የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም በገዛ ፍቃዳቸው ከሥልጣናቸው መልቀቃቸውን አስታወቁ።
አፈ ጉባዔዋ ሰኞ ሰኔ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. በድምጺ ወያኔ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ ‹‹አምባ ገነነናዊ መንግሥት ወደ መመሥረት ደርሰናል፤›› በማለት ምክር ቤቱ ባለው አምባ ገነናዊ አካሄድ ራሱን በራሱ እንዲያጠፋ የሚያደርግ ውሳኔ እንዲያስተላልፍ እየተደረገ ነው በማለት ስድስተኛው ምርጫ ባለመደረጉ እየተኬደበት ያለውን የሕገ መንግሥት ትርጉም ወቅሰዋል፡፡
ስለዚህም በኢ-ሕገ መንግሥታዊ አሠራር ላለመሳተፍና በሕገ መንግሥታዊ ትርጉም ውሳኔ ላለማስተላለፍ ሕሊናዬ አይፈቅድልኝም በማለት መልቀቂያ እንዳቀረቡ አስታውቀዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገብሩ ገብረ ሥላሴ ለምክር ቤቱ የደረሰ ይፋዊ የመልቀቂያ ደብዳቤ እንደሌለና መረጃውን ከሚዲያዎች እንደሰሙት ገልጸዋል።
አፈ ጉባዔዋ በሥራ ምክንያት በመቀሌ እንደሚገኙም አስታውዋል።
ወ/ሮ ኬሪያ ከኃላፊነት ለመልቀቅ መወሰናቸው የታወቀው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በኮሮና ወረርሽኝ የተነሳ የዘንድሮን ምርጫ በወቅቱ መካሄድ ባለመቻሉና የተመረጡ ምክር ቤቶች የሥልጣን ዘመን በመገባደዱ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ የመንግሥት ሥልጣን እንዴት ይቀጥል በሚለው የሕገ መንግሥቱ ዝምታ ላይ ትርጉም ለመስጠት ለረቡዕ ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ስብሰባ በጠራበት ወቅት ነው።
የአፈ ጉባዔዋ ከኃላፊነት መልቀቅ የሚወሰነው በፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው። የምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ ዋናው አፈ ጉባዔ በሌሉበት ወቅት ምክትል አፈ ጉባዔ ተክተው የመሥራት ኃላፊነት እንደሚኖራቸው ይደነግጋል።
አፈ ጉባዔዋ እንዳሉት ከሥልጣን ለመልቀቅ የወሰኑት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ሰሞኑን የሚቀርበው የሕገ መንግሥት ትርጉም አሰጣጥ አካል ላለመሆን ነው።
አፈ ጉባኤዋ አባል የሆኑበት ፓርቲ ሕወሓት ምርጫው በጥንቃቄ መካሄድ እንደሚችልና በሕገ መንግሥት ትርጉም ሥልጣን መራዘም የለበትም የሚል አቋም መያዙ ይታወቃል።
ለተፈጠረው የሕገ መንግሥት አጣብቂኝ የሕገ መንግሥት ትርጓሜን የመረጠው ገዥው ብልጽግና ፓርቲ ትርጓሜውን የሚሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሁሉንም የአገሪቱ ብሔረሰቦች በአባልነት የያዘና የሚመራውም የብልጽግና አባል ባልሆነ አመራር እንደሆነ በመጥቀስ የውሳኔ ሂደቱ ገለልተኛ እንደሚሆን በሊቀመንበሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በኩል መግለጹ ይታወሳል።
ከዚህ በተጨማሪ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ከትግራይ ክልል የቀረቡ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ አልተስተናገዱም የሚል ቅሬታ እንዳላቸውም ምንጮች ገልጸዋል። (ምንጭ፡- ሪፖርተር)