“በአስቸኳይ በኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ይቋቋም፤ ወላይታ በክልል ባልተዋቀረበት የሚደረግ ምርጫ ተቀባይነት የለውም”
በወላይታ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች (ታህሳስ 5 2013ዓ.ም)
የኢትዮጵያ ስድስተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ከመካሄዱ አስቀድሞ የወላይታ የክልል መዋቅር እና ሀገር አቀፍ የቤቶችና ሕዝብ ቆጠራ መካሄድ እንዳለበት በወላይታ የተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲካ አመራሮች አስታወቁ፡፡ በቅርቡ በስድስተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ አካሄድ ላይ ያለውን አቋም ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ያስታወቁት አመራሮቹ አገርቱ ከገጠማት የፖለቲካ ቀውስ ለመውጣት ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሳተፈ የሽግግር መንግስት መመስረት ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ ጭምር ገልፀዋል፡፡
“በወላይታ የህዝብ ተወካይ ሆነው ሊመረጡ የሚችሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንና አባላትን በማሰርና በማሳሳድ ብልፅግና ፓርቲ አካሂዳለው የሚለው ሀገራዊ ምርጫ የራስን የበላይነት በማንገሥና ሌሎችን በማግለል ላይ ያነጣጠረ ከመሆኑም በላይ ሀገሪቱን ወደ ሌላ ቀዉስ የሚከት ነው” ሲሉ አመራሮቹ አስጠንቅቀዋል፡፡
እንደ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ ገለፃ መቅደም ያለበት የቤቶችና ሕዝብ ቆጠራ መሆኑ እየታወቀ ምርጫውን ለማጭበርብር እንዲመች ስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ሁለት ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች ቆጠራውን ማሸጋገሩን በወቅቱ ተቃዉመናል ብለዋል፤ የቤቶችና ሕዝብ ቆጠራ ለሚዛናዊ የሀብት ሥርጭትና ክፍፍል እንዲሁም ሚዛን ለጠበቀ የተፋጠነ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ዕድገቱን በታቀደና በተቀናጄ መንገድ ለመምራት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተው “የሕዝብ ቆጠራ የሕዝቡን ቁጥር ለማወቅ የሚደረግ አይደለም” ሲሉ የመንግስትን አሰራር ኮንነዋል::
በወላይታ የመንግስት ፀጥታ አካላት በወሰዱት ኢ-ሰብዓዊ እርምጃ 36 ሰዎችን ለሞት ከ 172 ሰው በላይ ለአካል ጉዳት የተዳረጉበት ወንጀል የሚመረምር ገልለተኛ አካል እንዲቋቋም እና የደቡብ ብሄር ብሔረሰቦች ክልል አስተዳደር መንግስታዊ የሀላፊነት ጊዜው ያበቃ በመሆኑ ተዓማኒነት ያለው ምርጫን ለማካሄድ እንዲቻል የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ለብሔር ብሔረሰቦች ጥሪ እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል፡፡
የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ የወላይታ የክልል አወቃቀር ለድርድር የማይቀርብና ከክልል አወቃቀር ጋር በተያያዘ የብልፅግና ፓርቲም ሆነ አመራሮቹ የሚወስኑት ማናቸውም ውሳኔዎች ተቀባይነት የሌላቸው በመሆኑ ለወላይታ ሕዝብ የክልል መዋቅራዊ አስተዳደር የፌዴራል መንግስት ችሮታ ሳይሆን መብት እንደሆነ ታውቆ ለተግባራዊነቱ የቀድሞው የዞን ምክር ቤት ያቋቋመው የክልል ምክር ቤት አመቻች ኮሚቴ ስራም እንጀመር ሲሉ አሳስበዋል፡፡