ከዎላይታ ሕዝብ ዲሞክራሳዊ ግንባር በወቅታዊ ጉዳይ የተሰጠ መግለጫ
August 12, 2020
የዎላይታ ሕዝብ ራስን በራስ በክልል ደረጃ የማስተዳደር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ታህሳስ 10፣ 2011 ዓ/ም በዞን ምክር ቤት አስወስኖ ከላከበት ቀን ጀምሮ የክልል እና ፌዴራል መንግስትን በፍጹም ሰላማዊ መንገድ አስፈላጊ የሆኑ ሁሉንም ህጋዊ መስፈርቶች አሟልቶ ስጠይቅ ቆይቷል፡፡ እስከ ታህሳስ 10፣ 2012 ዓ/ም ድረሰ የክልል መንግሰት ሕዝበ-ዉሳኔ እንዲያደራጅ ቢጠበቅም ፈቀደኛ ሳይሆን ቀርቶ ከፌዴራል መንግስት አካላት ጋር በመሆን የዎላይታ ሕዝብ ጥያቄ ምላሽ ህዝብ በሚፈልገው ሳይሆን እነሱ በሚፈልጉት መልክ ከውሳኔ ለመድረስ የተለያዩ አማራጮችን ሰሞክሩ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ከታህሳስ 2012 ዓ/ም በኃላ የሕዝብ ጥያቄ እንዲመለስ ፊት አዉራሪ በመሆን የፌዴራልና የክልል መንግስት አካላት አመራጮችን እምቢ በማለት የሚታወቀው የዎላይታ ዞን አስተዳደር ፊት አመራሮች የዎላይታን ጥያቄ ከፈራሹ ደቡብ ክልል ም/ቤት በላይ ወደ ሆነዉ ወደ ፌዴሬሸን ም/ቤት ሰላማዊ ትግላቸውን በማሰቀጠል በታህሳስ ወር 2012 ዓ/ም መጨረሻ አከባቢ የይግባኝ አቤቱታቸውን አስገብቷል፡፡ ይህን ከደረጉ በኃላ ከህዝብ ከተወጣጡ አካላት ማለትም የህዝብ ሽማግሌዎች፡ የወጣት(የላጋ) ተወካዮች፤ አክትቨስቶች፣የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ፣የምሁራን ተወካዮች፤ የሲቭክ ማህበር ተወካዮች እንዲሁም ተዋቂ ግለሰቦች ጋር በቀጣይ ሰላማዊ ትግል ዙሪያ ዉይይት ማካሄድ መጀመራቸዉ ይታወቃል፡፡
የዚህን ሰላማዊ ትግል በቀን 03/12/12 ዓ /ም ዉይይት እያደረጉ ባሉበት ሁኔታ ባልታወቀ ምክንያት በመንግስት ፀጥታ ኃይሎች መተገታቸው ህገ-ወጥና ኢ-ህገ-መንግስታዊ ከመሆኑም ባለፈ የአምባገነናዊ መንግስት መገለጫ ስለሆነ ዎሕዴግ አጥብቆ ይቃወማል፡፡
ስለሆነም የዎላይታ ሕዝብ ሰላማዊ ትግል አራማጆች ላይ የማገት ድርግት የፈጸሙ አካላት በአስቸኳይ ለህግ-እንዲቀርብ፤ የታገቱ ሰዎች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ፤ መንግስት በፈጠረዉ ሁኬት ከ15 በላይ የሆኑ ንጹሃን ዘጎች የሞቱ ስለሆነ ነፍሳቸው በህግ እንዲጠየቅና ፍትህ እንዲረጋገጥ፤ የዎላይታ ሕዝብ ክልል የመሆን ጥያቄ በአስቸኳይ ምላሽ እንዲያገኝ፤ የሕዝብን ትግል የሚያጠለሽ፤ከኦነግ ሼነ እና ከሕዋኣት ጋር የሚያለክኩ የመንግስት መግለጫዎች በአስቸኳይ እንዲታረሙና መንግስትም በዚህ መግላጫ ላይ ሕዝቡን በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ፤
ሕዝባዊ አመጽ ተቀስቅሶ ሌላ አቅጣጫ ከመያዙ በፊት መንግስት የሚመለከታቸውን ሁሉአቀፍ ማህበረሰብ በማነጋገር ከሕዝብ የሚመነጭና ተቀባይነት ያለው በሳል መፍትሄ እንዲሰጥ፤
የዎላይታ ሕዝብ ጥያቄ እንዲስተጓጓል እንዲሁም የተዛባ እንዲሆን የሚሰሩ የመንግስት አካላት፤ የኢትዮጵያ ማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ(ኢዜማ)፤ አንዳንድ የግልና የመንግስት ሚዲያዎች ላይ ወጥቶ የቀኝ-ዘመም ማብራሪያ የሚሰጡ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ፤
መላዉ የዎላይታ ሕዝብ ሆይ ያለምንም ልዪነት የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ የሚታወቁበትን ፍጹም ሰላማዊ ትግል የሕዝቦችን አብሮነት በማይነካ መልኩ በማቀናጀት አጠናክራችሁ እንዲትቀጥሉ እያሳሰብን ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔረ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለዎላይታ ሕዝብ ያላችሁን የኢትዮጵያዊ ወገንተኝት እንዲታሳዩና ከጎችን እንዲትቆሙ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡
ዎላይታ ሕዝብ ዲሞክራሳዊ ግንባር
ነሐሴ 6 ቀን 2012 ዓ.ም
ዎላይታ