በማሰርና በመፍታት የሚቆም የነፃነት ትግል የለም!!!

wolaita today

ታህሳስ 14 2013ዓ.ም

በክብረአብ ደምሴ

ለምን በህዝቡ ላይ በደልና እንግልት ይፈጸማል? ለምንስ ይሄ ተደረገ ወይም ይደረጋል? ብለው የሚጠይቁ ዜጎች አንገታቸውን እንዲደፉ ለማድረግ ያልተገባ ስም የመስጠትና የማሸማቀቅ ስራ በብልፅግናው ቀጥሎአል፤ የወላይታ ሕዝብ ጥያቄ እንዳያነሳ የስነልቡና ጫና ለማሳደር ማሰርና መፍታትን እንዲሁም ያለወንጀል የታሰሩትን ለዋስትና ከፍተኛ ገንዘብ መጠየቅን እንደ ሌላ የትግል ማክሰሚያ ዘዴም ብልፅግናው ተያይዞታል፡፡

የብልፅጋናው ካድሬም ሆነ ተሿሚ ከጠቅላዩ እስከ ሆድ አደሮቹ የይገዙ ተስፋዬም ሆነ እንዲሪያስ ህጉንም ህገ መንግስቱንም በበቂ ሁኔታ አልተረዱትም፤ ሊማሩ እንጂ ሊያስተምሩ የሚገባቸውም አይደሉም፤ የዜጎች መብትና ነጻነት እስከምን ድረስ እንደሚሄድ በቂ ግንዛቤም የላቸውም፤ ከላይ የወረደ የሚል መመሪያ ለማስፈፀም ከመላላክ ያለፈ ሚና የላቸውም፡፡ የወላይታ ህዝብ ግብ በክልል አስተዳደር ብቻ የተገደበ አይደለም፤ የአቢሲኒያዎች “ኢትዮጵያ” የሚትባለው አገር እንደ አገር ከቀጠለች የወላይታ ብሄር ከሌሎች ብሄር ብሔረሰቦች ጋር እኩል የመወከል፣ የተጠቃሚነትና የመወሰን ጥግ ድረስ መብትን ማስከበር ነው፡፡

በአቢሲንያዋ “ኢትዮጵያ” በወላይታ ውስጥ የሚኖር የእያንዳንዱ ግለሰብ ብሶትና ምሬት በየቦታው ተጠራቅሞ ነው በድምሩ የወላይታን ህዝብ ብሶት ፣ ምሬትና ቁጣን የወለደው፡፡ ለሆድ ያደሩ፣ ከላይ የወረደ መመሪያ የሚሉትን የተስፋዬንና የእንዲሪያስን ዓይነት በድን ሰዎች ተሸክሞና አዝሎ በወላይታም ሆነ በሀገር ደረጃ ምንም አይነት ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ወላይታ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡

በተለይ ሀገርና ህዝብን ሳይሆን እራሳቸውን የሚያስቀድሙ ግለሰቦች የመጨረሻው ደረጃቸው በህዝብ ፊት መዋረድ ነው፤ እንደ … ፡፡ ተመሳሳይ ግለሰቦችን በመሾምና በመሻር፣ ከአንድ አካባቢ የተባረረን ግለሰብ ሌላ ቦታ ወስዶ በመሾም በህዝብ ላይ ዳግም እንዲፈነጭበት በማድረግ የሚመጣ፣ የሚታይ ለውጥ አይኖርም፤ ለውጥ ከራስ ይጀምራል፤ ራስ ሳይለወጥ የለውጥ መሪ መሆን አይቻልም፤ እንደ ብሔራዊ ቴየአትር አርቲስት የመድረክ ላይ ተዋናይ መሆን ግን ይቻላል፡፡

የወላይታ ህዝብ እየተራበና እየደኸዬ ባለሥልጣናትን በማጠብደል፣ ከእወቀትና ከእውነት ጋር ለተጣሉ የብልፅግና ስርዓት ተከታዮች አከባቢን ጥሎ በመሸሽና እራስን ለውርደት በማመቻቸት፣ በሌሎች ላይ የሚፈጸሙ በደሎችን እንዳላየና እንዳልሰማ ሆኖ በራስ ጉዳይ ብቻ በመጠመድ፣ ለሐይማኖተኝነት የተሳሳተ ትርጓሜ በመስጠትና የራስን ፍርሃት ለመደበቅ የአገር ጉዳይና ፖለቲካ አይመለከተኝም በሚል የኃይማኖት ተቋማትና ቅዱስ መጻህፍትን የቀበሮ ምሽግ በማድረግ በተዘዋዋሪ የጨቋኝ አገዛዝ ሥርዓት እንዲያፈረጥም ድጋፍ አይሰጥም፡፡

የወላይታ ህዝብ እንከን የሌለው መዋቅራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጥ ይፈልጋል፤ ጥገናዊ ለውጥ አይሻም፤ የከሰመውን አሃዳዊነትንም አምርሮ ይጠየፋል፤ የፋሽስቱ መኖሪያ ዓይነት ቅብ ለውጥም አያልምም፡፡

የወላይታ የክልል መዋቅር የፌዴራል መንግስትና የአስፈፃሚው አካል ችሮታ ሳይሆን መብት ነው!!!