መንግስት ከህዝቡ ጋር እልህ ውስጥ ከሚገባ ለተጠየቀው ህጋዊ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ መስጠት አለበት!!!
ከዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ም/ፕረዚዳንት
August 12, 2020
የወላይታ ብሔረሰብ የሀገሪቱን በሥራ ላይ የሚገኝ ሕገ መንግስትን ተጠቅሞ ፈራሹን ክልል በመልቀቅ የራሱን ክልል ለመመስረት በሕጋዊ መንገድ ያቀረበውን ጥያቄ ለመመለስ ፈቃደኛ ያልሆነ ክልል የወላይታ ብሔረሰብ በውስጡ የሚገኙትን ሌሎች ብሔረሰቦችን አቅፎ የመኖር የቆየ ባህልና እሴት እንተደሸረሸረ ለማስመሰል በክልሉ መንግስት እየተሠራ ይገኛል፡፡
ወላይታ ለኢትዮጵያ ሠላም ተግቶ የሚሠራ ሕዝብ ሆኖ እያለ ሌሎች ከወላይታ ውጪ የሚኖሩ ሕዝቦች የተሳሳተ መረጃ እንዲያገኙና በሕዝቡ ላይ ጥርጣሬ እንዲያሳድሩ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ስለዚህ እንደ አንድ ወላይታ ተወላጅና በዞኑ እደሚኖር ዜጋ መንግሰት በአሁኑ ሰዓት እየሰራ ያለው ስራ ስላሳሰበኝ የሚከተሉትን ነጥቦች መንግስት እንዲያጤን እጠይቃለሁ፡፡
- የክልልሉ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ በቀን 03/12/2012 ዓ.ም በደቡብ ቴሌቪዥን ባቀረቡት መግለጫ የወላይታ ዞን አመራሮች፣የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን እና ሌሎች የሕብተሰብ ክፍሎች በቁጥር 26 የሚሆኑት በወላይታና አካባቢው ላይ ሽብር ለመፍጠር ከኦነግ ሸኔና ሕዋሐት ጋር ሲያሰሩ ይዤ አስርያቸዋለሁ ብሎ ተናግሯል፡፡ ይህ ደግሞ ከእውነት የራቀ ሴራ ፖለቲካ መሆኑን በውስጡ ስለምኖር መመስከር የምችለው ጉዳይ ነው፡፡
መንግስት በሠጠው የቤት ስራ መሠረት ከሐይማኖት አባቶች ተወካዮች፤ ከነጋዴው ማህበረሰብ ተወካዮች፤ ከምሁራን ተወካዮች፣ ከየላጋ ተወካዮች፤ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት ተወካዮችና ከሴቶች ተወካዮች ጋር መክረው ሠላማዊ የክልል ጥያቄን በሠላማዊ መንገድ ለማስኬድ ሲወያዩ የነበሩ መሆኑና ላረጋግጥ እወዳለሁ፡፡ የታሰሩ ሰዎች ስብጥር እነዚህን ሁሉ ያካተተ መሆኑ ሰላማዊ መሆኑን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፤ ምንም እንኳ ስብሰባው ከሕዋሐት ጋር ባይሆንም ይሁን ቢባል እንኳ ሕዋሐት የብልጽግና ፓርቲ ተቃዋሚ አንጂ ሽብርተኛ ነው ተብሎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አልተፈረጀም፤ተፈርጆ አልሰማንምም፡፡ ብልጽግና ሕዋሐትን እንደተቃዋሚ ሊጠላው/ ሊፈረጀው ይችላል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ለድርጅቱ ለብልጽግና ፓርቲ እንጂ በሕግ ሽብረተኛ ሊያስብል የሚችል የሕግ ማዕቀፍ የለውም፡፡ ይህ የሚያሳየው ብልጽግና ፓርቲ የፈረጀው/ ወሰነው ሁሉ በሕግ የታሠረ ነው ብሎ የሚያምን ሕግን የማያውቅ አመራር ክልሉን እየመራ መሆኑ ነው፤ - ይህ የቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ ለኢሳት ቴሌቪዥን በቀን 05/12/2012 ዓ.ም በሠጠው ቃል የሞቱት ሕጻናት(9-12 ዓመት 3 ሕጻናት) እና ወጣቶች ከወላይታ ውጪ የሆኑ ብሔረሰብ ተወላጆች ንብረት ላይ አደጋ ሊያደርሱ ሲሉ በመከላከያ ሠትዊት ተተኩሰው ሞተዋል ብለዋል፡፡ ይህ ሰው ሌሎች ብሔሮች ወላይታን በጥርጣሬ እንዲያዩና ጥላቻ እንዲያዳብሩ እያደረገ ስለሆነ መንግስት ሴራውን እንዲያቆመውና መረጃው የተሳሰተ መሆኑን ገልጾ ሕዝቡን ይቅርታ መጠየቅ አለበት፤
- የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳውም በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመስርቶ የሠጠው መግለጫ የወላይታን ሕዝብ እያስቆጣ ያለ መሆኑ ታውቆ የወላይታንና ያሳሳተውን የኢትዮጵን ሕዝብ ይቅርታ እንዲጠይቅ አመለክታለሁ፤
- አሁን ስራ ላይ ያለው ሕግ ተጥሶ ሕዝቡ የሚያምናቸውን አመራሮች በኃይልና በወታደር ገርስሶ ሕዝቡ የማይፈልጋቸውን ከዚህ በፊት መብቴን አላስከበረልኝም፣ ልማት አላመጣልኝም ብሎ በሕዝብ ግምገማ በዘመነ ደኢሕዴን ጡረታ የወጡ አመራሮችን በኃይል ለመሾም የሚደረገው ጥረት ዋጋ ሊያስከፍል ስለሚችል እውነትም የለውጥ መንግስት ከሆነ የሕዝቡ ይሁንታ ያላቸውን መሪዎች ማቆየት ወይም ሕዝብ በሚፈልጋቸው መተካት፤ ይህ ባልሆነበት መንግስት ራሱ ችግር እንዲፈጠር የሚፈልግ መሆኑን ሕዝብ እንዲያውቅ እንፈልጋለን፤
- የኢትዮጵያ እናቶችና አባቶች በሌላቸው አቅም ከመቀነታቸው በሚያዋጡት መዋጮና ግብር የሀገርን ዳር ድንበር ከጠላት እንዲከላከልና ሕገ መንግስትን እንዲጠብቅ የተዋቀረው የሀገር መከላከያ በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ጭፍጨፋ በአስቸኳይ እንዲያቆምና ከሠላማዊ የወላይታ ምድር እዲወጣ እጠይቃለሁ፡፡
- በክልሉና በፌደራል መንግስት ትዕዛዝ ለሞቱት ሕጻናትና ወጣቶች ቤተሰብ መንግስት ተገቢውን ካሳ በአስቸኳይ እንዲከፍል እጠይቃለሁ፡፡
ከላይ የዘረዘርኳቸውን የፌደራልም ሆነ የክልሉ መንግስት በአስቸኳይ አጥነው ምላሽ መስጠት አለባቸው፡፡
ለሟቾች ቤተሰብና ለመላው የወላይታ ሕዝብ እግዚአብሔር መጽናናትን እንዲሰጥ እመኛለሁ!!!
ዶ/ር ወንድሙ ወልዴ
ነሐሴ 05 ቀን 2012 ዓ.ም
ወላይታ ሶዶ ኢትዮጵያ