የዘምቢሉ ህልውና – የኢትዮጵያ “የግዛት አንድነት”
የኢትዮጵያ “የግዛት አንድነት” ዕውን ሊሆን የሚችለው “የሕዝቦቿ አንድነት” ከተጠበቀ ብቻ ነው፡፡ የሕዝቦቿ አንድነት ደግሞ የሚገኘው በመካከላቸው በሁሉም ዘርፍ ፍጹም እኩልነት ሲኖር ነው። ይህ “እኩልነት” በተግባር ሲመነዘር ደግሞ እያንዳንዱ ብሄር ብሄረሰብ ለፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ ባሕልና ቋንቋው ዕድገት የሚያመቸውን አስተዳደር ያለምንም የውጪ ተጽዕኖ መተግበር ሲችል ነው፤ ሌላ ምንም የሚያወያይ ወይም የሚያከራክር አሻሚ ትርጉም የለውም።
“በኢትዮጵያ አንድነት” ስም የኢትዮጵያ ህዝቦች በአንድ ቅርጫት ውስጥ ታጉረው “አንድ ናችሁ” ተብለው “በአንድ ግዛት” ውስጥ ኖሩ እንጂ “አንድ ህዝብ” አልነበሩም።
የተፈጥሮ ሂደቱን ተከትለው ወደ አንድነት እንዳያመሩ እንኳ የአፄዎቹና የደርግ ሥርዓት የመከፋፈል እንጂ የማዋሃድ ባህርይ ስላልነበረው የታሰበው ህልማዊው “የህዝቦች አንድነት” ሊፈጠር አልቻለም።
ከጆርጅ ኦርዌልን ልዋስና በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት ልሞክር። የነበረው ሥርዓት – ሙዝ ትርንጎ ሎሚ ብርቱካን ፓፓያ ማንጎ መንደሪን አናናስ እና ለሎች ፍራፍሬዎችን በአንድ ዘምቢል ውስጥ አስቀመጣቸውና “ሁላችሁም ፍራፍሬዎች ስለሆናችሁ አንድ ዘር ናችሁ፤ ከናንተ መሃል ግን ብርቱካን ከሁላችሁም የተሻለ ጣዕም ስላለው ሁላችሁም የብርቱካን ጣዕም የተሻለ መሆኑን ተቀብላችሁ ብርቱካን ብርቱካን መሽተት አለባችሁ፤ ግን ደግሞ ፍራፍሬዎች ስለሆናችሁ በዚህ በጋራ ቅርጫታችሁ ውስጥ በአንድነት በሰላም ኑሩ” ተብሎ ተወሰነባቸው። ከጊዜ ብዛት እንድያውም አንዳንድ ፍራፍሬዎች በተለያየ ምክንያት የራሳቸውን ተፈጥሮአዊ ጣዕም መለወጥ እንደማይችሉ እያወቁ “ብርቱካን ብርቱካን” እንሸታለን ማለት ጀመሩ። አንዳንዶች ደግሞ በግድ “የብርቱካን ጣዕም ነው” ያላችሁ ተብለው እንዲያምኑ ተገደዱ። የማታ ማታ ግን ሁሉም በሩን ዘግቶ የየራሱን ዕውነተኛ ሽታና ጣዕም ሲያጣጥም ኖረ። አንድ ቀን “እኔም እንደ አንድ ፍራፍሬ ተፈጥሮ ያደለኝ የራሴ የሆነ ጣዕምና ጠረን እንዳለኝ ታውቆልኝ ከብርቱካን እኩል ተከብሬ የምኖርበት ጊዜ ይመጣል” ብለው መኖር ቀጠሉ። ታሪክም የራሱን ጊዜ ጠብቆ በራሱ ቀን ዘንቢሉን ዘርግፎ ካሁን በኋላ በግድ “ብርቱካን ብርቱካን” መሽተት የለባችሁም እያንዳንዳችሁ የየራሳችሁን ቃና ይዛችሁ በእኩልነት በዘንቢሉ ውስጥ ከፈለጋችሁ በፈቃደኝነት መኖር ትችላላችሁ ብሎ ፍርድ ሰጠ።
የሚያሳዝነው ግን ጥቂቶች ዛሬም “በርግጥ ሁላችሁም የየራሳችሁ ጣዕምና ቃና አላችሁ፤ ሆኖም ግን እያዳንዳችሁ የየራሳችሁን ቃና መሽተት ከጀመራችሁ ዘምቢሉ መፈራረሱ ነውና ለዘምቢሉ ህልውና ሲባል ሁላችሁም “ብርቱካን ብርቱካን” እንደሸተታችሁ ቀጥሉ” ይሉናል።
ራሳቸውን የአንድነትና የ”ኢትዮጵያ” ጠበቃ አድርገው የሚቆጥሩት ለዚህም ምክር መሰል ትዕዛዛቸው የሚሰጡት በሳይንስ ወይም በሃቅ ላይ የተመሰረተ ሃሳብ ሳይሆን እንዲሁ በደፈናው “ለኢትዮጵያም የሚበጃትንም ሆነ ለእናንተ ህልውና እኛ እናውቅላችኋለን” የሚለውን የተለመደ አደዳቢ ስብከት ተመርኩዘው ነው።
ከሰማንያ የሚበልጡ የተለያየ ቋንቋና ባህል የያዘውን ህዝብ አፍኖ ለኢትዮጵያ አንድነት ሲባል ሁላችሁም አንድ ባህልና ቋንቋ እንደራሳችሁ አርጋችሁ ኑሩ የሚለውን የጅል አባባል ከአንድ ከመቶ ዓመት በላይ ተሞክሮ ያንገፈገፈና የተቀበረ ስርዓት ስለሆነ በጭራሽ ወደዚያ አንመለስም!!!
ድል ለወላይታ!!!