ሕግን ለአንዱ ዜጋ ሥራ ላይ አውሎ ሌላው ሲመጣ መደበቅ አይቻልም!!! የጠየቅነው የዎክመ ብቻ ነው!!!

Wolaita Today

 

በአምሳሉ መሠኔ (ቃቆ)

በተለያዪ ጊዜያቶች የወላይታ ሕዝብ የነበረበትን የአስተዳደራዊ መዋቅር ችግር ለመፍታት ትግል አድርጓል፡፡በ1992 ዓ/ም በተደረገው የዎጋጎዳ ትግል ውስጥ የሀገር ሽማግሌዎች ተሰደው አዲስ አበባ በነበሩበት ወቅት እኔም የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ እዛው ስለነበርኩ ለጠ/ሚ መለስና ለሌሎች የፌዴራሉ አስተዳደር አካላት የሚያቀርቡትን አቤቱታ ሲያዘጋጁ የተወሰኑ አባቶች ጥያቄው ወላይታ ዞን ይሁን የሚል አይሁን ክልል እንጠይቅ ሲሉ ሌሎች በሳል አባቶች በአንድ ጊዜ ሁለት ደረጃ ከፍ ለማለት መጠየቁ ከባድ ነው፤ የዞኑን ካሳካን ከተወሰነ ዓመት በኃላ ክልል እንጠይቃለን ብለው ሀሳብ ሲለዋወጡ ሰምቻለሁ ፡፡

ይህ የትግል ሂደት ጊዜውን ጠብቆ ቀጠለና የወላይታ ብሔር የክልልነት ጥያቄ ከቀበሌ ጀምሮ መክሮበትና ተነጋግሮ በዞን ም/ቤት ወስኖ፣ ዓለምን ያስደመመ ፍጹም ሠላማዊ ሰልፍ አድርጎ፣ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል ም/ቤት በሕገወጥ መንገድ አንድ ዓመት ሙሉ በማቆየቱ በይግባኝ ፌዴሬሽን ም/ቤት ወስዶ ትግሉን ጫፍ አድርሶ ውሳኔ እየተጠባበቀ ነው፡፡

በዚህ መሐል ደኢህዴን #በጥናት የተረጋገጠ ነው 1ለ55 አደረጃጀት ይቀጥል; በማለት ያቀረበውን ሀሳብ ሁሉም ሲደግፉ ወላይታ ብቻውን ተከራክሮ መጨረሻ ላይ ክቡር ጠ/ሚ ወላይታ ብቻውን ያራመደውን ሀሳብ ተቀብሎ “55ቱም አንድ ሆነው ይቀጥሉ ማለቱ ድርቅና ነው፤ ለጠየቀው ሁሉም ደግሞ ክልል አንሰጥም” በማለት ክልሉ ስንት ቦታ መከፈል አለበት? ለሚለው በተለያዩ መንገዶች እና ዘዴዎች እየተሞከረ ይገኛል፡፡

ከዚህ መረዳት የሚቻለው ሁለት መሠረታዊ አካሄዶችን መንግሥት እየተጠቀመ መሆኑን ነው፡፡

1/ በማያሻማ መልኩ በሕግ አግባብ የቀረበውን የዎክመ ጥያቄ ጉዳይ ሆን ተብሎ ታፍኖ እንጂ በሕገ መንግስቱ መሠረት መፈፀሙ የማይቀር ነው፡፡ ሕግን ለአንዱ ዜጋ ሥራ ላይ አውሎ ሌላው ሲመጣ መደበቅ አይቻልም፡፡

በዙሪያዋ ያሉ ሁሉ የሚፈሯት ወላይታ ምን ትሁን (ከኮንታ ውጭ) ?? እንደ እስራኤል ተከባ ትኖራለችና ከዎብክመ ጋር ልቀቋት፡፡

ወላይታ ከ50 ነገሥታት በላይ ተፈራርቀው የነገሱባት፣ በራሷ የመገበያያ ገንዘብ #ማርጯዋ; የነገደች፣ ብቻዋን ሀገር የነበረች ምንም አትሆንም፤ ለሥራ በሚታትሩ ልጆቿ፣ ድንበር የለሽ ባለ ምጡቅ አዕምሮ ትውልዷ፣ ወደ ገናናነቷ በእርግጥ ትመለሳለች፤ በኢትዮጵያ ሀገራችንም ጉልህ አሻራ ማሳረፏን ትቀጥላለች፡፡

ወላይታ ብቻዋን በ1955 ዓ/ም በዎላይታ ሕዝብ ብር ኡማ ወንዝ ላይ የብረት ድልድይ ጥላ አሻግራ፤ 1992 ዓ/ም ለራሷ ሞታ፣ ተርባ፣ ተሰዳ ፣ብዙ መከራ አይታ፣ ያለ ድካም ስንት ነገር ተጠቅመውም ዛሬ አብረሽ አልኖርም እያሉ ናቸው ፤ በእርግጥ መብታቸው ነው፤ ሠላሙን ሁሉ፡፡ ለማንኛውም ወላይታ ብቻዋን የበለጠ ታድጋለች፤ ትበለጽጋለች፡፡ ለሚጠራጠሩ ዶ/ር ደጃዝማች ወ/ሰማዕት እና ፈረንሳዊው ቫንደርሃይም የፃፉቸውን መጽሐፎች ትጋብዛለች፡፡

2/ ደቡብ ክልል ፈርሶ በማናቸውም መስፈርት ከሚፈጠሩ አዳዲስ ክልሎች ውስጥ አንዱ ወላይታ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን እውነታ ጠ/ሚሩ በመጀመሪያ ውይይት ቀን አረጋግጠዋል፡፡ ነገር ግን አሁን በሚቀርበው ኦሞቲክ በተባለው ክልል ውስጥ ወላይታ ባለበት የትም አንደራጅም ያሉትን መልሶ መላልሶ ማናገር ማወያየት ምን ይጠቅማል? ጉዳዩ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ውሳኔ የሚፈልግ ይመስላል፡፡ #ከእነ እንትና ጋር ኑሩ;  የሚለው መንግሥት #ከእነ እንትና ጋር; ተወያይቶ ከወላይታ ጋር በአንድ ክልል ተደራጁ ብሎ ያሳምናቸው ይወስን እንጂ ወላይታን በምን ጉዳይ ምን ሊያወያይ ይፈልጋል? ዎክመ ሰጥቶን መገላገል እያለ?

በሙሉ ፈቃዳችን (Full& free consent) የጠየቅነው የዎክመ ብቻ ነው፡፡