ይድረስ ለSeyoum Teshomeና አሳዳሪዎቻቸው እንዲሁም ገዳዮቻችን
በታምራት ግቦን
August 11, 2020
እናንት “ጭምብል-ለባሽ ኢትዮጵያዊያን” የዘረኝነት ጥግ መገለጫ ናችሁ። ሞትንና የህዝብን ሰቆቃ ደፍሮ ለመዘገብ አቅም ያጣችሁ የፖለቲካ ድኩማን። “ህዝቡ ተነግሮት መብቱን አሳልፎ ካልሰጠ መንግስት በጥይት ቢቆላው ስህተት የለውም” የምትሉን ሰው-ጠል ፍጡራን::
ለኔ ምንሊክ፣ ሀይለስለሴ፣ መንግሥቱ፣ መለስና ሀይለማርያም# የኢትዮጵያ መሪዎች ናቸው – ደግም ክፉም የሠሩ። ያንዱ ደግነት ብቻ ተወርቶ፣ የሌላው መሰሪነት ብቻ እንዲዘፈን መሻት፣ ያው የናንተው የዘረኝነት ወግ ሆነ እንጂ የምንሊክ ህፀፅ ሲነሳ፣ ወላይታን አሊያም ኦሮሞን ማቅለል ኢ-አመክኗዊ ነው። የሃይለማርያምም ሆነ የመለስ ህፀፅ ሲነሳ የሚንጨረጨር ወላይታ ና ትግሬ ካለም እንዲሁ። ግን መሪዎቹን በወጡበት ብሄር ሳቢያ የምንጠላ አሊያም የምናጀግን ከሆንን ከንቱዎች ነን – የአክራሪ ብሔርተኝነት ካንሰር ተጠቂዎች። በናንተ ስሌት፣ ደግም ሆነ ክፉ ቢሠራ – ሁሌ መዋረድ፣ ሁሌ መሰደብ ያለባቸው መሪዎች አሉ። በሌላ መልኩ፣ ሁሌ መወደስ የሚገባቸው ፃድቃን መሪዎች አሉ። ይህ ነው እንግዲህ የናንተ የጎዶሎነት ጅማሮ።
የወላይታን ስነልቦና አላወቅህም እንጂ ካንተ በላይ ወላይታ የአማራ ወዳጅ ነው። አታውቀውም እንጂ ‘አማራ ውስጥ ወላይታ’፣ ‘ወላይታ ውስጥ አማራ’ የይዞታ ባለቤት ሆነው፣ ተጋብተው፣ ተዋልደው፣ በየሚኖሩባቸው አከባቢ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ ና ፖለቲካዊ ተሳታፊዎች ሆነው ኖረዋል። በወላይታ ምድር ሌሎቹም እንዲሁ እትብታቸው ተቀብሮ “ወላይታ ሀገሬ” ብለው ይኖራሉ። ወላይታ የአማራ፣ የትግሬ፣ የኦሮሞ፣ የጉራጌ፣ የስልጤ፣ የካምባታ…መኖሪያቸው ነች። ግን እናንት “ጭምብል ለባሽ ኢትዮጵያዊያን”፣ ገዳዮቻችን ወጪት ሰባሪ ሆናችሁብንና “መዓት” ተመኛችሁብን።
ወላይታን፣ ባገሩ ለስራ በተሰማራበት በኢትዮጵያ ከተሞች አንገቱን ቀላችሁ። ሲቀጥል፣ በክልሉ ሀብት ንብረት አፍርቶ በከተመበት ከነነፍሱ አቃጠላችሁ። በመጨረሻም እስከቀየው፣ እስከቤቱ ዘልቃችሁ በደ(ጃ)ፉ ደፋችሁ። የቀደሙት ጉልበቱን ሲበዘብዙ፣ ያለጥርት አስቀርተውት እንዲሁ አለፉ – ነፍሱን ግን አልቀሙበትም። እናንት “ጭምብል-ለባሽ ኢትዮጵያዊያን” ግን አልጋ ለመውረስም፣ ባልጋው ለመደላደልም፣ ደጋግማችሁ ገደላችሁ። የናንተ የፖለቲካ ጥም መቁረጫና የኪሳራ ማወራረጃ፣ የለፍቶ-አዳሪው ደም መሆኑ ሲታይ ምንኛ ይሰቀጥጣል!? ኧረግ…ደርግስ በስንት ጣዕሙ!? ይሁን’ጂ ዛሬም ቢሆን ወላይታ ሃሳብን በሃሳብ ከመሞገት፣ ጥያቄን በብዕሩ ከመከተብና መብቱን በደብዳቤ ከመጠየቅ አይመለስም። ወላይታ እንደሆን የሚበጀውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ህዝብ ነው፤ ጥይታችሁንና ማገዷችሁን አትፍጁ።
ጥይት ስጋውን ብትገልም፣ ሃሳቡን የመግደል አቅም አይኖራትም። ወላይታ በማንነቱ ኮርቶ ለዘላለም ይኖራል፤ ነገም ሌላ ቀን ነው።
ህዝብ ያሸንፋል!!!