የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ /ዎብን/ ያወጣው ወቅታዊ መግለጫ
መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም
የወላይታ ሕዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄውን እጅግ በሠለጠነ ሁኔታ ሕጋዊና ሠላማዊ መንገድ ተክትሎ ሲያቀርብ የቆየ መሆኑ የአደባባይ ሐቅ ነው፡፡ የህዝቡ ጥያቄ ምላሽ እንደሚሰጠው ሕዝቡ በትዕግስት እየተጠባበቀ በነበረበት ወቅት ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም የወላይታ ዞን የቀድሞ አመራሮች፣ የሽማግሌዎች ምክር ቤት አባላት፣ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች፣ ማህበራዊ አንቂዎችና የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ስብሰባ ላይ በነበሩበት በድንገት ወታደራዊ ከበባ ተደርጎ ተይዘው መታሰራቸውን ተከትሎ አከባቢው ላይ ቀውስ ተከስቶ ቆይቷል፡፡ በአከባቢው በተፈጠረው ተቃውሞ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ባልተመጣጠነ እርምጃ በርካታ ንፁሐን ለሞትና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ከቀውሱ በኋላ በመጨረሻም ለእስራት የተዳረጉ አካላት በዋስ እንዲፈቱ በመደረጉ አከባቢው በተወሰነ ደረጃ ወደ መረጋጋት እየተመለሰ ነበር፡፡
ይሁን እንጅ የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት መስከረም 13 ቀን 2013 ዓ.ም ባስቻለው ችሎት ቀደም ሲል በወላይታ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት የተጠበቀውን የዋስትና መብት በማንሳት በዕለቱ ችሎት የቀረቡ አካላትን በቁጥጥር አውሎ በወላይታ ሶዶ ማረሚያ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ይህን ተከትሎ ወደ መረጋጋት እየተመለሰ የነበረው የአከባቢው ሁኔታ ወደ ስጋት እየተመለሰ ለመሆኑ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡
ድርጅታችን ዎብን ለተከሰተው ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀትና ሠላም ለማስፈን የሚጠቅሙ ምክር ሐሳቦችን ከማቅረቡ ባለፈ ሁኔታው እንዲሰክንና እንዲረጋጋ የሚጠቅሙ አማራጮችን ሲወስድ ቆይቷል፡፡ እንደ ዎብን ሁሉም ተዋንያን የሕዝቡን ዋናውን ጥያቄ ማዕከል ያደረገ እንቅስቀሴ ላይ እንዲያተኩረ፣ ከአፍራሽ እንቅስቃሴዎች በመታቀብ የሕዝባችን በክልል የመደራጀት ጥያቄ ምላሽ በሚያገኝበት መንገድ ላይ እንዲያተኩሩ ጥሪ ስያቀርብም ቆይቷል፡፡
ድርጅታችን ለተከሰተው ችግር ሠላማዊና ፖለቲካዊ መፍትሔዎች በማበጀት የተመሰረተው ክስ ተቋርጦ አከባቢውን ለቀውስ የዳረገና የንፁሐንን ሞት ያስከተለ እርምጃ እንዲወሰድ ያዘዘ የመንግሥት አካል ሕዝቡን በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅና ተጎጂዎችም ካሳ እንዲከፈላቸው በአጽንኦት ጠይቋል፡፡ የመንግሥት አካል በአከባቢው ዘላቂ ሠላም የማስፈን አዎንታዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ለሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ ተሰጥቶ ፣ ወደ ልማትና ወደ ተሟላ ሠላማዊ ሁኔታ ይፈጠራል የሚል ተስፋ ይዘን የቆየን ቢሆንም ባልተጠበቀ ሁኔታ የሕዝብ ጥያቄ ሲያነሱ የነበሩ አካላት ተመልሰው ወደ እሥር ቤት እንዲገቡ የተሰነው ውሣኔ ድርጅታችንን እጅግ ያሳዘነ እርምጃ ነው፡፡
በተለይ በወላይታ ባህል ጊፋታ የዘመን መለወጫ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ የታሰሩ የሚፈቱበትና ሁሉም መላው የወላይታ ሕዝብ አዲሱን ዓመት በደስታ የሚቀበልበት በወላይትኛ “Kanaw Kafuwawka gifaata” , ለእንስሳትና ለአእዋፋት የደስታ በሚሆንበት ወቅት ይህንን የህዝቡን ደስታ የሚረብሽ እርምጃ የመውሰድ ዓላማ በቅንነት ሕግ ለማስከበር ብቻ ተብሎ መሆኑን እንድንጠራጠር ግድ ብሎናል፡፡
በመሆኑም መንግስት አሁን እየተከተለ ያለው አቅጣጫና እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ለአከባቢው ሠላምና መረጋጋት አስጊ ከመሆናቸው ባሻገር በቀጠናው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማስከተል መረጋጋት የሚያሳጡ መሆናቸውን ድርጅታችን ይገነዘባል፡፡ በሂደቱም የወላይታ ሕዝብ ከልማት፣ ከኢንቨስትመንት ከሠላም ርቆ ሥራ አጥነትና ድህነት እየከፋ በመሄድ ሕዝቡን ለበለጠ ሰቆቃ የሚዳርግ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል መገንዘብ ተገቢ ይሆናል፡፡
ስለዚህም፡-
1) መንግሥት ለተፈጠረው ችግር በግልፀኝነት ከሕዝቡና ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ዘላቂ መፍትሔ ከማበጀት ውጪ ሰዎችን በማሰር የሚገኝ ምንም ዓይነት ፋይዳና ፣የሚፈታ ምንም ዓይነት ችግር አለመኖሩን፣ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች አፍራሽና ለአከባቢው ሠላም፣መረጋጋትና ልማት የማይበጁ መሆኑን ተገንዝቦ ከምንም በላይ ሕዝቡን ማዕከል በማድረግ አሁን ሕግ በማስከበር ሽፋን የሚወሰዱ እርምጃዎችን በማቆም ዘላቂ ዕልባት ሊያመጣ በሚችል ፖለቲካዊና ማህበራዊ መፍትሔ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ አዎንታዊ እርምጃዎችን በመደገፍ ሁሉም አካላት የበኩካቸውን እንዲወጡ እንጠይቃለን፡፡
2) የወላይታ ሕዝብ በከፍተኛ ትዕግስት ፍፁም ሠላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ የጠየቀው በክልል የመደራጀት ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጠው ከየትኛውም ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥቶ እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡ ስለሆነም የክልል ጥያቄ ምላሽ የመስጠት ሂደት የደረሰበት ደረጃ ለሕዝባችን በይፋ እንዲገለፅ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡
3) መላው ሕዝባችን ከየትኛውም ጊዜ በላይ ለሠላሙ ዘብ ሆኖ በመቆም በተለመደው ሁኔታ የራሱን መብት ሕጋዊና ሠላማዊ አማራጮችን ብቻ ተጠቅሞ መጠየቁን እንዲቀጥልና ለማናቸውም ዓይነት ፀብ ጫሪ ትንኮሳዎችና አጀንዳ የማስቀየር ወቅታዊ ፕሮጀክቶች ምላሽ በመንፈግ ትኩረቱን በክልል የመደራጀትና ሌሎች ሁለንተናዊ መብቶች በሚከበሩበት መንገድ ላይ እንዲያተኩር የአክብሮት ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
4) በአጠቃላይ በሀገራችን ኢትዮጵያ እያጋጠሙን ላሉ ችግሮች መፍትሔ የሚሆነው ሁሉንም ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የሰከነ ፣ግልፅነት የተሞላውና በመተማመን የተመሰረተ ውይይት አድርጎ በሀገሪቱ ዕጣ ፈንታ ላይ በጋራ የመወሰን አቅጣጫ መከተል ነው፡፡ በመሆኑም የምርጫ ዝግጅት ከመጀመሩ አስቀድሞ የፌዴራሉን መንግሥት ጨምሮ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አከላትና ሁሉም ባለድርሻዎች ግልፅነት የተሞላ የውይይትና የመግባባት መድረክ በማዘጋጀት ይፋዊ የውይይት እንዲጀመር እንዲሰሩ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ዎላይታ ብሑራዊ ንቅናቄ
መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም
ወላይታ ሶዶ