በምስኪን ህዝብ የሚነግድ ቁማርተኛ በዛ!

Wolaita Today

በረድኤት ታምሬ (ዶ/ር)

July 28, 2020

“የህዝባችን ክብር እና ላእላይነት መገለጫ የሆኑትን ምኒሊክን ስም የሚያጠለሹ አካላት ያለርህራሄ እንዲከስሙ ይደረጋል” – የብልጽግና የእቅድ ትግበራ ቼክሊስት

  1. “ላእላይነት” ማለት የበላይነት ማለት ነው። ላእላይ ምስቅልና “superiority complex” ማለት ነው። የጎርፍ ውሀ በሚጠጣባት እና ህዝብ ሜዳ ላይ በሚጸዳዳባት ቅጽል ስሟ “ጉስቁልና” በሆነች በአፍሪካ ደረጃ እንኩዋን የወደቀች በምትባል ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ አይነት የናዚ የአርያን ምርጥ ዘር ነን አይነት ፖለቲካ እንዴት ሊነሳ ቻለ? ይሄ ንግግር በደርግ ግዜ የሚታሰብ አልነበረም። በኢሀዴግ ቁጥር አንድ ግዜም እንደዚሁ። አንድ ሰሞን “የሰውነት ውሀ ልክ ነን” የሚሉ ብሄረተኞች ሲነሱ ከእረኝነት ወደ ፖለቲከኝነት ፍሬቻ ሳያበሩ እጥፍ በማለት የሚፈጠር ያለመብሰል ችግር ነው ብለን አልፈነው ነበር። እረኞቹ የህዝባቸውን ቁመና እንደማይመጥኑ ማንም ያውቅ ነበር።

አሁን ግን ምራቅ ከዋጡት ፖለቲከኞችም እንዲህ አይነት ነገር ሲደገም ምን ይባላል? አላማቸው ሀገር ማፍረስ ነው? መቼም በዚ ዘመን ላእላነትን/ታእታይነትን የሚቀበል ይኖራል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው! እንኩዋን ዛሬ ትላንትም የተቀበለው የለም! ሌላው ቀርቶ ህዋን (space) አስሰናል፣ አተም ሰንጥቀናል የሚሉ በሚጨበጡ መለኪያዎች የላቀ የስልጣኔ ደረጃ ላይ ከሚገኝ ማህበረሰብ የወጡ ሰዎች/ቡድኖች “ላእላይነታችንን እናረጋግጣለን” ቢሉ የሚሰማቸው የለም! በቃሬዛ ተጭኖ ረጅም ኪሎሜትሮችን አቋርጦ ወደ ህክምና የሚሄድ ህዝብ፣ በወጉ በልቶ የማያድር፣ ንጹህ የመጠጥ ውሀ የሌለው ህዝብ ጉስቁልናውን እና የኑሮ ቀምበሩን የሚያቀልለትን የልማት ስራ እንጂ የተጠማው የሙታንን ሌጋሲ ማስቀጠል ተቀዳሚ አጀንዳው ሊሆን አይችልም።

  1. “ያለምንም ርህራሄ እናከስማለን” የሚለውስ? ፍጹም የፋሺዝም መገለጫ አይደለምን? ማስተዋል ሆይ ከወዴት አለሽ?!?

ተኩላ ፖለቲከኞች በምስኪን ህዝብ ስም አትነግዱ!!!