የዎላይታ ሕዝብ የትግል መሪዎች መታሰርን አስመልክቶ ዎሕዴግ ያወጣው አስቸኳይ መግለጫ

Wolaita Today

August 09, 2020

መንግሥት ሠላማዊና ሕጋዊ የሆነውን የሕዝብ ጥያቄ ወደ ሁከት ለመቀየር የሚያደርገው እንቅስቃሴ እንዲያቆም አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

ዛሬ ቀን ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም የወላይታ ዞን አመራሮችና ከተለያዩ ሕዝባዊ አደረጃጀት የተወጣጡ የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምሥረታ አስተባባሪ ካውንስል አማካሪ ቦርድ አባላት በወላይታ ጉታራ ስብሰባ ላይ ባሉበት ወቅት ድንገት በመጣው የመከላከያ ኃይል ታፍነው ታስረዋል፡፡ የወላይታ ዞን ኮር አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ተወካዮች፣ የድርጅታችን የዎሕዴግ ም/ሊ/ር ፣የዎብን አደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊ፣ የዎላይታ ልማት ማህበር ሥራ አስኪያጅ ፣የተለያዩ አክትቪስቶች እና ሌሎች ክልል ምሥረታ አስተባባሪ ካውንስል አባላት ታፍነው ታስርዋል፡፡

የፌዴራልና የደቡብ ክልል መንግሥታት የወላይታ ሕዝብ ሠላማዊ ጥያቄ ወደ ሁከት ለመቀየር የሚያደረገው ሕገወጥ ድርጊት እንዲያቆም አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

የወላይታ ዞን አመራሮችንና የወላይታ ክልል ምሥረታ ካውንስል አማካሪ ቦርድ አባላትን፣ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎችንና በአጠቃላይ የሕዝቡ የትግል መሪዎችን በማሠር የሚቆም ትግል የለም፡፡ ፍትሐዊ፣ ሕገ-መንግሥታዊና ፍፁም ሠላማዊ በሆነ መንገድ በመጠቀም የወላይታ ሕዝብ ለሚጠይቀው ጥያቄ በሠላም ምላሽ ከመስጠት ይልቅ አመራሮችንና ታጋዮችን የማሠር እርምጃ ፈፅሞ ሕገ-ወጥና የመብት ጥሰት ተግባር ነው፡፡

በመሆኑም የወላይታ ሕዝብ ጥያቄ ምላሽ እስኪሰጠው እና በሕገ-ወጥ መንገድ በሠላም ስብሰባ እያካሔዱ ሳሉ በወታደራዊ ከበባ የታሠሩ የወላይታ ሕዝብ የትግል መሪዎች እስኪፈቱ ድረስ ሁላችንም በአንድነት እስረኞች ነን፡፡ የታሠሩ ሰዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱና የወላይታ ሕዝብ በክልል የመደራጀት ሕገ-መንግስታዊ ጥያቄ በአስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ አጥብቀን እንጠይቃለን፡
የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር

ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም

ዎላይታ ሶዶ

Wolaita Today
Wolaita Today
Wolaita Today