የይስሙላ ተግባራት ለአገር ሰላም አይበጁም!!!

የካቲት 23 2015ዓም (በክብረአብ ደምሴ)

ለአንድ ሥራ ሂደቱ ትክክል ካልሆነ ውጤቱም ትክክል አይደለም፤ ብልሽቱ ከሂደቱም ጭምር ስለሆነ ነው፡፡ ሲጀመር ምርጫ መደረጉን የተስማማው የብልፅግና ፓርቲ ካድሬ ብቻ ነዉ፤ ህዝቡ ሂደቱን ባልተቀበለበት ውድቅ ሆነ አልሆነም ትርጉም የለውም። ህዝብን ግራ ማጋባት አያስፈልግም፡፡ የወላይታ ህዝብ የራሱን አቋም ካርድ ባለመውሰድ እና እንዳልመረጡ አሳይቱዋል፤ የወላይታ ህዝብ ፍላጎቱ ህገ መንግስቱ የምያጎናፅፈዉን ራስን በራሱ የማስተዳደር መብቱን ማስከበር ነዉ።

ህዝብ የሚፈልገውን አማራጭ ሳያቀርቡ ምረጡ ማለት ማንን ለማሞኘት ነበር? ይህ የተወሰኑ ቡድኖች በተለይም የብልፅግና ፓርቲ እና አካባቢው ላይ ያነጣጠረ ፖለትካዊ ጥቃትም ነው ብለን እናምናለን፡፡

ይህ የማስመሰያ ምርጫ ሊካሄድ የብልፅግና መንግስት በተቆጣጠራቸው የመገናኛ ብዙሃን እወጃ ሲያደርግ በቀረቡት አማራጮች ላይ የአንድን ፓርቲ ፍላጎት ብቻ ያካተተ በመሆኑ ሕዝቡ ካርድ ለመዉሰድ አልፈለገም፡፡ ከዚህም የተነሳ የብልፅግና ካድሬዎች ካርዱን ራሳቸዉ ፈርመዉ በስማችን ወሰዱ፤ ለምርጫ ብቁ ያልሆኑ እና ዕድሜያቸው ከ 18 ዓመት ዕድሜ በታች የሆኑ የ1ኛና መለስተኛ እንዲሁም የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎችን በማጭበርበር የምርጫ ካርድ ዕደላ ተደርጓል፤ በተጨማሪም ስራ አጥ የሆኑ ግለሰቦችንና ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው ሥራ ፍለጋ ላይ የነበሩትን የስራ ቅጥር ታገኛላችሁ በሚል መደለያ የህዝቡን ፍላጎትና ከነባራዊው እውነታ ጋር የሚቃረን ክፉ አካሄድ ተፈፀመ፤ እንከን በእንከን የሆነ ማጭበርበር ተከሰተ፡፡ በዚህ ምርጫ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ አልተሳተፈም፡፡ ምክንያቱም ሕዝቡ የሚፈልገዉ የራሱን ክልል ብቻ ነዉ፡፡

አሁን ምን መደረግ አለበት?

ሁሉንም ባሳተፈ መንገድ ፣ ህገ መንግስቱ ባስቀመጠው መንገድ መሰረት መንግስት መፍትሄ ማስቀመጥ ይኖርበታል። ዋናው መነሻችን ሆነ መቋጫው ህገ መንግስት መሆን አለበት ነው፡፡

በወላይታ ለህዝብ እንሰራለን የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎች ከልባቸው ቁርጠኛ መሆን አለባቸው፡፡ የሕዝብን መብት ማክበርና ማስከበር አለባቸው፡፡ ዴሞክራሲ የሚያብበው የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት ሲንሸራሸሩ ብቻ ነው፡፡ የአገሪቱ ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲከበሩ ነው፡፡ ብልፅግና ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሕዝብ የበላይነትንና የሥልጣን ባለቤትነትን አምነው መቀበል ነው፡፡

የይስሙላ ተግባራት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታውም ሆነ ለአገር ሰላም አይበጁም!!!