በኢትዮጵያ ሁለቱ አለሞች ውስጥ ምኞት መብት ነው
በአንዱአለም ታ. ቦልጠና
ኅዳር 11 2013ዓ.ም
ፖለቲካ ጤነኛ መገለጫው በገሃድም በጓዳ መወቃቀስ እና ህዝብን የሚፈታተኑ እንቅፋቶችን ማሳየት አንዱ ጎኑም አይደል እስኪ የተረዳሁትን ላካፍል፡፡ በዚህች አጭር ገላጭ ምንጫሮዬ የእኩልነት አቀንቃኞችን እና የአክራሪ ሪፐብሊካኒስቶችን ፍትጊያ ልጠቁም፡፡ ከአንድ ማህጸን የወጡ የአንዲት እናት ሁለት ልጆች በሃሳብ ፍጥጫ ጦር ከመማዘዝ ሃገር እስከመሰነጣጠቅ ምን ገፋፋቸው የሚለውንም አስቀምጣለሁ፡፡ እኚህ የኢትዮጵያ መንትያዎች ህልመኞች ናቸው፡፡ ህልም በራሱ ጸጋ ነው፡፡ መልካም ሲሆን፡፡
በኢትዮጵያ በነበረው ባለፈው መንግስት በስመ እኩልነት ከሪፐብሊካኒስቱ በላይ ህዝብን የጨቆነ ባለጭምብል ዛሬ ተከርብቶ በአዲስ አሰላለፍ መለያ ቀይሮ አይተናል፡፡ የሚገርመው ግን የአፍቃረ ሪፐብሊክ ትልቁ ራእይ በስመ ሰዋዊነት በህዝብ ላይ ሙሉ ቁጥጥር እና የበላይነትን መቀዳጀት ነው፡፡ ይህም ከህግ እና ከህገመንግስት በላይ ያደርጋቸዋል፡፡ ለዚህም በብሄር በሃይማኖት ወይም መሰል ስበት የሚመሰረቱ ማናቸውንም ማህበራትን በማዉደም ሰዎቹን በመግደል በማሸማቀቅ እና ሃብት ማፍራትን በመከልከል ማደህየትን ይተገብራል፡፡ በዚህም ከአንድ ፋብሪካ የወጡ ምርቶች ይመስል አንድ አይነት አልጫዎችን ይፈጥራል፡፡ ይህ ደግሞ በተገፊዎች ውስጥ ቁጣን ቁጭትን እና አጸፋ የመመለስ ለዘብተኛ ከሆኑም ራሳቸውን የመከላከል ሃይልን ይቀሰቅሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ሰዎች በብሄር በሃይማኖት ወይም በተገፉበት በዛው መስመር ራሳቸውን ሊከላከሉ ይደራጃሉ፡፡ ቀድሞ ያልተደራጁትን የጨቆነው እብሪተኛው ሪፐብሊካኒስት በሁለተኛው ኡደት የደረጁ እና ካወቁበትም ጥምረት የፈጠሩ ሃይላትን ይገጥማል፡፡
ሪፐብሊካኒስቶች ሃገራችን በሚሏት ኢትዮጵያ ላይ አሁን እየሆነ ያለው እውነታ የሁለተኛው ኡደት የፈጠረው ፖለቲካዊ ውጥረት ክሩ መበጠሻው ጋር በመድረሱ ነው፡፡ ይህም የከረረው ይበጠስ በሚሉ ጦር ሰባቂዎች እና የጥቂቶችን ፍላጎት ለማርካት ብቻ ሲባል ህዝቦች አይሰቃዩ በሚሉ አካላት መካከል የተፈጠረ ሃገራዊ ደዌ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ደዌ የተባባሰው ክሩ ተበጥሶ ያረጀው ድጋሚ ስራ ላይ ይዋል ወይስ በአዲስ ጥቅም ላይ የዋለው ስለቆሸሸ ላውንደሪ ይግባ በሚለው ጉዳይ ነው፡፡
ሪፐብሊካኒሰቶች የቀጣይ መቶ አመት እጣ ፋንታህን/ሽን ልቆጣጠር ሲሉ በማንነት የሚደራጁት ደግሞ እጣ ፋንታዬ የእኔው የራሴ ስለሆነ ለሌላ አሳልፌ አልሰጥም፤ የእኔ ለእኔ የአንተውም ለአንተ ይላሉ፡፡ የጋራ መጫወቻውም በጋራ የምንፈጥረው እንጂ ሚስጥር አይሁን ባዮች ናቸው፡፡ ይህ በዘፈን በቴአትር እና በድርሳናት እንደሚያቀሉት ተራ ጉዳይ ሳይሆን የሁለት አለማት ወይም የሁለት የአስተሳሰብ ዋልታዎች ግጭት እንደመሆኑ እጅግ በጣም ከባድ ነገር ነው፡፡ አስተሳሰቦቹን መሸከም በተቃርኖ ካለው ጋር መነጋገር መግባባት እና የጋራ መፍትሄ ላይ መድረስ በራሱ የጦርነት ያክል ከባድ ትግል ማካሄድ ነው፡፡ መደረግ ግን አለበት፡፡
በማንነት መደራጀት የመገፋት ውጤት መሆኑ እየታወቀ ዳግም መግፋት ይህንን ስሜት ይበልጥ ጥልቅ ቢያደርገው እንጂ ችግሩን አይፈታውም፡፡ ለካንሰር ፓናዶል ሰጥቶ ድነሃል እንደማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ፖለቲካዊ መቀንጨር ነው፡፡
አንድ ግለሰብ በቤቱ ሊኖር ስለሚገባው አኗኗር ለመወሰን ሙሉ ስልጣኑን ለጎረቤቱ የሚሰጥ እንከፍ የሚስት አያያዝን ለማስተማር ጎረቤቱ አልጋው ላይ ይወጣል፡፡ በስመ ሰዋዊነት እሺ ይለዋል ወይም በስመ ህልውና በሃሳብ ገና ከቤቱ ሳይነሳ እንደማያዋጣ ያስተምረዋል፡፡ አጅሬው ሚስቶቻቸውን የሚፈቅዱለት ጋር ሄዶ እፍ እፍ መባባል ይችላል፡፡ የሰው ልጅ በህልውናው ጉዳይ ላይ እንቅልፍ ላይ እያለ እንኳን ዘብ ይቆማል፡፡ እንኳን ሚስቱን ከጅለህ ቀርቶ እጇ ላይ ያለውን የሰአት ብራንድ ያወክ ጊዜ ጦርነት እንዳወጅክበት ቢቆጥር አትገረም፡፡ ቀድመህ ተኩሰሃል፡፡ ጦርነት ጦርነት ነው፡፡
እነዚህ ሁለቱ አለሞች በአንዲት ፕላኔት ውስጥ ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ ሌላ ፕላኔት እስካልተፈጠረ ድረስ ያላቸው ብቸኛ አማራጭ በአብሮነት መኖር ነው፡፡ እንደየ አስተሳሰብ አጽናፋቸው የትም ዋልታ ድረስ አቋማቸውን በቀኝም ሆነ በግራ ቢያራምዱ ሁለቱም እኩል መብት አላቸው፡፡ አስተሳሰብ ነው እና ሰው አንድን ነገር ለምን አሰብክ አይባልም፡፡ በአጭሩ የወላጆች የስነልቦና ቀውስ ወደ ልጆች አለም ተሸጋግሮ ነው፡፡ የአንዱ ቤተሰብ እኩልነት የሰዋዊነት መለኪያ ነው ሲሉት የሌላኛው ቤተሰብ አንተ የበላይ ነህ እና ይህንን ማንም አይከለክልህም ብለው ያሳድጓቸዋል፡፡ እነዚህን በሰማይም በምድርም የማይታረቁ እና የተራራቁ ፍላጎቶችን በያመኑበት መንገድ እያራመዱ አብረው መኖር አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሁለቱ አሻንጉሊት ያልሆነ የጋራ መጫወቻ ያስፈልጋል፡፡ ይህ የግድ ነው፡፡ አለበለዚያ አንዱ ሌላውን ለማጥፋት በተነሳ ጊዜ የሩዋንዳው ፍጅት በዛሬአዊው አለማችን መከሰቱ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ሰው ሰው ነውና ከራሱ ጋር እኩል የሆነውን ሌላ ሰው፤ የምትተነፍሰውን ኦክሲጂን፣ ሰሃንህ ላይ የሚቀርብልህን ምግብ፣ የውሃህን የንጽህና ደረጃ፣ ኪስህ ሊኖር ስለሚገባው ገንዘብ፣ የማህበራዊ ግንኙነት ራዲየስህን የቤትህን ወርድ እና ስፋት እና የደስተኝነት ጽዋህን ሰፍሬ ልስጥህ የሚል እብሪት ማንም አይታገስም፡፡ ባለእኔው ስለ ራሱ ‘’እኔ’’ ያውቃል፡፡ አንተም ለራስህ፡፡ በጋራ ጉዳይ ግን በማዋጣት እና በመካፈል ብቻ እና ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ሌላ ሌላውን መመኘት ይቻላል፡፡ ይህ መብት ነው፡፡ መቀበል ግን ባለእኔው ሲፈቅድ ብቻ ነው፡፡ ባለእኔው ካልፈቀደም እኩልነት እንቁ ነው እና እኩልነትን በክብር በመቀበል ከእውነታው ጋር መታረቅ ነው፡፡በቃ ይኸው ነው፡፡