ከ125 ዓመታት እሥራት ለመፈታት ዋዜማው ላይ ነን?
በአምሳሉ መሠኔ (ቃቆ)
ዛሬ 01/10/2012 ዓ/ም ሰኔ እና ሰኞ ተገናኙ አልተገናኙ የሚለው ብዙም አላስጨነቀኝም፤ ሁሉም ቀናት የፈጣሪ ሥራ ናቸውና ለእኔ ተመሳሳይ ናቸው፡፡
የዛሬ 125 ዓመት 1887 ዓ/ም ዎላይታ ወደ ኢትዮጵያ አንድነት ከመጣችበት ጊዜ ጀምሮ በኢ-ፍትሐዊ የአስተዳደር መዋቅር ሥር ሆና ሲዳሞ ክ/ሀገር፣ ሰሜን ኦሞ፣ ደቡብ በሚባሉ አንድ ጊዜ ዳሞታ አውራጃ ሌላ ጊዜ ያሻቸውን ቅጽል ስም እየሰጡና እየለጠፉ አዙሪት ተጫውተውብን በኢትዮጵያ ካርታ ስማችን እንዳይጠራ አጥፍተው ቆይተዋል፡፡
ለነገሩ 7 ዓመት ሙሉ አድዋ ላይ ጣሊያንን ያሸነፈውን የአፄ ምንሊክ ጦር ተዋግተው መጨረሻ ላይ በአጼው መሪነት ዎላይታ ድረስ ዘምተው እዚሁ በተደረገ ደም አፍሳሹ ጦርነት ተሸንፎ የተያዘን አካል በመሰል አስተዳደራዊ የመዋቅር እሥር ቤት ካላሰሩ በምን ያኖሩታል፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ክቡር ዶ/ር ደጃዝማች ወ/ሰማዕት ወደ ዎላይታ አውራጃ አስተዳደሪ /ገዥ/ ሆነው ሲሾሙ በ1955 ዓ/ም አፄ ኃ/ሥላሴ ከተናገሯቸው ነገሮች አንዱ ” የዎላይታ ሕዝብ ኃይለኛ በመሆኑ በአስተዳደር ደረጃ ከጠቅላይ ግዛት ጋር በእኩል ስለሚታይ ዘመናዊ የትምህርት ዕውቀት የቀሰሙ ሙሁራንን ነው እየመደብን የቆየነው፤ አሁን ደግሞ አንተንም የሾምንህ፤ ገርማሜ ነዋይንም የላክነው ለዛ ነበር፡፡ በተጨማሪም ሕዝቡ የመጨረሻው ንጉሥ ካዎ ጦና ከተያዙ በኃላ ደስተኞች አይደሉምና በፍቅር አስተባብረህ ጥሩ ሥራ ሥራ ብለን ከሙሉ ነፃነት ጋር ሾምንህ” የሚል ነበር፡፡ አቤቱ አምላኬ ሆይ እንኳን ክ/ሀገር ልዩ አውራጃ ብለውን ጃንሆይ በሞከሩ ዛሬ የኢትዮጵያ ሁለተኛ ከተማ ነበረች፤ ይቅር ብቻ፡፡
ይህ የዘመናት በደል በጀግናው የዎላይታ ብሔር ከባድ ትግል በ1992 ዓ/ም ለመጀመሪያ ጊዜ ዎላይታ በዞን ደረጃ ተዋቅሮ በስሙ የተጠራበት ጊዜ ሆኗል፡፡ በአስተዳደራዊ መዋቅር ምን ያህል እንደተጎዳን ከ1992 ዓ/ም ጀምሮ ዎላይታ ላይ ያሉ ሁሉ አቀፍ ለውጦችን ማየቱ ከበቂ በላይ ይመስለኛል፡፡
የደርግ ሥርዓት የሰራቸው ጥሩ ጥሩ ከሀገር ፍቅር ጋር የሚገናኙ ጉዳዮች ቢኖሩም እንደ ዋዱ (WADU) ዓይነት እጅግ የላቀ ውጤት ማምጣት የሚችሉ ነገሮችን ያሳጣን “በአንድ አውራጃ የዚህን ያህል Investment” አይቻልም በሚል አስተሳሰብ ነበር፡፡ ወይ መንጌ ግን ዎላይታ የክ/ሀገሩን የወታደር ኮታ ብቻውን ማለት በሚያስችል ደረጃ ሞልቶ በሌላ ክ/ሀገርና አውራጃ ኮታ ገብቶ ለኢትዮጵያ ሀገሩ ፈንጂ ላይ የሚንከባለሉ ጀግኖች የዎላይታ ልጆች መሆናቸውን ያውቅ ይሁን? በአውራጃ ደረጃ የዚህን ያህል ልማት አያስፈልግም አለ እንጂ ለወታደር ከአንድ አውራጃ የዚህን ያህል ወታደር በዝቷልና ተመለሱ አላለም ብዬ ነው፡፡
The last and also the least የሆነው የዛሬው ፈራሽ የደቡብ ክልል ልጅ ባላፈራንበት በጠለፋ ጋብቻው ያደረሰብን በደል ተቆጥሮ አያልቅም፡፡ የሚገርመው ከምስረታው ጀምሮ የዚህን ክልል አወቃቀርና አስተዳደር በበላይነት ከመሩ ባለሥልጣናት ውስጥ የዎላይታ ልጆች ቁጥር ከየትኛውም ብሄር የበለጠ ሆኖ እናገኛለን፡፡ የማይገባንን ጠይቀን አናውቅም ጠይቀን የተከለከልነውም ነገር የለም ግን በእነዚህ ልጆቻችን የሚገባንን ብዙ ነገሮች በይሉኝታና ፍራቻ ያጣንበት ወቅት ነበር፡፡ በወደቀ እንጨት የሚል ተረት ይሆናል ብዬ እንጂ ከፖለቲካው የአስተዳደር በደሎች ውጭ ለመጥቀስ ያህል በተለይ በተለይ በ1989 ዓ/ም የኢትዮጵያ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ አሸናፊ በመሆን በ1990 ዓ/ም ሀገሩን ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ ኮ/ካፕ ውድድር የተሳተፈውና በአንዴ ተራራ የሆነባቸው ዎላይታ ቱሣ በወራት ውስጥ ሲፈርስ የክልል የዞን ተብየው ኦሞ ዞን አስተዳደር በዝምታ አይተው ማለፋቸው በአልጋ ወራሹ ድቻ ተተክቶ እስካየንበት ጊዜ ድረስ የጨለማ ዘመን ነበረን፣ አሜሪካን ሀገር አንድ ጥቁር ሰው ተገደለ ተብሎ ያለውን ጩሄት ከእኛው በደል ጋር ስናነጻጽረው የእኛ ነፍስ አይመስልም፡፡ በቁም ሰድበውን በድለውን አባረውን ሁሉን ችለን አንድ ህፃን ልጅ ለ30 ለ40 ተራ በተራ በዱላ አናቱን ቀጥቅጠውት አልሞት ሲል በሕይወት ያለን የእግዚአብሔርን ነፍስ የሟች ወላጆች እርማቸውን አልቅሰው እንዳያወጡ ቤኒዚን አርከፍክፎ አቃጠሉት ገደሉት ብላቴ ማሰልጠኛ ያለ ጦር እያለ አፍንጫው ሥር ያለ የቶጋ ካምፕ አጋአዚ ጦር እያለ ደቡቦች አልተከላከሉንም፤ አጥፊዎችን በአግባቡ ለሕግ እንኳን አላቀረቡም (የአምላኬ ፍርድ በአድራጊዎች ላይ ይረፍ)፡፡
ስለዚህ የዎላይታ ብሔር ከዚህ የዘመናት የአስተዳደር መዋቅር ጭቆና ይላቀቅ፤ ክቡር ዶ/ር አብይ ይፍቱን፡፡ ያለን መሬት ጠባብ የሚመስላቸው የብላቴን፣ የኦሞን፣ የሐመሣ፣ የዎይቦ፣ ማንኢሣ፣ ጫራቄ፣ ሶኬና አጃንቾ፣ የበዴሣ፣ የቁሊያ፣ የአረካ፣ ደሜና ሣዋሬ ወዘተ እንዲሁም የአባያና ኡማ (ጊቤ 3) ሰው ሰራሽ ሐይቆች በዘመናዊ የግብርና ሥራ ከተመሩ እንኳን ለዎላይታ ለሌላው ይተርፋሉ፡፡ ዋናው ግብርናውን በማዘመኑ ላይ መሥራት ነው፡፡ ደግሞም ሀገር ሳይሆን ክልል ነው የጠየቅነው፡፡ ከታች ፎቶ ላይ የምትመለከቱትን የአባላ አባያ ወረዳ የአባያ ሐይቅ ማልማት ከቻልን ብቻ በቂ ነው፡፡
ለመኖሪያ ቦታ ከጠበበን እንደ ቻይና 90ና 100 ፎቅ ወደ ሰማይ እንገነባለን አየር ላይ የድንበር ክርክር የለም፤ ሁከት ፈጠረብኝ የለውም፡፡ ግልግል፡፡ አንድ ከተማ ውስጥ 50 ሚሊዮን ሕዝብ ዓለም ላይ ይኖራል፡፡
ሳጠቃልል ዎላይታ ዳግም ወደ አስተዳደራዊ መዋቅር እሥር ቤት አይገባም፡፡ በዎላይታ ክልል ውስጥ አብረው አንድ ላይ እደራጃለሁ የሚል አካል ወይም የሚባል አካል ካለ ግን ቀድሞውኑም መኝታውን ለእንግዳ የሚለቅ፤ ልጆቹ ተርበው እንግዳ የሚያበላ ባህል ባለቤት ነው ምድረ ካዎ ሳታ ሞቶሌ ካዎ አማዶ ፤ ካዎ ጦና ሀሹ ሣሮ ይዴታ ብለን እንቀበላለን፡፡
ዎላይቶ ቃጣራ ጌላ ፣ ኔ ላጌ ቤኢዶባ ቤኣ !!
የዎላይታ ክልላዊ መንግሥት !!
ኮርሚቻ ጦና !! Case closed.