የካድሬዎቹ ኳራንቲ…

Wolaita Today

በክብረአብ ጌታቸው

ይቺ “ለምን አሁን?” የሚሏት ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ ያለፈውንና ሊመጣ የሚችለዉን የፖለቲካ ሸፍጥ ይዛ ትመጣ ይሆን ወይ የሚል የማሰላሰያ ወቅታዊና ተገቢ ጥያቄ ናት፡፡ ሰውየው ያጨበጭባል፤ አብሮት የነበረ ጓደኛውን “ለምንድነው የምታጨበጭበው?” ብሎ ቢጠይቀው “ሌሎች ስለሚያጨበጭቡ ነው” ብሎ መለሰለት፤ ነገሩ “መሀይምነት ይውደም” ብለው ሳይገባቸው ግራ እጅ እንዳወጡት ነው፤ ሰውን መማሩ ካለማወቅ ነፃ ያወጣል እንጂ መፈክር ከሽለላ የዘለለ ፋይዳ የመውም፡፡

ሰሞነኛው የወላይታ ደኢህዴን/ብልፅግና ፓርቲ አባላት ተወካዮች (የወላይታ ህዝብ ተወካዮች አላልኩም) የደቡብ ክልል ምክር ቤት ከፈረሰ በኋላ በትዕዛዝ ይሁን ለፖለቲካ ብልጣብልጥነት በኮሮና እንደተጠረጠረ/እንደታመመ ግለሰብ ካድሬዎቹ ኳራንቲ አድርገዋል፡፡ በዓለም ላይ የብዙዎችን ህይወት ከቀሰፈው በሽታ የተነሳ ኳራንቲ የተደረገ ግለሰብ ከዳነ ወደ ቀድሞው ኑሮው ይመለሳል ካልሆነ ነፍስና ስጋ ይለያያሉ፡፡

የካድሬዎቹ ኳራንቲ የህዝቡ ብሶትና ጥያቄ ገብቷቸው ነው ወይ?

በወላይታ ውስጥ የደኢህዴን/ብልፅግና ካድሬዎች እስከ ማዕከላዊው መንግስት ድረስ ያሉትን ጨምሮ ውስጣቸው በትዕቢት አብጧል፤ ይህ ህዝብ “ምንም አያመጣም” የሚል የተሳሳተ ስሌት ውስጥ ገብተው በሰዎች ደም ባህር ውስጥ ይዋኛሉ። የካድሬዎቹ የሰንበት ጸሎትና የዓርብ ዷዋ የታይታ ነው፤ ከወላይታ ለጋ ታዳጊዎች የወላጆቻቸውን ፍቅር ሳይጠግቡ በጠራራ ፀሐይ መንገድ ላይ ሎተሪ አዝዋሪ፣ ሊስትሮ ጠራጊ ፣ ደሞዝ የሚከለከሉና በአሰሪዎቻቸው የሚደፈሩ የቤት ሰራተኛ ሆነው ሲሰደዱ የካድሬ ልጆች በግል ትምህርት ቤት ምሳ ተቋጥሮላቸው ይቀማጠላሉ፤ ካድሬው በደሃው ህዝብ ስም የተበጀተውን ረብጣ ገንዘብ ወደ ኪሱ ይከታል፤ የካድሬ ተለጣፊ የሆኑ ነጋዴዎችና የበጎ አድራጊ ድርጅቶች ኃላፊዎች ሲተርፋቸው ጥቢኛ ኑሮ ላጎሳቆለው ይወረውራሉ፤ ይህ ትዉልድ ነገሩ ገብቶታል፣ ነገርግን የደኢህዴን/ብልፅግና ካድሬዎች አሁንም በመንታ መንገድ ላይ ሆነው ያንገራግራሉ፤ ይህ ትውልድ ካድሬ ባለስልጣናት እያደረሱ ያለውን በደል በልቦናው መዝግቦ ይዟል። ጥያቄው የወላይታ የክልልነት ጥያቄ ብቻ አይደለም፤ ያለፈ ነው፤ ሁሉም እንደየስራው ሂሳብ የሚያወራርድበት፤ መልካም የሰራ የሚመሰገንበት ሌላውም እንደሰራው የሚመዘንበት ነው፤ በመንግስት ካዝና ስፖንሰርነት በተቀነባበረው በሌዊው የ”ጊፋታ አዋርድ” የሚሞኝ ቂል የለም፤ ሰውዬውም ሳይገባው አጨብጭቧል፡፡

የካድሬው ኳራንቲ ዉሻ ወደ ትፋቱ እንደሆነስ?

የኮሮና በሽታ ታማሚ ከህመሙ ሲያገግም ወደ ቀድሞው ኑሮው ይመለሳል፤ የካድሬዉ ኳራንቲ ከማን ነው? የደቡብ ክልል ምክር ቤት ፈርሷል፤ የኢህአደግ/ብልፅግና መንግስት ከህዝብ ጋር ያለው የአምስት ዓመት የአስተዳደር ኮንትራት ውል መስከረም 30 ያበቃል፤የብልፅግና ፓርቲ የስልጣን ዕድሜ ማራዘሚያ የህገ መንግስት ትርጓሜ ተቀባይነቱ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ባለበት የካድሬው ኳራንቲ ምን የሚሉት ነው? የኳራንቲ ሳምንታት ሲያጠናቅቁ ልክ እንደ ዉሻ ካድሬው ወደ ትፋቱ እንደሆነስ?

በተለይ በወላይታ ያለውን ፓለቲካ በሚዛናዊ አዕምሮ መፈተሽ፣ ያለ ስሜታዊነት ማስተዋል፣ በመመረቅ ፈንታ ውሸትና እውነቱን በተለያየ ዘዴ አበጥሮ ለመለየት አንጀትና ዓይን እንዲኖረን ያለንበት ሁኔታ ያስገድደናል፡፡ የካድሬዎች ክፋትና በጎነት በወሬ ሳይሆን አሳማኝ መረጃ ባለው ሥራቸው መመዘን አለበት፡፡ ዬለጋ ይህንን ማድረግ በጀመረ ጊዜ የጭፍን ወሬዎችና ሐሳቦች መጫወቻ ከመሆን ይድናል፤ ራሱ ዳነ ማለት ደግሞ ትዉልዱ ዳነ ማለት ነው፡፡ አለበለዚያ ነገሩ “መሀይምነት ይውደም” ብለው መማር ካለማወቅ ነፃ ማውጣቱን ዘንግተው ግራ እጅ እንዳወጡት ነው የሚሆነው፡፡

እውን ካድሬው ድሮዬን አልደግምም…. ባይበላ ይቅር ይላል ወይ?

መንግስቱ ንዋይ የሞት ፍርድ ከተወሰነባቸው በኋላ “…ይግባኝ ብዬ ጉዳየን የሚመለከትልኝ የኢትዮጵያ ህዝብ ቢሆን ኖሮ ይግባኝ ማለት በፈለግሁ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ እንደማይሆን አውቃለውና፤ በይግባኝ የአፄ ኃ/ስላሴን ፊት ማየት አልፈቅድም፤” ብሎ አልፏል፤ ከደቡብ ክልል ም/ቤት ራሳቸውን ኳራንቲ ያደረጉ ካድሬዎች እንዲህ ዓይነት ዉሳኔ ለማድረግ የመንፈስ ልዕልናና ሞራል አላቸው ወይ? ምክንያቱም እስከ ዛሬ ታማኝነታቸው አባሎቻቸው ለወከሏቸው ደኢህዴን/ብልፅግና መሆኑ የዉሾን ነገር ያነሳ…. እንዳይሆን ስጋት አለ፡፡

ወዳጆቼ ለህሊና መኖር ችሎ የህዝብ ልጅ ከመሆንና ጠላትን ከማሳፈር ወዲያስ ምን ጀግንነት አለ?

ወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት!!!