ይድረስ ለተከበሩ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ
ከአብዲ ራዋ
August 09, 2020
ይድረስ ለሀገራችን ህዝቦች ፣ለኃይማኖት ተቋማት ምክር ቤት ፣ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ለምትኖሩ እውነተኛ የሚዲያ ባለሙያዎች:-በዛሬው ዕለት በወላይታ ዞን በሶዶ ከተማ ጉተራ የስብሰባ አዳራሽ የዞኑ አስተዳዳሪ የዞኑ የብልፅግና ቢሮ ኃላፊ ፣ምሁራን ፣የሀገር ሽማግሌዎች ፣የመብት ተሟጋቾች ስብሰባ እያደረጉ በነበሩበት ወቅት የፌደራል ፖሊስ ፣የሀገር መከላከያ ሰራዊት አዳራሹን ከበው የዞኑን ርዕሰ መስተዳድር አቶ ዳጋቶን ጨምሮ ጨምሮ ከ26-28 የሚሆኑ የህዝብ ተወካዮች በቁጥጥር ስር አውለው ወዳልታወቀ ስፍራ ወስዷቸዋል፡፡ይህንንም ተከትሎ ለተቃውሞ በወጡ ነዋሪዎችና በፀጥታ አካላት መሀከል ግጭት ተቀስቅሶ ከተማዋ ለረጅም ሰዓት በተኩስ ድምፅ ስትናጥ አምሽታለች፡፡ነዋሪዎቿም በጥልቅ ጭንቀትና በአስፈሪ ድባብ ውስጥ አምሽተናል፡፡ከዛሬዎቹ ታጋቾች መሀል አብዛኞቹ ላለፈው አንድ ዓመት በተከታታይና በተደጋጋሚ ከጠ/ር አብይ ጋር ሲገናኙ ፣ሲመክሩ ፣ሲወያዩ የነበሩ ነበሩ፡፡
ካልተሳሳትኩ ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚ/ሩ ቢሮ እንደተገኙ አውቃለሁ፡፡የሀገራችን ህዝቦች የኃይማኖት አባቶች የፖለቲካ አባላትና አመራሮች:-ሀገራችን አሁን ባለችበት ዘረፈ ብዙ ፍዳዎች ፣መከራና ስቃይ መሀል ሌላ ብዙ የማያስኬት የፖለቲካ ሴራ ያሻታልን?የብሔር ፣የዕምነት ፣የጎሳ ፣ግጭቶች የለኮሱብን እሳት ወላፈኑ ሳይዳፈን ፣በcovid 19 በግላጭ እየተቀጣን ፣በኑሮ ወድነት ከአፈር ትቢያ ተቀላቅለን ፣በነገ የምግብ ዋስትናችን ላይ የአንበጣ መንጋ ፍጅትና የጠኔ ዳንኪራ እየጎሰመብን ፣በምስራቅ አፍሪካ ጂኦ ፖለቲክስ በቅርብና ሩቅ ባሉ ባላጣዏቻችን ሴራ እየተፈተንን ፣በአጎራባች ክልልና ዞኖች የንፁሃን ህይወትና ንብረት ሲጠፋና ሲወድም እያየን ፤ፍፁም ማስተዋል የጎደለው እርምጃ ና አፈና መፈፀሙ ሊወገዝ ይገባል፡፡
በሌሎች አካባቢዎች ያየናቸው በድንጋጤና በሀዘን ልቦቻችንን ያደሙት ፣የሀዘን ሸማቸውን ሳያወልቁ ፣የንብረቶቻቸውን አመድና ብናኝ ሳይጠርጉ ፣ወላይታን ለአዲስ ሀዘንና ለቅሶ የመታጨቷ ሴራና ከወዲሁ ሊቆምና ሊታረም ይገባል፡፡ከአንዳንድ ሚዲያዎች “ከህውሃትና ከኦነግ ሸኔ ጋር …ወዘተ”የሚለው መግለጫ ሌላው ቅስም ሰባሪ ክስ ነው፡፡የተከበሩ ጠ/ሚ :-ሀገራችን አሁን ባለችበት ዘርፈ ብዙ ውጥረቶች መሀልም ቢሆን ፤የህዳሴ ግድባችን የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ደስታ ከዳር እስከ ዳር በዕልልታ ፣በደስታ ፣በአዳዲስ ዜማዎች ሲታጀብ የወላይታ ህዝብና ነዋሪዎቿ ግን በጥይት አረር የባሩድ ሽታ መታጠን አለብን?ይህ ተገቢ ነው?መመካከር መያየትና መነጋገር ሮኬት ከማምጠት የተሻለ ስልጣኔ ነው፡፡ደግሞ የአንድ ፓርቲ አባላት በመሆናችሁ የህዝብን ጥያቄ ያቀረቡ አባላቶቻችሁን በጓዳችሁ አትፋጩም?የሆነ ሆኖ ለዘላቂ የህዝቦች ሰላም እስር የመሳሪያ ድምፅ ሳይሆን መወያየት ፣መመካከር ፣መከራከር እንጂ ሌላው መንገድ ውሃ አይቋጥርም፡፡ህዝብ እንደ ህዝብ ያመነበትን ጥያቄ የጠየቀው “ይህ አካል ፣ይህ መንግስት ይሰማኛል”ብሎ ነው፡፡አይ አልሰማህም የማናግርህ በባሩድ ሽታ ነው ከተባለ የሁላችንም “ከል”የመልበሻችንጊዜ ቅርብ ነው፡፡ፈጣሪ የሰጠንን ሰላም በፈጣሪ ስም እንጠብቅ፡፡ወንድሞቻችንን መልሱልን፡፡
ያንዣበበብንን አደጋ ፣ክፉ ሴራ ፈጣሪ ይመልሰው፡፡ሠላማችንን መልሱልን፡፡