቤ እንዲያስገባ ኣሳስባለሁ፡፡ አጁታን በተመለከተ ከኮሮና ጋር ተያይዞ ምንም የንግድ እንቅስቃሴ ማድረግም ብድር መክፈልም ስለማይቻል በምክክር ቢታቀድበት እና በቂ ጊዜ ቢሰጠው መልካም ነው፡፡
ለመነሻ ያህል በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ስር የሚተዳደሩ ሁለቱ አውራ የመንግስት ባንኮች ንግድ ባንክ እና ልማት ባንክ ናቸው፡፡ በግሉ ዘርፍ የሚመሩት አንጋፋ ባንኮች ዳሽን ዘመን፣ አዋሽ ፣ ህብረት፣ አቢሲኒያ፣ አንበሳ፣ ቡና፣ ብርሃን፣ ኦሮሚያ ኮኦፕሬቲቭ አሁን እየተቋቋሙ ካሉትም ኣማራ ባንክ እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ ደቡብ ግሎባል ለአቅመ ባንክ መድረሷን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
የተቋማት ዝርዝር እንቅስቃሴዎቻቸው ላይ እንዲሁም የባንኪንግ ስራቸው ላይ ብዙ መነጋገር ቢቻልም የጽሁፉ አላማ ይህ ስላልሆነ ባንኮቹ እንደተቋማት ስብስብ ስላላቸው የፖለቲካል ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ተጽእኖ ላይ እና በህዝቡ ዕለታዊ ህይወት ላይ ስላላቸው ሚና መነጋገሩ የተሻለ ነው፡፡ ታዲያ ግን ባንኮቹ ባለቤቶቻቸው እነማን እንደሆኑ የሚሰጡት የብድር ፋሲሊቲ ተጠቃሚው የየትኛዉ የህብረተሰባችን ክፍል መሆኑ የትኞቹስ ብሄሮች በብዛት እንደተወከሉ ሃገሪተዋ ውስጥ የካሽ ክምቸት ማዕከል ከሚባሉት መሃል ወላይታ ምን ያህል እንደሚያበረክት ከዚህ አንጻር ወላይታው ምን ድርሻ እንዳለው ካለው ድርሻ አንጻርም ወላይታው በከተሞቹ ባሉት ባንኮች ምን ያህል ከተጠቃሚነት ገሸሽ እንደሚደረግ ለማየት እንሞከራለን፡፡
የመንግስት ከሆነው ከንግድ ባንክ እንጀምር እና ሙሉ መረጃው ባይኖረኝም አብዛኛው ባህር ዳር እና አከባቢው የሚገኙ ሆቴሎች ስብስብ ብድር ያገኙት ከንግድ ባንክ ነው የሚል መረጃ አለ፡፡ ይህንን ተከትሎ የማኔጀር ሽግሽግ ሲደረግ የባንክ ቡክ ከማቃጠል ዘመቻ እስከ አዲስ ባንክ የመመስረት ዘመቻ ውስጥ መገባቱን ይህንን ተከትሎም አማራ ባንክ መቋቋም አለበት በሚል እነቅስቃሴ መጀመሩን ማንም ሰው ያዉቃል፡፡ ልማት ባንክም ቢሆን በሃገራዊ ደረጃ በቢልየን የሚገመት ገንዘብ ያለ ተጠያቂነት በአብዛኛዉ ለቀድሞው ኢህአዴግ ሽርኮች መስጠቱን እና ኪሳራም እንደደረሰበት የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ መረጃው ሲታይ በኢትዮጵያ የብድር ተጠቃሚ የሚባሉት የትግርኛ ተናጋሪዎች የኣማራ ተወላጆች የኦሮሞ ተወላጆ ስልጤዎች፣ ጉራጌዎች እና አደሬዎች መሆኑን ያሳያል፡፡ እነዚህ መጠቀማቸው ክፋት አለው ብዬ አላስብም፡፡ ወላይታው እና ሌላው የደቡቢቷ የሃገራችን ክፍል ተወላጅ አለመጠቀሙ ግን ትክክል ነው ብዬ አልወስድም፡፡ እንግዲህ ልማት ባንክ የዎላይታው ዲስትሪክቱ ሶዶ ከተማ እና አቅራቢያው ያሉ ነጋዴዎችን በማበረታታት ብድር ማመቻቸቱን ለማወቅ ዊን ውሃ አጁታ ተጠር ማምረቻ እርሻዎች እና ሌሎች በብዛት መካከለኛ ኢንቨስትምንቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ልማት ባንኩ ከሌሎች ባንኮች አንጻር ሊመሰገን የሚገባው ነው ማለት ማጋነን አይሆንም፡፡
የባንኮች ችግር ከተነሳ አይቀር የወላይታ ነጋዴ ከቸርቻሪነት ባህሪ አለመላቀቅ በፊት የነበሩት ባንኮች የአከባቢው ህዝብ እንዳያድግ በሚል ብድር ይከለክሉ ስለነበረ ነጋዴው እነደማይተማመንባቸው፤ ይህንን ለማስተካከልም ሆነ ካፒታል ለመፍጠር በብዙ ሚልየኖች እቁብ እንደሚገቡ፤ ለባንኮቹ የብድር አሰጣጣቸውን ቅሬታ ሲያሰሙ የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ውስጥ ላሉ ግለሰቦች መደለያ ብድር በማመቻቸት እምቢ ሲሉም የቀድሞ ብድር አመላለስ ሂደትን መያዣ በማድረግ እና በማስፈራራት የነጋዴው ድምጽ እነዲታፈን ማድረግ፤ ነጋዴው ብድር የሚወስድበትን መስፈርት ከሌላው አከባቢ አንጻር ሆን ብሎ ማክረር ጥቂቶቹ ችግሮች ሲሆኑ ከዚህ በላይ ያለውን ሌሎች ሊመሰክሩ ይችላሉ፡፡
እንግዲህ ብድር ከሌለ አዳዲስ ፕሮጀክቶች አይታቀዱም ማለት ነው፡፡ ፕሮጀክቶች ሲኖሩ ተጠቃሚ የሚሆኑት የህዝቡ ልጆች ሲሆኑ ባለመኖሩ ተጎጂ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ማለትም ጥሩ የገቢ ምንጭ በአከባቢው አይኖርም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ስራ አጥነት ይስፋፋል፡፡ ገቢ የሌለው የህዝቡን እውነተኛ ድመጽ የሚያሰማበትን ዕድል ያጣል፡፡ ባሉት ጥቂት ተቋማት ያለውን ሀብት (ሪሶርስ) ለመሻማት ዶክትሬት ያለው ሰው ሰብዕናውን ሽጦ ህዝቡንም ቸርችሮ ለመናኛ ገቢ ሲባል ራሱን ያስገምታል፡፡ የአከባቢው ፖለቲከኛም ሆነ ተቀጣሪ አክቲቪስት ካለው የብቃት ደረጃ ዛቅ ብሎ በዞን እና በዩኒቨርሲቲው በኩል እንደግሉኮስ ጠብ የምትል ጥቅም ለማግኘት የህዝቡን ክብር ያስደፍራል፡፡ ሕዝቡን ወክያለሁ የሚለው ተወካይም ቢሆን ሌሎች በህዝቡ ህልውና ላይ እንደምንጣፍ እንዲረማመዱበት ከማመቻቸትም አልፎ ይህንን የሚቃወሙ የአከባቢ ተወላጆችን ስም ያጠፋል፣ ያሳስራል፣ ያስወጋል፣ ሲያሻውምያስገድላል፡፡ ይህንንም ለመሸፋፈን ከህዝቡ ጋር ታቦት ይሸኛል ወይም ከፓስተሮች ጋር ራት ይበላል፡፡
አዳዲስ የልማት ፐሮጀክቶች የሉም ማለት ህዝቡ የፖለቲካ ጥያቄዎቹን ተፈጻሚ የሚያደርግበት አቅም የሚፈጥርበት ገቢ የለውም ማለት ሲሆን ይህ ማለት ህዝቡ ክብሩ እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጥለት አይኖረውም ማለት ነው፡፡ የመኖር ህልውናውም ዋስትና የለውም ማለት ነው፤ ልጆቹ ይገደላሉ፣ ይፈናቀላሉ የለፉበትን ጥሪታቸውን ተነጥቀው ይባረራሉ፡፡ ሴት ልጆቹ ይደፈራሉ በመንገድ ላይ ይወልዳሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሲፈጸምባቸው ሰሚ ጆሮ ያጣሉ፡፡ እንገዲህ ነገሮች እንዴት ባለ ስልታዊ መንገድ የተያያዙ እንደሆኑ ማስተዋል ይቻላል፡፡
ይህም ማለት አቅሙ የተፈጠረላቸው የህዝባችንን እጣ ፋንታ ይፈተፍቱታል ማለት ነው፡፡ አንትን ወይም አንቺን አፍኖ ስላነቺ እና ስላንተ ሌላዉ ፈላጭ ቆራጭ የሚሆነው ይህንን ከማድረጉ በፊት ከኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ብሔርህን በማግለል ነው፤ ሌላ የስላሴ ሚስጥር የለውም፡፡ ደሃ ከሆንክ/ሽ ድምጽህ/ሽ የሚደመጥበትን መድረክ ታጣለህ፣ ታጪአለሽ፡፡ የማይደመጥ ሰው ደግሞ ሲረገጥ እንኳ መረገጡ አይሰማለትም፡፡ ባንኮች ይህንን ማድረጊያ አንዱ መሳሪያ ናቸው፡፡ ስለዚህ ሱፍ የለበሰ ማኔጀር ሁሉ ባንኩ ለሚያገለግለው ለሌላው እንጂ፣ ለአንተ/ቺ የቆመ ተቋም ማኔጀሩም የዛው ገፊ ተቋም ፍላጎት አስፈጻሚ ነው፡፡ ይህ ዘረኝነት፣ ገፊነት፣ አግላይነት፣ አቆርቋዥነት፣ በዝባዥነት እና ኢምፔሪያሊሰት የበላይነት የሚተገበርበት ዘመናዊው ዘዴ ነው፡፡ አንተ/ቺ ስላላየህ/ሽ ወይም ስላልደረሰብህ/ስላልደረሰብሽ የለም ማለት አይደለም፡፡ ችግሩ እንዳለ እያወቁ ዝም ማለትም ተቋማቱ አሰራራቸውን እንዲያሻሽሉ ድምጽ አለማሰማትም ከክፋ ተግባራቸው ጋር መተባበርን ያሳያል፡፡ ይህ ደግሞ ከራስ ወገን በኩል ሲሆን በጥልቀት ያማል፡፡
ከዚህ አንጻር ወላይታ ሶዶ ዲስትሪክት ንግድ ባንክ እንዲሁም ሌሎች የግል ባንኮች ሶዶን የካሽ ማሰባሰቢያ፣ አዲስአበባን ማከማቻ እና ለሌሎች ማከፋፈያ መድረጋቸውን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ለአብነትም ያህል የዳሽን ባንክ ቅርንጫፉን ሶዶ ከተማ ሲከፍት በመጀመሪያው ዓመት አሰባስበዋለሁ ብሎ ከገመተው ከአራት እጥፍ በማይተናነስ ከስምንት መቶ ሃምሳ ሚልየን ብር በላይ ማሰባሰቡን ሰምቻለሁ፡፡ ባንኩ በአሁን ሰአት በአመት በቢልየኖች እያሰባሰበ እንደሚገኝም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ንግድ ባንክ ልማት ባንክ እንዲሁም የግል ባንኮች በአመት ከወላይታ የሚያሰባስቡት ካሽ ከሃያ አምስት ቢልየን እንደማይተናነስ አንድ ባንክ ውስጥ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለው ሰው አጫውቶኛል፡፡ ከዚህ አንጻር በአመት ወላይታ ላይ ለኢንቨስትመንት የሚውለው ፋይናንስ ከስድስት መቶ ሚልየን በላይ እንደማይበጥ ሌላኛው የባንክ አመራር ውስጥ ያለ ሰው አውግቶኛል፡፡ ይህም ከሚሰበሰበው ገንዘብ 0.5% ከአንድ በመቶ በታች ነው፡፡ ህጉ ደግሞ ከ30 እስከ 40 በመቶ መሆን አለበት ይላል፡፡ ስለዚህ ወላይታ በየዓመቱ እየተዘረፍ ይገኛል ማለት ነው፡፡ የሚዘረፈው ግን በህጋዊ ተቋማት በኩል መሆኑ የማያበሳጨው ካለ ጤነኛ አይደለም ቢባል ምንም አልተጋነነም፡፡
ጥያቄው ይህ እስከመቼ ይቀጥል? በሌላ አነጋገርም ይህ መች ይቁም? የሚለው ይሆናል፡፡ ይህ መቀጠል ከሌለበትም ምን መደረግ አለበት ባንኮቹስ የአከባቢዉን ልማት ከመደገፍ እና ህዝባዊ ባለቤትንትን ለማረጋገጥ ምን ማድረግ አለባቸው የሚለውም በባንኮቹም ሆነ በህዝቡ ውይይት እና የማስተካከያ እርምጃዎችን ሊቀይሱ ይገባል፡፡
ወላይታ ላይ ያሉት ባንኮች ለአከባቢው እድገት የሚጠቅሙ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ፋይናነስ ለማድረግ ከአከባቢው ከሚሰበሰበው ገንዘብ ከ30 በመቶ እስከ40 በመቶ በብድር መስጠት አለባቸው፡፡ ይህ እንዲሳካም ከንግዱ ማህበረሰብ ከፖለቲካ ሃይሎች እና ከወጣቱ ጋር ተቀራርበው መስራት አለባቸው፡፡
ይህ ካልሆነ ህዝቡ በባንኮቹ ላይ ምን አይነት እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርበታል የሚለውም ሳይውል ሳያድር ሊታሰብበት የሚገባ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ ህዝቡን እነደሚታለብ ላም (ካሽ ካው) ማየት የዘመናችን ድንቁርና ነው፡፡