የወላይታ አከባቢ ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ከዎብን የተሰጠ መግለጫ
ነሐሴ 17 ቀን 2012 ዓ.ም
የተከበረው የዎላይታ ሕዝብ በ1887 ዓ.ም የራስ መስተዳድሩ እና ስልጣኔው በኃይል ከፈረሰበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት በርካታ ዓመታት ራሱን በራሱ የማስተዳደርና ሀገራችንንም ቅቡልነት ባለው ተግባቦት በጋራ የማስተዳደር ጥያቄውን በተለያዬ መልኩ ሲያነሳና ሲታገል መቆየቱ ይታወቃል፡፡ በ1983 ዓ.ም በሀገሪቱ የተደረገውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ በተደራጀው የሽግግሩ መንግሥት ወቅት ዎላይታ ራሱን የቻለ ክልል እንደነበረም ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን በ1987 ዓ.ም በፀደቀው ሕገ መንግሥት መሠረት ዎላይታ በደ/ብ/ሕ/ክ መስተዳደር ሥር ያለ ህዝቡ ፍላጎት እንዲካተት ተደርጓል፡፡ ከመነሻው ጀምሮ በመቃወም ሲጠይቅና ሲታገልለት የቆየው የዎላይታ ሕዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር የሚያስችለው በክልል የመደራጀት መብቱ አሁንም አልተከበረለትም፡፡
ሕዝቡ በክልል የመደራጀት መብቱ እንዲከበርለት ጥያቄውን ይበልጥ በማጠናከር ሕዝባዊ መሠረት ይዞ እጅግ በሰለጠነና ፍፁም ሠላማዊ በሆነ መንገድ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ በ2011 ዓ.ም የዎላይታ ሕዝብ እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር ተወያይቶ በሙሉ ድምፅ ያፀደቀው በክልል የመደራጀት ጥያቄ በዎላይታ ዞን ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ ፀድቆ ህዳር 10 ቀን 2011 ዓ.ም ለደቡብ ክልል ምክር ቤት በጽሑፍ ቀርቧል፡፡ የሀገሪቱ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙባቸው በተለያዩ መድረኮችም የዎላይታ ሕዝብ በክልል ለመደራጀት ያለውን ፅኑ ፍላጎት በማያሻማ ሁኔታ ግልፅ ተድርጓል፡፡
የደቡብ ክልል ምክር ቤትና የክልሉ መንግሥት ከዎላይታ ዞን ምክር ቤትና ከሕዝቡ የቀረበውን ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት ተቀብሎ ለምርጫ ቦርድ በመምራት ሕዝበ ውሣኔ እንዲካሄድ በሕገ-መንግሥቱ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ባለማድረጉ የወላይታ ዞን ምክር ቤት ጥያቄውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረቡ ይታወቃል፡፡ የሀገሪቱ መሪዎችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፌ-ጉባዔ ለሚዲያ ቀርበው በሀገሪቱ ውስጥ የተነሱ የማንነትና የሕዝቦች በክልል የመደራጀት ጥያቄዎች ሕገ-መንገሥቱ በሚፈቅደው አግባቡ ምላሽ እንደሚሰጥ መገለፁን ተከትሎ የዎላይታ ሕዝብ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት የሚሰጠው ውሣኔ በትግዕስት ሲጠባበቅ ቆይቷል፡፡
በዚሁ ሁኔታ እያለን ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም የዎላይታ ዞን አመራሮች፣ ከተለያየ አደረጃጀት የተወጣጡ የዎላይታ ብሔራዊ ክልላዊ ጥያቄ በሕጋዊ መንገድ ሲያስተጋቡ የቆዩ የሀገር ሽማግሌዎች ተወካዮች፣ የንግድ ምክር ቤት አመራሮች፤ የድርጅታችን ዎብን አደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊ፣ የዎህዴግ ም/ሊቀመንበር፣ የተለያዩ አክቲቪስቶች እና ምሁራን መታሰራቸውን ተከትሎ በተነሳው የሕዝብ ተቃውሞ በርካቶች ለሞትና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ የፀጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ በመውሰዳቸው ምክንያት ንፁሐን ለሞትና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡
የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ ድርጅታችን ዎብን ችግሩ በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ፣ የታሰሩት እንዲፈቱና በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት ለሞቱት፣ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ተጣርቶ ካሳ እንዲከፈል፣ የክልሉ መንግሥት ሕዝቡን በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅና ጉዳዩን በሰከነ መንገድ በመመልት እልባት እንዲሰጥ ሠላማዊ ጥሪ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡
ድርጀትታችንና የተለያዩ ባለ ድርሻ አካለት ፣ ከምንም በላይ ሠላም ወዳዱ የወላይታ ሕዝብና በሀገራችንና በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የሕዝብ መብት ተቆርቋሪዎችና በሚዲያ ተቋማት በተደረገው ሰፊ ጥረት የታሰሩ አካላት በዋስ እንዲፈቱ የተደረገውን እርምጃ በአዎንታዊ መንገድ ተመልክቶታል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የደቡብ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ነሐሴ 16 ቀን 2012 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የህዝቡ ጥያቄ በዴሞክራሲያዊ መንገድና በራሱ በህዝቡ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ ባጠረ ጊዜ ምላሽ እንዲያገኝ በተደራጀ መንገድ እየሰራ እንደሚገኝ መግለፁን ተመልክተናል፡፡
ይሁን እንጅ መንግስት በወላይታ በተከተሰተው ቀውስ ወቅት ለሞቱትና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው አካለት በገለልተኛ አጣሪ አካል በሚወጣው ሪፖርት መሠረት ካሳ ስለ መክፈል፣ የሠላም ቀጠና ሆኖ በቆየው አከባቢ በተፈጠረው ቀውስ ኃላፊነት ለመውሰድም ሆነ ሕዝቡን ይቅርታ ለመጠየቅ ድፍረት መታጣቱ ስህተት መሆኑን ድርጅታችን ያምናል፡፡ እንዲሁም ለተከሰተው ቀውስ ተጠያቂነት ወደ ሌላ አካል ለማስተላለፍ በሚያሳብቅ ሁኔታ የተገለፀው መግለጫ መንግስት እንደ መንግሥት በራሱ በኩል ለሚፈጠሩ ውድቀቶችም ሆነ ስኬቶች በተገቢው መልኩ ኃላፊነት ለመውሰድ አለመዘጋጀቱን ያመለክታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በመግለጫው የሕዝቡ ጥያቄ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በኩል ለምርጫ ቦርድ ተመርቶ ሕዝበ ውሣኔ የሚካሄድበትን ሁኔታ እንደሚገለፅ እየተጠበቀ እያለ የክልል ጥያቄው ባጠረ ጊዜ ምላሽ እንደሚሰጥ በድፍኑ ተጠቅሶ መታለፉ ያሳስበናል፡፡
በመሆኑም ዎብን ቀጥሎ የተቀመጡ ጥያቄዎችን ለመንግሥት እያቀረበ በሀገራችን ሆነ በዓለም ደረጃ የሚገኙ የሚገኙ የፍትሕና የሕዝብ ተቆርቋሪ ተቋማት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጥ የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ ጠሪያችንን እናቀርባለን፡፡
- የወላይታ አመራሮችም ሆነ ከሌሎች የተለያዩ ማህበረሰቡ የተወጣጡ የክልል ጥያቄ አራማጅ አካላት ላይ የተመሠረተው ክስ ተቋርጦ ለችግሩ በሐቅና በመተማመን ላይ የተመሠረተ ውይይት ተካሂዶ ዘላቂ ዕልባት የሚበጅበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንዲሰራ አጥብቀን እየጠየቀን ከዚህ ውጭ በየትኛውም አካል የሚደረግ አካሄድ ለሕዝቡ፣ ለአከባቢው ሠላምና ልማት የማይበጅ መሆኑ ግንዛቤ ተወስዶ ሁሉም አካላት የሕዝቡን ጥቅም በማስቀድም ሠላማዊ መፍትሔዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አጥብቀን እናሳስባለን፡፡
- የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ ለሞቱትና ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች በገለልተኛ አካላት ተጣርቶ ተጊቢ ካሣ እንዲከፈልና ጉዳት ያደረሱ አካላት ላይ ተጣርቶ በሕግ እንዲጠየቅ እንዲደረግ በድጋሚ እንጠይቃለን፡፡
- የወላይታ ሕዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄ በገዥው ፓርቲ አቅጣጫ ሣይሆን በሕገ-መንግስቱ ድንጋጌ መሠረት ከፌዴሬሽን ምክር ቤት በኩል ለምርጫ ቦርድ ተመርቶ ሕዝበ-ውሳኔ እንዲካድ እንዲወሰን እንጠይቃለን፡፡
- መላው የወላይታ ሕዝብ፣ የመንግሥት አመራር አካላት፣ የመብት አቀንቃኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት ተቋማት ለአከባቢው ሠላምና ፀጥታ ፣ ለአንድነትና የተፈጠሩ ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱ እንደ በፊቱ ሁሉ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ