የወላይታው የፖለቲካ ቁማር – የብልግ(ፅ)ናው አክሮባት
በክብረአብ ጌታቸው
ከእውነት ሸሽቶ እንደፈለጉት የፖለቲካ አክሮባት መስራት የማታ ማታ እናንተን (ፖለቲከኞችን) ለትዝብት ሕዝቡን ለጉዳት ጥሏል። ባለፉት 27 ዓመታት አገር ተረካቢ፣ የተማረና ያልተማረ ፣ ሴትና ወንድ ፣ ታዳጊ ትዉልድን ለስደትና ሰቆቃ በስልጣን ማማ ላይ ለመንጠልጠል ያዉም ጭንጋፍ ለሆነ ስልጣን ሲባል ህዝብን ለአሰቃቂ ግፍና መከራ የዳረገውን፣ የማይሞላውን ከርስ ለመሙላት አቋርጠው የሚወጡትን ያልበሰለ የወላይታ የደኢህዴንን ፖለቲከኞች አካሄድ “ፖለቲካ ነው” ብሎ ለማለፍ መሞከር፤ ራስን ማሞኘት ነው፣ ሲቀጥል ኢ-ሰብዓዊነት ነው፤ ከዚህም ሲያልፍ ድንቁርና ነው፤ ይሄ ፖለቲካ አይደለም። ይሄ በሰዎች ህይወትና ነፍስ የሚጫወቱት ቁማር ነው። “የትኛው ፖለቲካ ትክክል ወይንም ስህተት ነው?” ለማለት በቅድሚያ በወላይታ እንዲህያለ የሙታን ፖለቲካ መቆም እንዳለበት ማመን አለብን።
ቀድሞውንስ የወላይታ ህዝብ ተወካዮች ነበሩት?
እዚህ ላይ የኔም ሆነ የሁላችን ጥያቄ “በእርግጥ ትክክለኛ የወላይታ ህዝብ ተወካይ አለን?” ወይ የሚለው ነው። የለም! ግን የወላይታ ህዝብ ተወካዮች ሳይሆኑ የደኢህዴን/ብልፅግና ፓርቲ አባላት ተወካዮች ነበሩ የሚል እምነት አለኝ።
የወላይታ ህዝብ እስከዛሬ ባለዉ የኢትዮጵያ ታሪኩ ተግዟል፤ ተረግጧል፤ ተንቋል፤ ተንቋሿል።የባለፉት 27 ዓመታት እየደረሰ ያለዉ አከባቢያዊ ሳይሆን ብሄራዊ ዉርደትና ንቀት ግን ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ልዩ ከልዩም ልዩ ነው፤ ታዲያ ቀድሞውንስ የወላይታ ህዝብ ተወካዮች ነበራችሁን? ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ወላይታ ዉስጥ ያለዉና የነበረው የደኢህዴን/ብልፅግና አገዛዝ ዕቅዱና ስራዉ ሁሉ የወላይታን ህዝብ ማስጨነቅና ማበሳጨት ነዉ እንጂ ህዝብ በሚሰራዉ ስራ ተደስቶ አያዉቅምና፡፡ የእስካሁኑ ተሞክሮዓችን እንደሚያሳየው የወላይታው ደኢህዴን/ብልፅግና ውጥረት ሲበዛበትና መዉጪያና መግቢያዉ ሲጠፋዉ ከደቡብ ምክር ቤት ለቀናል የሚል ለውጥረት ማስተንፈሻ ጊዜ የሚገዛ መሆኑን ነው። ከምክር ቤት መልቀቅ ብቻ ሳይሆን በወላይታ የአደራ መንግሰት እንዲቋቋም ከዞን እስከ ቀበሌ ድረስ ካለው መዋቅር ጭምር መልቀቅ የግድ ነው::
እዚህ ላይ ሰኔ 2010ዓ.ም የተፈፀመውን አሳዛኝ ድርጊት ማስታወሱ ስለ ህዝብ ውክልና የበለጠ ለመረዳት ይረዳል የሚል እምነት አለኝ፤ የዕርቅ ሿሿንም ትዝብት ማከል ተገቢ ነው፡፡
ጥቁር ሰኔ
ከሰኔ 8 – 10 2010ዓ.ም ባሉት ቀናት በአዋሳ በወላይታ ብሔር ተወላጆች ላይ የሰብዓዊነትና የዜግነት ክብር ያዋረደ ግፍ የሲዳማ የክልል ጥያቄን አስታኮ በደኢህዴን ዉስጥ ያሉ የወላይታና የሲዳማ ፖለቲከኖች የስልጣን ፍቲጊያ የተነሳ በህዝብ ላይ በደል ተፈፅሞአል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁለቱንም ብሔር ተወላጆች ወክለው በደኢህዴን ፖለቲካ የፊት መስመር ላይ የነበሩ ከተጠያቁነት እንደማያመልጡ መታወቅ አለበት፤ ጥሉ የህዝብ አልነበረምና፤ አንድ ሕዝብ ከሌላ ሕዝብ ጋር ተጋጭቶ አያውቅም፤ አይጋጭምም፡፡ በዚህ የፖለቲካ ልሂቃንና አመራሮች ሴራና የብልጣብልጥነት ቁማር በበዛበት ወቅትም ቢሆን እንኳን የወላይታና የሲዳማ ሕዝብ አልተጣሉም፤ አይጣሉም፡፡
ተጎታች ሽማግሌዎች
ሰኔ 2010ዓ.ም በአዋሳ ከተማ የተፈፀመውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ተከትሎ ህዝቡ ተጣልቷል፣ ዕርቅ እንፈፅም ያሉ በሁለቱም በኩል ያሉ ሽማግለዎችም ሽምግልናን ዋጋ አሳጥተዋል፤ የሲዳማ ሽማግሌችዎች በፖለቲከኞቹ የተሰጣቸውን script (የድራማ ድርሰት) በሚገባ ተውነዋል/ተጫውተዋል፤ ተሳክቶላቸዋልም፡፡ በወቅቱ ወላይታን ወክለናል ያሉ ሽማግሌዎች በደኢህዴን የተመረጡ የጥቅምና ቤተሰብአዊ ዝምድና ትስስር እንደነበራቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፤ የዚህ ትችት ዓላማ ሽምግልናን ዋጋ ለማሳጣት ሳይሆን በ1992ዓ.ም ወጋጎዳን በመቃወም በሽምግልና ከተሳተፉት አሁንም በዕድሜ የጎለመሱ ሰዎች ትምህርት እንዲወስዱ ለመጠቆም ነው::
ሽምግልና ወደተጠሩበት ሁሉ መሄድ አይደለም፡፡ ወደ ፊት ከታሪክ ተጠያቂነት ለማምለጥ ወደሌላኛው የህይወት ኡደት ከመሻገራቸው አስቀድመው በተሳሳተው ጎዳና ላይ መጓዛቸውን አምነው ተጎታች ሽማግሌዎቹ በስህተታቸው ብፀፀቱ የወደቀውን የሽምግልና ዋጋ ለማዳን ዕድሉ በእጃቸው ነው፤ በማህበረሰቡም ውስጥ ቀና ብለዉ ያለመሸማቅ የመሄድ እድላቸው የሰፋ ነው፡፡ በርግጥ ይህን ለማድረግ የሞራል ልዕልና ይጠይቃል፡፡
የእምነት ተቋማት ተወካዮች
በተለይ እጅግ የሚያሳዝነው በወላይታ የነበሩና አሁንም ያሉ የተለያዩ የእምነት ተቋማት ተወካዮች ዉክልና በወቅቱ ግርታን መፍጠሩ ዛሬም ሊታለፍ የሚገባ ጉዳይ አይደለም፤ ምክንያቱም የኃይማኖት ተቋማት ለግለሰብና ለማህበረሰብ ያላቸውን አስተምህሮት እውነትን ፣ ፍትህን ፣ ሀቅና መልካም ምሳሌነትን የሚያስተምሩና የሚሰብኩ በመሆናቸው ነው፡፡ በጊዜው በዕርቅ ሿሿ ተሳታፊ ስለነበሩት ግለሰቦቹ ተሳትፎ የተጠየቁት የእምነት ተቋማቱ የበላይ አስተዳዳሪዎችና ሽማግለዎች ስለጉዳዩ የሚያውቁት ጉዳይ እንደሌላቸውና በዕርቅ ሿሿ የነበሩት የእምነት ተቋማቱን እንደማይወክሉ፣ እንደ ግለሰብ መታየት እንዳለባቸው አረጋግጠዋል፤ ለዚህም በድምፅ የተደገፈ ማስረጃዎች ነበሩ፤ አሁንም አሉ፡፡ “የሚያስታርቁ ብፁዓን ናቸው” “ይቅር ተባባሉ” “ቂም ለማንም አይጠቅምም”…ወዘተ አስተምህሮት በእምነት ተቋማት የእሁድና ዓርብ ስብከትና ትምህርት ሲደጋገም ለዘመናት እንደነበርና ወደፊትም የሚቀጥል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በአፄዎቹና በኢህአደግ አገዛዝ ያሉ የእምነት ተቋማት ከሚመጣው ሁሉ ጋር መነጎድ ለኛ የእምነት ተቋማት አባልና ተከታዮች ድርጊቱ ሊሰጠን የሚችለውን ትርጓሜ ትምህርትና መልዕክት ማጤን የአስተማሪዎቹና የሰባኪዎቹ ሃለፊነት ነው፤ በርግጥ ነባራዊው እውነታ ግራ ያጋባው አጥማቂው ዮሐንስ “የሚትመጣው አንተ ነህ ወይስ ሌላ” ብሎ ጠይቋል፤ እኛስ ታዲያ ዛሬ ማንን እንስማ?
የደኢህዴን/ብልፅግና ፖለቲከኞችና ተባባሪዎቹ ተጠያቂነት
የደኢህዴን/ብልፅግና አመራሮች አባላትና ቀለብተኛ ተላላኪዎች በሠሩት ሥራ ልክ በግል እና በጋራ ህዝባዊ የመንግስት አስተዳደር ሲቋቋም ተጠያቂነት አለባቸው፤ የሕሊና ሳይሆን የህግ ተጠያቂነት፡፡