የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ለመስጠት ቃል የገባውን ከሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ አጠፈ፡፡
ነሐሴ 26 2012ዓ.ም
የዓለም ባንክ የኮሮና ቫይረስ ጫናን ለመከላከልና ለሰብዓዊ ስራዎች ከሚውሉ ጉዳዮች ውጭ ለኢትዮጵያ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሀ ግብር ሊያቀርበው የነበረውን ከሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ (ብድርና ድጎማ) እንደማያቀርብና ከኢትዮጵያ ጋር በዚህ ረገድ የገባውን ስምምነት እንዳቋረጠ ከምንጮቹ አረጋግጧል። የአለም ባንክ እርምጃውን የወሰደው ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሀ ግብሮችን ቃል በገባችው መሰረት በሙሉ ይዘቱ አልተገበረችም በሚል ነው።
ኢትዮጵያ ከዚህ አመት ወይም 2012 አ.ም ሲጀመር አንስቶ ለሶስት አመታት ተግባራዊ የምታደርገውን የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን ይፋ ስታደርግ ያስፈልገኛል ካለችው አስር ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ውስጥ ከአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ጋር የወጪውን ስልሳ በመቶ እንደሚሸፍን ቃል የገባው የዓለም ባንክ ነው። የዓለም ባንክ እስከ ሶስት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚደርስን ገንዘብ በብድር ለማቅረብ ተስማምቶ ነበር።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በሀገር ውስጥ በኢኮኖሚ ተቋማት ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ እና አሁንም በኢኮኖሚ ማሻሻያ ሂደት ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ሁኔታው ከባድ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል ስጋታቸውን እየገለጹ መሆናቸውን ጭምር ዋዜማ ራዲዮ ዘግቧል።
ባለፈው ሳምንት አሜሪካ ለኢትዮጵያ ልትሰጥ የነበረው 130 ሚሊየን ዶላርን እንዲዘገይ መወሰኗ ይታወቃል፡፡