ጊዜያዊ ጸጥታ ዘላቂ ሰላም አይሆንም!!!
ተመስገን ማርቆስ ኪንዶ (ዶ/ር)
ሲብላላ ቆይቶ ሰሞኑን የድምጻዊ ሃጫሉን መገደል ተከስቶ የፈነዳው የሊህቃን አለመግባባት እጅግ ወደኋላ እንዳይጎትተን ያስፈራል፡፡ መንግስት በግድያው እጃቸው አለበት ያላቸውን የተወሰኑ ሰዎች አስሮ ወደፍርድ ቤት ማመላለስ ጀምሯል፡፡ ይህ ጊዜያዊ ጸጥታ ሊሰጠን ቢችልም ዘላቂ ሰላም ግን አያመጣም፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ስልጣን ከመያዛቸው በፊት ተቃዋሚዎች የቀድሞውን ኢህአዴግ ሲጠይቁ የነበረ አንድ ዋነኛ ነገር አለ፡ ብሄራዊ እርቅ፡፡ ያኔ በዚህ ጥያቄ ታላግጥ የነበረችው ህወሃት ራስዋ አሁን ይህን መጠየቅ ጀምራለች፡፡
የሃገራችን ፖለቲካ የመልአክና የጭራቅ ፖለቲካ ነው፡፡ ሚኒሊክ መልአክ የሆኑለት ወገንና ሚኒሊክ ጭራቅ የሆኑበት ወገን ንትርክ፡፡ መለስ ዜናዊ ከሰማይ ነው የወረዱት ወይስ ከሲኦል ነው የመጡት የሚል ጭቅጭቅ፡፡ ሚኒልክም፣ ሃይለስላሴም፣ መንግስቱ ሃይለማሪያምም፣ ጃዋር መሃመድም፣ ሌሎቹም መሪዎችና ፓለቲከኞች ስዩመ እግዚአብሄርም አይደሉም፣ ሰይጣንም አይደሉም፤ ሰዎች ናቸው፡፡ መልካም ስራም ስህተትም የሚሰሩ፡፡
ከታሪካችን ጥሩውንም መጥፎውንም በሰከነ ሁኔታ ተነጋግረን ስህተቱን አርመን ትምህርት የሚሆነውን ይዘን መሄድ ነው ብሄራዊ እርቅ፡፡ ከኛ በፊት የነበሩት ሰዎች በመሰላቸው መንገድ እንጂ በአምላክ ትእዛዝ አይደለምና የሰሩት የተሰጠንን እንዳለ ይዘን የመቀጠል ግዴታ የለብንም፤ በሰይጣን ምሪትም አይደለም ሲንቀሳቀሱ የነበሩትና የነበረውን አውድመን ከዜሮ ካልጀመርን ማለትም የጤና አይደለም፡፡
ጥግ የያዙ ያልታረቁ የታሪክ፣ የማንነት፣ የሃብት ክፍፍል ወዘተ ጥያቄዎችን ወደመሃል ማምጣት ነው ብሄራዊ እርቅ፡፡ መቶ በመቶ መስማማት ባይታሰብም የተቻለውን ያህል ተቀራርበን የማንስማማባቸውን ነገሮች በምርጫ ካርድ ለመለየት መስማማት ነው ብሄራዊ እርቅ፡፡ በምርጫ የተሸነፈው ያልተስማማባቸው ሃሳቦች ለጥቂት አመት በአብላጫ ድምጽ ገዢ መሆናቸውን ተቀብሎ በቀጣይ ምርጫ የራሱን ሃሳብ ገዢ የሚያረግበት እድል መኖሩን ተማምኖ በሰላም መኖሩ፤ የተለየ ሃሳብ ያለውን ሰው “የኢትዮጲያ ጠላት” ወይም “የብሄሮች ጨቋኝ” ሳይሆን ልክ እንደኛው መልካም መድረሻ ፈልጎ ለጋራ ጉዟችን ግን አማራጭ መንገድ የሚፈልግ ብለን መውሰዳችን፡፡
የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት ምርጫ ከመድረሱ በፊት ሰፊ ህዝባዊ ውይይቶችን በማድረግ፣ በማስተማር ወዘተ ወደመግባባት ያመጣናል የሚል ተስፋ የነበረን ተስፋችን ጨልሞ ሳንግባባ ምርጫው ሲደርስ ሊመጣ የሚችለውን እልቂት እየፈራን ሳለ ሌላ እልቂት ምርጫውን አራዘመው፡፡ የቤት ስራውን ሳይሰራ የነጋበት ተማሪ አስተማሪው ታመው ቢያድሩ ጥቂት ፋታ ያገኝ ይሆናል፡፡ የአብይ አህመድ መንግስት አስተማሪው እስኪያገግሙ “ኮሚሽን ተቋቁሟል” እያለ ማልመጥ ይቀጥላል ወይስ የምርጫውን መራዘም እንደ እድል ወስዶ ምርጫው እንደገና ከመምጣቱ በፊት የቤት ስራውን ይሰራል?
የባለፈው ሁለት አመት የቤት ስራችንን ሳንሰራ “ጉርሻ ጥያቄዎች” እየሰራን ነበር፡፡ የሚያጨቃጭቁ ዋና ዋና አጀንዳዎችን የተወሰኑ ሰዎች እንዲደበሩበት ኮሚሽኖች ሰርተን ተጨማሪ ጭቅጭቅ የሚፈጥሩ የትምህርት ፖሊሲ መቀየር፣ የንግድ ፖሊሲ መቀየር ወዘተ ላይ ተገባ፡፡ እነዚህ ሁለት አመት መቆየት አይችሉም ነበር?
የኢህአዴግ መንግስት አማራጭ ድምጾችን ሲያፍን ቆየ፡፡ የብልጽግና መንግስት ደግሞ በየፊናችን እንድንለፍፍ ተወን፡፡ ሁለቱም ወደመነጋገርና መግባባት አላመጡንም፡፡ አሁን ብልጽግና ኢህአዴግነቱ ተነስቶበት አደገኛ ናቸው ያላቸውን ድምጾች ቢያፍን ለጊዜው እንረጋጋ ይሆናል እንጂ ነገ ሰላም አይሆንም፡፡ ወንጀለኞች መጠየቅ አለባችው፤ ነገር ግን የሃጫሉ ግድያ ተራ ወንጀል አይደለም፡፡ ከጀርባው መለዘብ ያለባቸው ተቃርኖዎች አሉበት፡፡ እዛ ላይ ካልሰራን በሽታውን ትተን ምልክቶቹን በማከም አባዜያችን እንቀጥላለን፡፡
ሳሩዋ ኤሆ!