የነፍጠኛ አስተሳሰብ አራማጅና ተጠቂ መቼም የነፃነት ትግል አጋር መሆን አይችልም!!!

July 30, 2020

የወላይታ ህዝብ በውሸት ተስፋ ዳግም እንዳይገዛ የአጼዎቹና የደርግ ጨቋኝ አስተዳደር ከሚገባው በላይ አስተምሮታል፤ በተለይ ደግሞ የደርግ መንግስት መውደቅ ተከትሎ ስልጣን የጨበጠው የኢህአዴግ እና የወራሹ ብልፅግና ድርጅታዊ አሰራራቸውንና የፖለቲካ ቁማራቸዉን ህዝቡ አዉቆባቸዋል፤ ከእንግዲህ ወዲያ በወላይታ የብልፅግና ፓርቲ ብልጣብልጥነት አያዋጣም፡

የጡረተኛ ደኢህዴን አባላትና ግልገል ካድሬዎች የሥልጣን አምሮትና ለስልጣን እየታገሉ ፣ የወላይታን ህዝብ ሲያምሱና ሲያተራምሱ፣ አሮጌ ችግሮችን በአዲስ ችግሮች ከመተካት ባለፈ የመፍትሄ አካል አለመሆናቸው የወላይታ ህዝብ የሥልጣን ባለቤትነቱን ተረክቦ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበትና ከማዕከላዊ መንግስት ጋር በክልል የፖለቲካ አስተዳደር ተዋቅሮ፣ ፍትሀዊ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ስልጣን ባለቤት የመሆን ትግሉ አማራጭ ሳይሆን ብቸኛ ምርጫ ከሆነ ከመቶ ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ወላይታን ከደሀነትና ከተመጽዋችነት የሚያወጣው ይሄው ብቻ ነው፤ ምክንያቱም ወላይታ የበይ ተመልካች መሆኑ የሰውነት ክብሩንና የሰውነት ዋጋዉን አሳጥቶናል፡፡

የብልጽግና ሰዎችና አጫፋሪዎች እንዲሁም የነፍጠኛ አስተሳሰብ አራማጅና ተጠቂዎች ይወቁትም፣ ይግባቸውም፣ አይግባቸው ከወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዉጪ ሌላ ምርጫ ለድርድር አይቀርብም፤ በወላይታ የብልጽግና ሰዎችና አጫፋሪዎች ወገኑን አዋርዶ እውነተኛና ታሪካዊ ክብርን የሚጎናፀፍ ማንም አልነበረም፣ አይኖርምም፤ እንዲሁም ደግሞ የነፍጠኛ አስተሳሰብ አራማጅና ተጠቂዎች በጥላቻ ላይ የህብረት ኢትዮጵያ አይመሰረትም፡፡

የወላይታ ህዝብ ለሐቅ እና ለነፃነቱ ከመታገል ውጪ ከየትኛውም ህዝብ ጋር ጠብ የለውም። ጠቡ ከጨፍላቂዎች እና ከአጼያዊ አስተሳሰብ ልክፍት ተጠቂዎች ጋር ነው፡፡ ማንም ራሱን ከአጼያዊ አስተሳሰብ ልክፍት ጋር ካቆራኘና ያንኑ ካቀነቀነ ልክፍቱ ወደ ጋንግሪን አድጎበታል፤ የዛ ልክፍት አስተሳሰብ አራማጅ መዳኛው አስተሳሰቡን መታከም አልያም በአስተሳሰብ ልክፍቱ ሞቱን ማፍጠን ነው፡፡

አጼያዊ ኢትዮጵያ በማንነቱ የሚያሸማቅቅ ለወደደው ለማንም ላቦራቶሪ ተሞክሮ ይታይ እንጂ በወላይታ እንዲሞከርና ማንነታችን እንዲሟሸሽ እውቅና አንሰጠውም። የወላይታ ህዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄና መልሱ የህዝብን ስነ ልቦና እና ነባራዊ እውነታውን ብቻ የያዘ ነው፤ ከአቢሲኒያ ገዥ ምኒልክ ጋር በተደረገው የሰባት ዓመት ጦርነት ስድስቱን በድል የተወጣው ወላይታ በውስጥ ባንዳዎች ሴራ መሸነፉን የአቢሲኒያ የግዛት መስፋፋት ታሪክ የማያውቅ የሰባት ዓመት የዉጊያ የታሪክ ዘገባን ማገላበጥ ዕውቀትም ትምህርትም ይሆናል፡፡ በርግጥ የኢትዮጵያ ታሪክ የተጻፈው በገዥዎች ስለሆነ ገዥዎች ሥልጣንን ተቆጣጥረው እዉነታን በመበረዝ ታሪክን በሚፈልጉት አቅጣጫ በማፃፍ ብርቱ ጥረት አድርገዋል፤ ዬለጋ (ወጣቱ) ከጊዜ በኋላ ራሱ ነፃ ሆኖ የወላይታን ታሪክ መርምሮና ተመራምሮ እውነታውን ይደርስበታል፤ አጼዎቹና ተላላኪዎቻቸው ቀድሞው ባሰራጩት መርዘኛ የውሸት ታሪክ እንደ ታዴዎስ ታንቱ የተደናገሩ የዕድሜ አቻዎቻቸው አሉ፡፡

የወላይታ ህዝብ ከአጼዎቹ ቀጥታ ትዕዛዝ ተቀብለው በሚያስተዳድሩ ተላላኪዎች የኢኮኖሚና የፖለቲካ ውድቀት ተዳርጓል፤ ከዚህ የውድቀት አዙሪት ለመውጣት ብቸኛው መንገድ ራስን በራስ ማስተዳደር ብቻ ነው፤ ሌላ አማራጭ መፍትሄ የለም፤ የወላይታ ህዝብ ለራሱ የሚመቸውን የፖለቲካ አስተዳደር የሚወስነው ራሱ ነው፤ የፖለቲካ ቁማርን መሰረት ያደረገና ማንነትን በማጥፋት በአቅጣጫና በወንዝ ስም የማደራጀት የአፈና አካሄድ ዳግም በምንም መልኩ በወላይታ አይሞከርም። ሁሉም በልክ ሲሆን ያምራል። ራስን መወደድ ሌላውን በመጉዳትና በማጥቃት ራስን ለማኖር ሌላውን የማሳደድና የማጥፋት ተግባራት ኢሞራላዊና ሰይጣናዊነት ነው። በኢትዮጵያ የክልል መበራከት ማለት ዕኩልነትና ፍትሀዊነት ነው። ዕኩልነት የማይመቸው ለአሃዳዊያን ነው። በአቅጣጫና በወንዝ ስም ማደራጀት የሚለውን ፌዝ ተውትና እየተቸገራችሁም የወላይታን ክልልነት ተቀበሉት፤ በዚህም አያበቃም የከንባታ፣ የጉራጌ ፣ ከፋ፣ ቤንች ማጂ እና ሌሎችም ክልሎች ይፈጠራሉ፤ አሃዳዊያን እንደ ኮሶ ቢመራችሁም ዋጡት፤ ነገሩን በሂደት በደንብ ትለምዱታላችሁ፡፡

የነፍጠኛ አስተሳሰብ አራማጅና ተጠቂዎች እንዲሁም የብል(ጽ)ግና ሰዎችና አጫፋሪዎች ስህተታችሁ በወላይታ ላይ ያለውን እውነታ አለማወቃችሁ እና ለማወቅም አለመፈለጋችሁ ነው፤ ስለዚህ ታረሙ።

ወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት!!!