“አንድ በኤርትራ የትጥቅ ትግል ወቅት ትልቅ ስፍራ የነበረው ግለሰብ ወንድሜ ኮ/ል በዛብህ በህይወት እንዳለ እና በአይኑ እንዳየው ከአራት ወይም አምስት አመት በፊት ገደማ ነግሮኛል። በማይታወቁ ሰዎች ከሚፃፍ ፅሁፍ ይልቅ የአይን እማኝ ባምን እመርጣለሁ”— ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ
“ገፁ ከኤርትራ መንግስት ጋር የተያያዘ ስላልሆነ ሌሎች በፃፉት ዙርያ አስተያየት ለመስጠት እቸገራለሁ”— አንድ ከፍተኛ የኤርትራ ባለስልጣን
“Eritrean Press” የተባለ የፌስቡክ ገፅ ትናንት ይዞት የወጣ አንድ ፅሁፍ ላይ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መጀመርያ አካባቢ ተዋጊ ጀት ሲያበሩ ጀታቸው ተመትቶ የጦር ምርኮኛ ሆነው የነበሩት ኮ/ል በዛብህ ጴጥሮስ ከአመታት በፊት ህይወታቸው እንዳለፈ ፅፎ ነበር።
ይህንን ተከትሎ የኮ/ል በዛብህ ወንድም የሆኑትን ፕ/ር በየነ ጴጥሮስን ለቤተሰብ የደረሰ መረጃ ይኖር ይሆን ብዬ ማምሻውን አናግሬያቸው ነበር።
ፕ/ር በየነ በጉዳዩ ዙርያ በተደጋጋሚ ከኤርትራ የሚወጡ የሀሰት መረጃዎች እንዳሉ ጠቁመው “ይህ የተለመደ ነው። በየስድስት ወሩ ግዜ እየጠበቁ ስለ ወንድሜ ኮ/ል በዛብህ ጴጥሮስ የሚነዙት ወሬ ቤተሰብን ከማሸበር ያለፈ ጥቅም የለውም” ብለዋል።
አክለውም “ይህ አሁን ተፃፈ የተባለው የአይን እማኞች ከነገሩኝ የተለየ ነው። እንደውም አንድ በሀገሪቱ የትጥቅ ትግል ወቅት ትልቅ ስፍራ የነበረው ግለሰብ ወንድሜ ኮ/ል በዛብህ በህይወት እንዳለ እና በአይኑ እንዳየው ከአራት ወይም አምስት አመት በፊት ገደማ ነግሮኛል። በማይታወቁ ሰዎች ከሚፃፍ ፅሁፍ ይልቅ የአይን እማኝ ባምን እመርጣለሁ” ብለዋል።
ለፕ/ር በየነ ጉዳዩ በመንግስት ደረጃ በቅርቡ ተነስቶ ይሆን ብዬ ላቀረብኩላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “በመሪ ደረጃ መነሳቱን እንጃ፣ ታች ባሉ ባለስልጣናት በኩል ግን ተነስቶ ነበር። የሰማሁት በጉዳዩ ላይ መነጋገር እንደማይፈልጉ ነው። ጠበቅ ተደርገው ሲጠየቁ የኮ/ል በዛብህ ጉዳይ የባለስልጣናት ጉዳይ ሳይሆን የኤርትራ ህዝብ ጉዳይ ነው እንደሚሉ ሰምቻለሁ” ብለዋል።
“ይህ በየጊዜው የሚመጣ ወሬ ሰላም እየነሳን ነው፣ ቤተሰብም እያሸበረ ነው” ብለዋል ፕ/ር በየነ።
በጉዳዩ ዙርያ አንድ ከፍተኛ የኤርትራ ባለስልጣንን መረጃ ጠይቄ “ያልከውን ፅሁፍ አላየሁትም። ቢሆንም ገፁ ከኤርትራ መንግስት ጋር የተያያዘ ስላልሆነ ሌሎች በፃፉት ዙርያ አስተያየት ለመስጠት እቸገራለሁ” ብለው መልስ ሰጥተውኛል።
ይህ ፅሁፍ Ethiopia Check ላይ ካቀረብኩት የተወሰደ ነው። ይህን ገፅ ለማግኘት እነዚህን ሊንኮች ይከተሉ:
(ምንጭ፡- ጋዜጠኛ ኤልያስ መሰረት)