አድሏዊ የፍትህ ገመድ ይህችን ሀገር ጠላልፎ ቢጥላት እንጂ አያሻግራትም!!!
መስከረም 13 2013ዓ.ም
“የፍትህ ስርዓቱን ጠምዝዘህ የህዝብን ህገመንግስታዊ መብትና ስልጣን በሀይል ለመደፍጠጥና የፖለቲካ ተፎካካሪዎችን ለማዳከም እንደ ፖለቲካ ጅራፍ እየተጠቀምክ ስለፍትህ: የህግ የበላይነትን ስለማስከበር: ሀገራዊ አንድነትና: ሀገርን ስለማሻገር ልታወራ አትችልም:: ሀገርን ወደ መፍረስ ጥግ እየነዳህ ‘እኔ ብቻ ትክክል ነኝ’ አይባልም: ከተሳሳትክ ተሳሳትክ ነው በቃ::” ማልኮም ኤክስ
በአንዱ አካባቢ ክቡር የሆኑትን የሰው ልጆች: በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያዊያንን በብሔር ማንነታቸው ብቻ በጠራራ ፀሀይ በድንጋይ አስቀጥቅጠው ያስገደሉ፣ ከነነፍሳቸው ቤንዚን ተርከፍክፎባቸው በክብሪት እንዲቃጠሉ ያስደረጉና ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ያስደረጉ ግለሰቦችን ከአንዱ ስልጣን ወደ ሌላኛው የተሻለ ስልጣን እየሾመ ሲሸላልም የከረመና በነፃነት ተንፈላሰው እንዲኖሩ የፈቀደ የመንግስት አስተዳደር በሌላ አካባቢ ህግና ስርዓትን አክብረው በሰለጠነ አካሄድ ለህዝባቸው ህገመንግስታዊ መብት ጥብቅና የቆሙ ምሁራንን፣ ፖለቲከኞችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችንና የማህበረሰብ አንቂዎችን ለህዝባቸው ህገመንግስታዊ መብት ዘብ ስለቆሙ ብቻ በውሸት ማስረጃ በተፈበረከ የክስ መዝገብ ፍርድ ቤት እያመላለሰ እያጉላላቸው የህግ የበላይነትን ስለማስከበርና ፍትህን ስለማስፈን ሲያወራ ስትሰማ ስለየትኛው ሀገር እንደሚያወራልህ ሁሉ ግራ ይገባሀል::
አድሏዊ የፍትህ ገመድ ይህችን ሀገር ጠላልፎ ቢጥላት እንጂ አያሻግራትም:: በብሔር ማንነት ላይ ያነጣጠሩና በፖለቲካ ፍላጎቶች የሚነዱ የክስ ሂደቶች ለፍትህ ስርአቱ አጠቃላይ ውድቀት መንስኤ መሆናቸው የማይቀር ያገጠጠ እውነታ ነው:: አሁን ስልጣን የያዘው የመንግስት አስተዳደርም በተያያዘው የፖለቲካ መስመር ከቀጠለበት ሀገሪቱ በራሷ ጎራዴ ላይ በሆዷ ወድቃ ላትመለስ ህልውናዋ የማክተሙ ነገር ሳይታለም የተፈታ የቅርብ ሩቅ አደጋ መሬት ላይ ያለ እውነታ ነው::
የሀገር ባለቤትነታችንን ገፈው ሀገር-አልባ ከሆንንማ ሰነበትን እኮ ወገን፤ እጅግ አሳፋሪ ነው በእውነቱ!!