ከሰሜን ኦሞ ሰልስት ከደኢህዴን ቀብር እስከ ደቡብ ክልል ግነዛ በዚህች አጭር ዕድሜ ስንቱን አየን?
በአንዱዓለም ታ. ቦልጠና
ዘላለማዊ ክብር እና ሞገስ እንደ ሃገር ለኢትዮጵያችን ለወላይታም ለታገሉ ትውልዶች ለዎጋጎዳ ሰማእታት እና ወላጅ አባቴን ጨምሮ በህይወት ላሉ ጀግና ታጋዮች!
ሰላም ሰብአዊነት ስራ እና ስልጡንነት ወዳዱ የዎላይታ ህዝብ ደኢህዴንን በጀርባዉ ተሸክሞ ደቡብን አዝሎ በመገፋቱ ተመሳሳይ ግፍ በሰሜን ኦሞ መዋቅር ሲደርስበት የደረጋትን አሁን ደገማት፡፡ ደኢህዴንን ቀበረ፡፡ ደቡብንም አፈረሰ፡፡ ሰሜን ኦሞን አፈረሰ አሁን ደግሞ ደቡብ ክልልን ላይመለስ አፍርሶታል፡፡ ከእንግዲህ ኢትዮጵያን የሚመራ ማንም ይህንን አይረሳዉም፡፡ ደቡብ አንድ ላይ እንዲሆን በደም እና በአጥንት ዋጋ ስንከፍል ሃገራችን ኢትዮጵያ የተረጋጋች እና የበለጸገች ሃዋሳም የፍቅር እና የመቻቻል ተምሳሌታችን እንድትሆን ነበር፡፡ የዛሬይቷ ኢትዮጵያ ይህንን አልፈለገችም፡፡ በአፏ ማር እያፈስስች በእጆቿ ቢላዋ ትስላለች፡፡
እናም ይህንን (ሃገራችን ኢትዮጵያ የተረጋጋች እና የበለጸገች የፍቅር እና የመቻቻል ተምሳሌታችን ከተማችንም እንድትሆን) የምናደርገው ዎላይታ ሶዶን ነው፡፡ ሰላም ሰብአዊነት ስራ እና ስልጡንነት መናገሻዉ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ (ያዉም እዛ ካለ) ሶዶ ላይ ይሆናል፡፡ ማንም ብሄር የትም ይወለድ ምንም አይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ ኖረው (አሃዳዊም ቢሆን) ምንም አይነት ሃይማኖት ይከተል ዎላይታ ቤቱ ነው፡፡ ዎላይታነት Primordial በትውልድ (genetic) ዉርስ የሚገኝ ሳይሆን በምርጫ እና በፍላጎት የሚኮን ነው፡፡ ዎላይታ የራሱ ሪፐብሊክ ቢሆን ሁለት እና ከዚያ በላይ ዜግነት ይፈቅዳል፡፡ ይህ ማለት አንድ ሰው ትግሬ-ዎላይታ አማራ-ዎላይታ ኦሮሞ-ዎላይታ ሲዳማ-ዎላይታ መሆን ይችላል፡፡ በነገራችን ላይ አሁን የጠቀስኳቸው ሁሉ የህዝቡ ጎሳዎች ዉስጥ አሉ፡፡
ለምሳሌም፡ አማራ-ላይታ፣ ቄስጋ እና አማራ (ይህ በአጼ ምንሊክ ጊዜ የፈለሱትን አይጨምርም) ፣ሲዳማ-ዎላይታ፣ አይፋርሶ፣ ትግሬ-ዎላይታ፣ ትግሬ ማላ ፣እና ሌሎችም፤ ሳሳጥረው ማንም ሰው ዎላይታ ሲመጣ አይሸማቀቅም፡፡ ሲዳማዉ ሲዳማ ዎላይታዎች አሉት፡፡ ኦሮሞው ኦሮሞ ዎላይታዎች አሉት፡፡ አማራዉ አማራ ዎላይታዎች አሉት፡፡ ልክ እነደዚሁ ሃድያው ከምባታው ሃላባዉ ጎፋው ጋሞው ዶርዜው ቁጫው ቦሮዳው ዳዉሮው ባስኬቶው እና ሌሎችም የዚህ ጸጋ ባለቤቶች ናቸው፡፡ ይህ በተለያዩ የታሪክ የሶሲዮሎጂ የአንትሮፖሎጂ የታሪክ እና የባህል እዲሁም የሙዚቃ ጥናቶች ላይ የሰፈረ እውነት እና ሃቅ ነው፡፡ እናም እኛ ሌላ ከተማ ላይ ልናደርግ ሞክረን በራሳቸው የተከለከልነውን ድንቅ ሃገር የመገንባት ሃሳብ ዎላይታ ሶዶ ላይ እናደርገዋለን፡፡ ሶዶ ማንም ሰው በየትኛውም የሃገሪቷ ክፍል ችግር ቢፈጠር (አያምጣው እና) ሊሸሸግ የሚመጣባት የመማጸኛ ከተማ እናደርጋታለን፡፡ ከአክሱም ዘመነ መንግስት በፊትም እናደርገው እንደነበረው ዎላይታ የሁሉም ምርቻ እናደርጋለን፤ደግሞም ናትም፡፡
እኛ ሁሉንም ሁሉም እኛን ናቸው፡፡ ይህ ኢትዮጵያ ውሰጥ ወላይታ ብቻ ያላት እውነተኛ ኢትዮጵያዊነት መሆኑን ማስታወስ የፈለግ የአለም ሎሬት ጸጋዬን ጽሁፍ ማስታወስ በቂው ነው፡፡ ወላይታነት እውነተኛ ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ በሎሬት ጸጋዬ ስሌት ዎላይታነት = +/እውነተኛ ኢትዮጵያዊነት/፣ I meant absolute value፤ እናም ኢትዮጵያን የምትወዱ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ወላይታ ወዳድ ናችሁ፡፡ በዚህ ደስ ይበላችሁ፡፡ ወላይታ የሁሉም እናት የሁሉም ቤት!
ተመስገን ፈጣሪ ከሰሜን ኦሞ ሰልስት ከደኢህዴን ቀብር እስከ ደቡብ ክልል ግነዛ በዚህች አጭር ዕድሜ ስንቱን ላሳየሄን!