ኢትዮጵያዊነት ትርጉሙ ዳግም ይከለስ!!!
በአንዱአለም ታ. ቦልጠና
ኅዳር 5 2013ዓ.ም
ይህ ግለሰብ የአብን ከፍተኛ ኃላፊ ነው፤ በግልጽ ጦርነቱ የአማራ ነው ብሏል (ከበታች በአስረጅነት የተያያዘውን ይመልከቱ)፡፡ ይህንን ጦርነት በይፋ የደገፉትም አብን ብልጽግና እና ኢዜማ ናቸው፡፡ ጦርነቱ ግን ህዝባዊ ቅቡልነቱ የት ነው? ለሚለው በየ ከተሞች የተደረገው ሰልፍ በቂ ማሳያ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሶስቱ አካላት ከህዝብ ጋር ሳይሆን ከተማ ከሚኖር urban elite ጋር ነው የተማከሩት፡፡ ኤሊቱ ውስጥ ለእነሱ ቅርበት ያለው ቀድሞውንም ከህዝብ የራቀ ነው፡፡ ለመጣ ሁሉ የሚያጎበድድ ፣ የሙገሳ ቃላት የማያጥረው ተገለባባጭ ነው፡፡ ይህ የከተማ ኤሊት ዛሬን ብላ፣ ነገን ሙት ከሚለው ብሂል አልፎ አሁን ብላ፣ በኋላ ሙት ባይ ነው፡፡ ዛሬም ነገም ያለመሳቀቅ እንብላ፣ እንስራ፣ አብረን እንኑር እንንቀሳቀስ የሚለው ሃሳብ ውስጡ የለም፡፡
የኢትዮጵያ ነው፣ ሃገር ተከዳ ምናምን ለሚሉ ሰዎች ሃገር ማለት እኛ ነን፡፡ እኛ ደግሞ መከላከያን የሚያክል የሀገር (የእኛ) መከታ ከእኛ ውስጥ በአድልዎ ለአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ ከቆመ የሁላችን አንለውም፡፡ ይህ የመከላከያ ፖሊሲ ይፈተሸ፤ የህዝባችን ጋሻ መሆን የሚገባው ሃይል ወደሚገባው ክብር ማማ ወደ ተቋቋመበት አላማ እሴቶች እና ተልእኮው ይመለስ ባዮች ነን፡፡ ለመከላከያ ያለንን ክብር ግልፍተኞች ወገንን በወገን ላይ ጦር ሲሰብቅላቸው ብቻ የሚያሞግሱት የጎረምሶች ወዳጅ ሳይሆን የሁላችም ደጀን በመሆን በሁሉም በመወደድ፣ በመከበር፣ በመደገፍ እና ውድ ነፍሱን እና ደሙን ሲሰጠን ሁላችንንም ያለ አንዳች ስጋት በሙሉ በመተማመን አንዲንቀሳቀስ ነው፡፡ እኛ ፖለቲካን በፖለቲካ ይፈታ ባዮች ነን፡፡ መከላከያውም የተበላሸ ፖለቲካ ሰለባ አይሁን ባዮች ነን፡፡ እኛ ዎላይታዎች ነን፤ እኛ ኦሮሞዎች ነን፤ እኛ ጉራጌዎች ነን፤ እኛ ሲዳማዎች፣ ጉሙዞች ፣ ካፋዎች ፣ ካምባታ፣ ሃድያ ጠንባሮ እና ሃላባዎች ነን፡፡ እኛ የሀገሪቱ ድምጾች ነን፤ ይህንን ድምጻችንን ያላማከለ ነገር ኢትዮጵያዊነት ሳይሆን የአንድ ብሄር አካልነት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ትርጉሙ ዳግም ይከለስ፡፡
ለአንድ ወገን ጦርነት ክተት ማወጅ የመከላከያችንን ከፍታ ወደመሬት ዝቅ ያደርገዋል፡፡መከላከያውን መሬት ለመሬት ወደሚሳበው ፖለቲካችን አይጎተት፡፡ ከፍታው ላይ ይቆይ፡፡ አኛ ወደ እሱ ከፍታ እንጂ እሱ ወደ እኛ ዝቅታ አይውረድ፡፡ ሃገር ማለት እኛ ነን፡፡ አኛ ራሳችንን አልከዳንም፡፡ ይልቅ ሃገሩን ከድቶ ወደ ብሄር ጠርሙሱ ያጠለቃት አካል አደብ ይግዛ፡፡
ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት አሁን ፀጥታውን እና ደህንነቱን መከላከያውን ማሽከርከር እና የግል አሻንጉሊቱ ማድረግ በሚፈልገው ኃይል ሳይሆን በሁሉም ኢትዮጵያውያን እይታ ዳግም ይመዘን፣ ይተርጎም፣ ይተንተን፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያም በኢትዮጵያውያንዉያት ዕይታ ዳግም ይታይ፤ ይጠና፡፡
ኢትዮጵያ የአንድ አካልነት ወይ አንድ አይነትነት መልበስ ከሆነ ቀድሞውንም የለችም፡፡