የዎላይታ ሕዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄ አስመልክቶ ከዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ /ዎብን/ የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ

Wolaita Today

የተከበረው የዎላይታ ሕዝብ በ1887 ዓ.ም ምህረት የራስ መስተዳድሩ እና ስልጣኔው በኃይል ከፈረሰበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት በርካታ ዓመታት ራሱን በራሱ ኢትዮጵያችንንም በጋራ የማስተዳደር ጥያቄውን በተለያዬ መልኩ ሲያነሳና ሲታገል መቆየቱ ይታወቃል፡፡ በ1983 ዓ.ም በሀገሪቱ የተደረገውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ በተደራጀው የሽግግሩ መንግሥት ወቅት ዎላይታ ራሱን የቻለ ክልል እንደነበረም ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን በ1987 ዓ.ም በፀደቀው ሕገ መንግሥት መሠረት ዎላይታ በደ/ብ/ሕ/ክ መስተዳደር ሥር ያለ ህዝቡ ፍላጎት እንዲካተት ተደርጓል፡፡ ከመነሻው ጀምሮ በመቃወም ሲጠይቅና ሲታገልለት የቆየው የዎላይታ ሕዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር የሚያስችለው በክልል የመደራጀት መብቱ አሁንም አልተከበረለትም፡፡

ላለፉት 27 ዓመታት ከ56 በላይ የሚሆኑ ብሔር ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን ጨፍልቆ ሲገዛ የነበረው የደቡቡ ክልላዊ መንግስት በኢፍትሐዊነቱ፣ በፀረ ዴሞክራሲ ባሕርዩ እና በለየለት አምባገነናዊ አገዛዙ የሚታወቅ ነው፡፡ በሀገሪቱ የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ በሐዋሳ ከተማና በሲዳማ ዞን በሚኖሩ የዎላይታ ተወላጆች ላይ የተፈፀመው ዘር ተኮር ጥቃትም በክልሉ ሥር ሰድዶ ከነበረው ኢፍትሐዊ፣ አድሎአዊ አስተዳደር የአመራር ዝንፈት እና ዜጎችን ለመከላከል ግድየለሽ በመሆኑ ምክንያት መሆኑን በመረዳት ድርጅታች ሲያወግዝ እንደቆየ ይታወቃል፡፡

በዎላይታ ተወላጆች ላይ የተፈፀመውን ብሄርን መሰረት ያደረገ ጥቃት ተከትሎ ሕዝባችን ቀድሞ ሲያቀርብ የነበረውን በክልል የመደራጀት ጥያቄ ይበልጥ በማጠናከር ሕዝባዊ መሠረት ይዞ እጅግ በሰለጠነና ፍፁም ሠላማዊ በሆነ መንገድ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ በ2011 ዓ.ም የዎላይታ ሕዝብ እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር ተወያይቶ በሙሉ ድምፅ ያፀደቀው በክልል የመደራጀት ጥያቄ በዎላይታ ዞን ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ ፀድቆ ህዳር 10 ቀን 2011 ዓ.ም ለደቡብ ክልል ምክር ቤት በጽሑፍ ቀርቧል፡፡ የሀገሪቱ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙባቸው በተለያዩ መድረኮችም የዎላይታ ሕዝብ በክልል ለመደራጀት ያለውን ፅኑ ፍላጎት በማያሻማ ሁኔታ ግልፅ ተድርጓል፡፡

የደቡብ ክልል ምክር ቤትና የክልሉ መንግሥት ከዞኑ ምክር ቤትና ከሕዝቡ የቀረበውን ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት ለምርጫ ቦርድ መርቶ ሕዝበ ውሣኔ እንዲካሄድ ባለማድረግ ምክር ቤቱ ለህዝቦች ሉዓላዊነት ያለው ክብር ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አድርጓል፡፡ ለክልሉ ምክር ቤት የቀረበው ጥያቄ ታፍኖ በመቅረቱ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድበት ለሀገሪቱ ምርጫ ቦርድ እንዲመራ ለፌደሬሽን ምክር ቤት በጽሑፍ የቀረበለት የሕዝብ ጥያቄም እስከ አሁን ምላሽ ሳይሰጥበት ቆይቷል፡፡ በሌላ በኩል ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47/2 ድንጋጌ መሠረት ሕገ-መንግሥታዊ ምላሽ ከመስጠት በጥናት እመልሳለሁ በሚል መነሻ የደቡብ ክልል መንግሥት በዥው ፓርቲ አመራር ሰጪነት አወዛጋቢ ጥናት ተካሂዶ የሪፖርቱ ቀርቦ ነበር፡፡ በዚሁም ጉዳይ የዎላይታ ሕዝብ ጥያቄ በሕገ-መንግስቱ ድንጋጌ መሠረት የቀረበ እንደ መሆኑ መጠን ሕገ-መንግሥታዊ ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባ የዎላይታ ሕዝብ፣ ድርጅታችን ዎብንና የዞኑ አስተዳደር በሁሉም የመንግሥት ደረጃ የሚገኙ የዎላይታ ሕዝብ ተወካዮችና አመራሮች በፅኑ በመቃወማቸው ጥናቱ ውድቅ መደረጉ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

የክልሉ ገዥ ፓርቲና የሚመራው መንግሥት ያስጠናው ጥናት ውድቅ የተደረገ ቢሆንም ሠላም አምባሳደር የተባለው በክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር የተቋቋመው ኢህገመንግስታዊ ኮሚቴ ክልላዊ አወቃቀርን አስመልክቶ ሌላ ጥናት እንዲካያሂድ ተደርጓል፡፡ በጠ/ሚር ዶ/ር አቢይ አህመድ የተቋቋመው 80 አባላትን ያቀፈው ይህ ኮሚቴ ባለፉት አራት ወራት ውስጥ በደቡብ ክልል ተንቀሳቅሶ የሕዝብ መድረኮችን በማዘጋጀትና ከተለያዩ ማህበራዊ መሰረቶች የተለዩ ሰዎችን በማሳተፍ ጥናት አካሂዷል፡፡ የኮሚቴው አባላት በዎላይታ ሶዶ ከተማ ባዘጋጁት ከሁሉም ማህበራዊ መሠረቶች የተጋበዙ ታዳሚዎች በተገኙበት መድረክ የዎላይታ ሕዝብ ፍላጎቱ ራሱን ለብቻ በክልል አደራጅቶ መምራት እንደ ሆነ እና ከሌሎች ብሔሮች ጋር እንደ ወትሮ ሁሉ በኢትዮጵያዊ ወንድማማችነት ተባብሮ ከመኖር ውጭ አብሮ በክልል የመደራጀት ፍላጎት እንደሌለው በግልፅ አስቀምጧል፡፡

ይሁን እንጅ ሕዝቡ አንስቶ ከነበረው ጥያቄ ባፈነገጠ መልኩ ህገወጡ የሠላም አምባሳደር የተሰኘው የጥናት ኮሚቴ የዎላይታ ሕዝብ ከሌሎች በኦሞ አከባቢ ከሚገኙ ሕዝቦች ተጨፍልቆ እንዲደራጅ የሚያደርግ ምክረ ሐሣብ አቅርቧል፡፡ ድርጅታችን ዎብን የጥናቱ ሪፖርት የዎላይታን ሕዝብ ፍላጎት ያላገናዘበ መሆኑን ቀድመን በመረዳታችን አካሄዱ የዎላይታ ሕዝብ መብት የሚጋፋ በመሆኑ እንዲታረም የሚያሳስብ መግለጫ ማውጣታችን ይታሳል፡፡ ኮሚቴው ከሕዝብ የቀረበውን ጥያቄና ከድርጅታችን በኦፊሴላዊ መግለጫ የተሰጠውን የእርምት ሐሣብ ወደ ጎን በመተው የህዝባችንን ፍላጎትና መብት የሚጋፋ ምክረ ሐሳብ ሰኔ 1 ቀን 2012 ዓ.ም በጠ/ሚ ቢሮ በተካሄደው መድረክ ማቅረቡን ድርጅታችን ተገንዝቧል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ላለፉት ሁለት ወራት ከፍተኛ ጥላቻ ባላቸው አደረጃጀቶች፣ ግለሰቦችና የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች በሚደግሟቸው ማህበራዊ ሚዲያ ገፆች በኩል በዎላይታ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጥላቻ ዘመቻ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ድርጅታችን እየተደረገ ያለው ዘመቻ አከባቢውን ወደ ሌላ ቀውስ ሊያመራ የሚችል መሆኑን በመገንዘብ ያቀረብነውን የሠላም ጥሪ ወደ ጎን በመተው ዘመቻው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ዘመቻው በጥቂት ጠባብ ፍላጎት ባላቸው ግለሰቦችና የከሰሩ ካድሬዎች ለፖለቲካ ንግድ ፍጆታ ለማዋል ታስቦ እንደሆነ በመመልት በራሱ መንገድ ሕዝቡና የመንግስት መዋቅር እንደሚያስቆመው ተገምቶ ነበር፡፡ ሆኖም የጥላቻ ዘመቻው መዋቅራዊ ይዘት ያለው እና በመንግሥት ሹመኞች መሪነት በተቀናጀ ሁኔታ እየተካሄደ ያለ መሆኑን የኮሚቴው ሪፖርት በቀረበበት ስብሰባ ላይ የአጎራባች ዞኖች ተወካዮች በግላጭ ከተናገሩት አስነዋሪ ከሆነው የጥላቻ ንግግራቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይህም የሃሰት እና ጥላቻ ህግ በተደነገገበት ወቅት መሆኑም መንግስት እንደ ሁለተኛ ዜጎች የሚቆጥራቸው ለመኖራቸው አመላካች ነው፡፡

ከላይ በተዘረዘሩ አንገብጋቢ ሁኔታዎች መነሻነት የድርጅታችን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በጥልቀት በመወያየት የሚከተለውን ባለ አራት ነጥብ መግለጫ አውጥቷል፡፡

  1. የዎላይታ ሕዝብ ከመነሻው ጀምሮ ያቀረበው ራሱን በክልል የማደራጀት ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47/2 ድንጋጌ መሠረት ሕገ-መንግሥታዊ ምላሽ የሚሰጠው እንጅ በጥናት የሚሰጠው ፖለቲካዊ ውሣኔ ሕጋዊ እና ቅቡል አይደለም፡፡ ከህዝቡ ፍላጎት ውጪ ከሌሎች ብሔሮች ጋር ዳግም በማዳበል በሕዝባችን መስዋዕትነት ድባቅ የተመታውና የወደቀውን ዎጋጎዳ መልሶ ለማደራጀት የተከሄደበት ሁኔታ ፈፅሞ የዎላይታ ሕዝብ ፍላጎት አለመሆኑ ይሰመርበት፡፡ በመሆኑም ለሕዝብ ሉዓላዊነት፣ ለፍትሐዊና ሕጋዊ ጥያቄ ክብር በመስጠት ሕዝባችን በክልል የመደራጀት ጥያቄ የቀረበለት ፌደሬሽን ምክር ቤት ሕዝበ ውሳኔ እንዲካድበት ለምርጫ ቦርድ በአስቸኳይ እንዲመራለት ድርጅታችን በድጋሚ አጥብቆ ይጠይቃል፡፡
  2. በጭፍን ጥላቻ የሰከሩ በአጎራባች አከባቢዎች የሚገኙ አንዳንድ ልሂቃን፣ የከሰሩ ፖለቲከኞችና አመራሮች በሕዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን አብሮነትና መልካም ጉርብትና በመካድ፣የውሸት ትርክት በመፍጠር ከፌዴራል እስከ ወረዳ ድረስ የረዘመ መዋቅር በመዘርጋት የዎላይታን ሕዝብ ክብር በሚያጎድፍ መንገድ እያካሄዱ ካሉት የጥላቻ ዘመቻ እንዲታቀቡ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡ ለሕዝባቸው የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የፖለቲካ ጥያቄ ምላሽ መስጠት እና ችግሮቻቸውን መፍታት ሲያቅታቸው የሕዝባቸውን የውስጥ አጀንዳ ወደ ውጭ የማስቀየስ አደገኛ አካሄድ ሕዝቡ እውነቱን በተረዳ ጊዜ ማምለጫ የሚያሳጣ መሆኑን በመገንዘብ ጊዜ እና ጉልበታቸውን ጥላቻ ከመዝራት ይልቅ ለሕዝባቸው ሐቀኛ ጥያቄ መልስ ለመስጠት እንዲያውሉት እናሳስባለን፡፡ በሕዝቦች መካከል የነበረው ዘመን ተሻጋሪ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር በጥቂት ልሂቃንና ኪሣራ በገጠማቸው ተስፈኛ የፖለቲካ ነጋዴዎች የማይናጋ መሆኑን በመገንዘብ ከጥፋት ተግባራቸው በመመለስ የቀረቻቸውን አቅም ለሠላም ግንባታ እንዲያውሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ መንግሥትም ዕኩይ ዓላማ ባነገቡ በጸረ-ሰላም አካላት ላይ በአፋጣኝ ሕጋዊ የእርምት እርምጃ በመውሰድ የጥፋት ተልዕኳቸውን በአስቸኳይ እንዲገታ አጥብቀን እየጠየቅን ይህ ባለመፈጸሙ በሴረኞች ተግባር ችግር ቢፈጠር ህዝባችን ህልውናውን ለማስከበር ያመነበትን አማራጭ መንገድ ለመከተል የሚገደድ መሆኑ ከወዲሁ ግልጽ ይሁን፡፡
  3. አመታትን ያስቆጠረውን የዎላይታን ሕዝብ ሕገ-መንግስታዊ ጥያቄ ለማሰናከል በተደራጀ ሁኔታ እንቅፋት የመፍጠር ሥራ አሁንም ተጠናክሮ እንደ ቀጠለ ድርጅታችን ይገነዘባል፡፡ ስለዚህም በመካከላችን ያሉ የአመለካከት ልዩነቶችን ለጊዜው በማቆዬት በሕዝባችን ልዕልና ላይ የተጋረጠውን ይህንን አደጋ በጋራ መቋቋም የህልውና ጉዳይ ነው በማለት ድርጅታችን አቋም ይዟል፡፡ በመሆኑም የዎላይታ ዞን አስተዳደር በተለያዬ ደረጃ ባሉ መዋቅሮች የሚሰሩ የህዝብ ተወካዮች፣የመንግሥት ተሸሚዎች ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የመብት ታጋዮችንና የሀገር ሽማግሌዎችን በመጥራት ለኮቪድ-19 ጥንቃቄ በሚደረግበት ሁኔታ አስቸኳይ የጋራ ውይይት ተካሂዶ ለቀጣይ ትግል በጋራ የምንቆምበት መደላድል ለመፍጠር መድረክ እንዲመቻች ድርጅታችን አጥብቆ ይጠይቃል፡፡
  4. የተከበራችሁ የዎላይታ ተወላጆች እና ወዳጆች፣ የድርጅታችን አባላት እና ደጋፊዎች ፣ የዎላይታ ዬላጋ፣ የዞኑ ፀጥታ አካላትና መላው ሕዝብ የጥፋት ትልዕኮ ባነገቡ አካላት በተለያዬ መልክ ለሚፈፀሙ ትንኮሳዎች ምላሽ በመንፈግ፣ በውስጡ ላሉ ብሄሮች ሁሉ ተገቢውን ጥበቃና የተለመደውን ፍቅር በመለገስ የጥላቻ ነጋሪት ጎሳሚዎችን በማሳፈር ለሕዝቦች አንድነት፣ መተሳሰብና አብሮነት መጠናከር ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ የተከበረ ህዝባዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

በሐቀኛ ሕዝባዊ ትግል የዎላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምሥረታ እውን ይሆናል!

ዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ /ዎብን/

ሰኔ 04 ቀን 2012 ዓ.ም

ዎላይታ ሶዶ

wolaitatoday
Wolaitatoday
wolaitatoday
Wolaitatoday
wolaitatoday
wolaitatoday
wolaitatoday