የመብት ተሟጋቾች እስርና አፈናው በወላይታ እንደቀጠለ ነው
ነሐሴ 29 2012ዓ.ም
በቅርቡ በብልፅግና ፓርቲ የመንግስት አስተዳደር መፈንቅል በተደረገው ወላይታ የመብት ተሟጋቾች እስርና አፈናው ተባብሶ እንደቀጠለው ነዋሪዎች በምሬት እየገለፁ ይገኛሉ፤ ወላይታ ሚዲያ ሐውስ ያነጋገራቸው እማኞች እንዳስታወቁት በመንግስት እየተፈፀመ ያለው የሀይል እርምጃ አከባቢውን የጦር ቀጠና ያስመሰለ ሲሆን የደቡብ ክልል ልዩ ሐይል አባላት 2 ሴት ታዳጊዎች ላይ የአስገድዶ መድፈር ድርጊት እንደፈፀሙ ከጤና ተቋማት የደረሰን ማስረጃ ያመላክታል፡፡ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ጥቃት የደረሰባቸው ታዳጊዎች ስነ ልቦና ለመጠበቅ ወላይታ ሚዲያ ሐውስ የታዳጊዎችን ማንነት ይፋ ከማድረግ የተቆጠበ ሲሆን ድርጊቱ ልባቸውን እንደሰበረ የታዳጊዎች ወላጆች አስታውቀዋል፡፡
በወላይታ የሰብዓዊ መብት ታጋይና የሙዝቃ አቀንቃኝ የሆነው ወጣት ቡቺ የብልፅግናው መንግስት ለእስር ግልጋሎት እየተጠቀመ በሚገኘው የወላይታ ሶዶ ግብርና ኮሌጅ ባጋጠመው የምግብ መመረዝ የጤና እክል የተነሳ ወደ ሕክምና ተቋም የተወሰደ ሲሆን ግብርና ኮሌጁ ያሉ ታሳሪዎችን ለመጠየቅ ወደ ስፍራው ያቀኑ የአይዳሚያ የሴቶች ንቅናቄ አመራር አባላት ገሊላ ኃይሉ እና ጄሪ ሳሙኤል በሠራዊቱ ታፍነው በእስር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ በቅርቡ በብልፅግና ፓርቲ የመንግስት አስተዳደር መፈንቅል የዞኑ አስተዳደር የነበሩትን አቶ ዳጋቶ ኩምቤን የተኩት ዶ/ር እንድሪያስ ጌታ የግብርና ኮለጁ ኃላፊ የነበሩ ሲሆን የተቋሙ የወቅታዊው አገልግሎት ላይ ጥያቄዎች እየተነሱ ይገኛል፡፡
የወላይታ ሕዝብ ለጠየቀው የክልል አስተዳደራዊ መዋቅር ጥያቄ ተከትሎ በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የሚመራው መንግስት በወሰደው ኃላፊነት በጎደለው ኢ-ሰብዓዊ እርምጃ የ36 ሰላማዊ ዜጎች ህይወት በመቅጠፍ 171 ዜጎች ላይ የአካል መጉደል ጉዳት መድረሱ ይታወቃል፡፡