የብር በዶላር ምንዛሪ ተመን ከተገመተው በላይ አሽቆልቁሏል
ነሐሴ 25 2012ዓ.ም
የብር በዶላር ምንዛሪ ተመን ከተገመተው በላይ አሽቆልቁሏል፤ ከሌሎች ሀገራት የመገበያያ ገንዘቦች አንጻርም ልዩነቱ በፍጥነት እየሰፋ ነው፡፡
መንግስት የብር በዶላር ምንዛሪ ተመንን በዝግታ ለማዳከም ከለጋሾች ጋር ተስማምቶ ነበር። ይሁን እንጂ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በገጠመው ፈተና ብር በራሱ ጊዜ ለጋሾች ካስቀመጡት ተመን አሽቆልቁሏል። የለጋሾች ጫናና ሀገራዊ የኢኮኖሚ ፈተናው ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዳደር ራስ ምታት ሆኖ መሰንበቱ አይቀሬ እየሆነ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት ከአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም : አይኤምኤፍ : እና የአለም ባንክ ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ እንዲያገኝ ያስቻለውን የሶስት አመት የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሲያዘጋጅ አንዱ ተቀብሎት ፈርሞበት የነበረው ቅድመ ሁኔታ የሀገሪቱን መገበያያ ብር የውጭ ምንዛሬ ተመን በፍጥነት እንዲያዳክም ፣ በጊዜ ሂደት ደግሞ የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን ማድረግ የሚለው ነበር።
የይፋዊ እና የጥቁር ገበያ የምንዛሬ ተመን ዋጋን ማቀራረብም ብርን ከማዳከም የሚጠበቅ ውጤት ቢሆንም በኢትዮጵያ ይሄም አልተሳካም። በጥቁር ገበያ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ45 ብር አካባቢ ነው እየተመነዘረ ያለው። ከመደበኛው ገበያ የዘጠኝ ብር ልዩነት አለው። ይህም የሆነው በመደበኛው ገበያ ብርን በማዳከም የሚጠበቀው የውጭ ምንዛሬ ግኝት ባለመሳካቱ ነው።
መንግስት በብሄራዊ ባንክ በኩል እተገብራቸዋለሁ የሚላቸው አሰራሮችም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ አሁን ባለበት ሁኔታ በዚህ ቀን ሊተገበር ይችላል ተብሎ መገመት የማይቻል እና መንግስት ለአለማቀፍ የገንዘብ ተቋማት ቃል ስለገባ ብቻ የሚናገረው እንደሆነ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ለዋዜማ ራዲዮ ገልጸዋል። (ምንጭ፡-ዋዜማ ራዲዮ)