“ልጄ ታናሽ ወንድሙን ለመፈለግ በወጣበት ነው የተገደለው” የሶዶው አባት ከወላይታ
ነሐሴ 07 2012ዓ.ም (ቢቢሲ አማሪኛ)
በወላይታው አለመረጋጋት የመጀመሪያ ልጃቸውን ተስፋዬን የተነጠቁት አባት አቶ ተፈሪ ሰይፉ ልጃቸው ታናሽ ወንድሙን ሊፈልግ እንደወጣ መቅረቱን በሐዘን ተሰብረው ተናግረዋል።
ቢቢሲ በትናንትናው ዕለት ባናገራቸው ወቅት አቶ ተፈሪ በበኩር ልጃቸው ሐዘን ላይ የነበሩ ሲሆን የሚኮሩበትን ልጃቸው ማጣታቸው ልባቸውን እንደሰበረው በምሬት ተናግረዋል።
ስለ 28 ዓመቱ ልጃቸው ተስፋዬም ሲያወሱ፤ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ በቢዝነስ ማኔጅመንት በከፍተኛ ማዕረግ ተመርቆም ኢንተርፕራይዝ ልማት በሚባል ድርጅትም ተቀጥሮ ይሰራ እንደነበር ገልጸዋል።
ለእረፍት ቤተሰቦቹን ሊጠይቅ መጥቶ ባለበት ወቅት እሁድ ምሽት ከተማው ውስጥ የጥይት ተኩስ በተከፈተበት ጊዜ ታናሽ ወንድሙ ቤት ስላልነበረ እሱን ፍለጋም ወጣ።
አቶ ተፈሪ እንደሚሉት ወንድሙን ወደቤት ለመመለስ የወጣው ተስፋዬ ላይመለስ በጥይት ተመትቶ ተገደለ።
እንደወጣ በቀረው ልጃቸው ሐዘን ክፉኛ የተሰበሩት ሳግ በሚቆራርጠው ድምጽ “ልጄ ለሞት ተዳርጓል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ሲቪል ነው፣ መሳሪያ አልታጠቀም፣ ምንም አያውቅም፣ ልጄ ባዶ እጁን ታናሽ ወንድሙን ለመፈለግ እንደወጣ ቀረ” ብለዋል።
የወላይታ ሕዝብ የክልልነት ጥያቄን ካነሰ ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ እንደሆነው የሚናገሩት አባት ያ ምላሽ ባለገኘበት ወቅት በተጨማሪ አመራሮቹ መታሰራቸው ቁጣን ቀስቅሷል።
በዚህም ሳቢያ ወጣቶች የታሰሩት ሰዎች ይፈቱ በሚልም እሁድ ዕለት ከተሞቹ ላይ ተቃውሞ ማሰማት መጀመራቸውን ጠቅሰው ልጃቸው ተስፋዬም ወንድሙን ከሰልፈኞቹ መካከል ፍለጋ ለመፈለግ ሲሞክር ነው የተገደለው።
“ልጁ አንድ ነገር እንዳይደርስበት፣ ጥይትም እንዳያገኘው በሚል ይዤው ልምጣ ብሎ ነው የወጣው። አካሄዱ ለተቃውሞ ሰልፍ አልነበረም፤ ትንሽ ወንድሙ በጥይት እንዳይመታ ለማምጣት ነበር” ይላሉ አባት አቶ ተፈሪ።
አለመረጋጋቱ ከተከሰተ በኋላ ተስፋዬ ወንድሙን ሊፈልግ ሲወጣም የተጨነቁት አባት “ተው አትሂድ ብዬው ነበር” ይላሉ።
በጥይት የመመታቱንም መርዶ የሰሙት ከጓደኛቸው በስልክ ነው ነው “ልጅህ በጥይት ተመትቷል፤ ሆስፒታል ተወስዷል ይባላል ተከታተለው። እኔ መውጣት አልቻልኩም ተብሎ ተደወለልኝ።”
እሳቸውም በዜናው ደንግጠው ወደ ሶዶ ሆስፒታል በፍጥነት አቀኑ። እዚያም በደረሱበት ወቅት የኮሮናቫይረስ ታማሚዎች ስላሉ አናስገባም አሏቸው።
“እዚያ ሰው መግባትም ሆነ መውጣት አይችልም አሉኝ” ክርስቲያን ሆስፒታልም እንዲሞክሩ ነገሯቸው።
አቶ ተፈሪ የተባሉትን ሰምተው ወደ ክርስቲያን ሆስፒታል ሄዱ። ክርስቲያን ሆስፒታል ውስጥ ፅኑ ህሙማን ክትትል ወደሚያገኙበት ክፍል እንደገባና በአምስት ጥይት እንደተመታም ተረዱ።
ሆዱ ውስጥ ያለውንም ጥይት ለማውጣት ቀዶ ጥገናም እየተካሄደ ነበር። ቀዶ ጥገናውም ሳይጠናቀቅ ህይወቱ አለፈ “ፅኑ ህምሙማን ክፍል ውስጥ እያለ አይኑን ሳላየው ልጄ ደክሞ ሞተ” የሚሉት አባት ከመሞቱ በፊትም ልጄ ከምን ደረሰ? እያሉ የሆስፒታሉን ሠራተኞችም እየወተወቱ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ዶክተሮቹም አባቱን እንዴት እንደሚያረዷቸው ለመንገር ዘገዩ፤ ቆይተው ከሁለት ሰዓት በኋላም ራሳቸው በቀጥታ ሳይሆን “በሌላ ሰው በኩል ልጄ እንደሞተ ነገሩኝ” ይላሉ።
የሚረዷቸውን ሰዎችም ጠርተው መኪናም ለምነው አስከሬኑን አመሻሹ ላይ ወደቤታቸው ወሰዱ። ሌላኛው ልጃቸው ግን ምንም ጉዳት ሳይደርስበት ወደቤት መመለሱንም የአምስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ተፈሪ ይናገራሉ።
“ከታላቅ ልጄ በላይ፣ ምንም ካላዬው ልጄ፣ ካላገባ፣ ልጅ ካልወለደ፤ እንዲሁ ያለ ስም የሚሞት ልጅ ያሳዝናል” የሚሉት አቶ ተፈሪ፤ ልጃቸው ዩኒቨርስቲ ጨርሶ ለፍቶ፣ ሥራ ይዞ ትዳር ሳይዝ ወግ ማዕረጉን ሳያዩ እንደወጣ መቅረቱ የእግር እሳት ሆኖባቸው ሐዘናቸውን አበርትቶባቸዋል።
“እንዲህ አይነት ሁኔታ በጥይት ተቃጥሎ ሲሞት፣ አምስት ጥይት ተተኩሶበት ሲገደል እጅግ የሚያስመርር ነው” የሚሉት አባት “አዝናለሁ፣ እጅግ አዝናለሁ፤ ቤተሰብ፣ ዘመድ አዝነናል” ሲሉ ሐዘናቸው የእሳቸው ብቻ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
እንዴት ሞተ ብሎ የሚጠይቅ የመንግሥት አካል አለመኖሩም ቁጭት እንደፈጠረባቸው ለቢቢሲ አዋይተዋል።
ከሰሞኑ በወላይታ በነበረው አለመረጋጋት 16 ያህል ሰዎች መሞታቸውን ቢቢሲ ያናገራቸው የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታል ሐኪም የሆኑት ዶ/ር መብራቱ ጪሻ ከተለያዩ ሆስፒታሎችና ከአካባቢው የተጠናቀሩ መረጃዎች እንደሚያሳዩ የተናገሩ ሲሆን ልጃቸውን በዚህ አለመረጋጋት የተነጠቁት አባት አቶ ተፈሪ ሌሎች አምስት ሰዎችም መገደላቸውን ሰምተዋል።
ዶ/ር መብራቱ ጪሻ ጨምረውም በአካባቢው በነበረው አለመረጋጋት ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሕክምና ተቋማት የመጡት 49 ሰዎች ላይ ጉዳት የደረሰው በጥይት ተመትተው መሆኑን አመልክተዋል።
ዞኑን በክልልነት ለማደራጀት ከተቋቋመው ሴክሬታሪያት ስብሰባ ተሳታፊ የነበሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሕግ ባለሙያዎችና የአገር ሽማግሌዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ ነው ወላይታ ውስጥ ችግሩ የተከሰተው።
የወላይታ ዞን ምክር ቤት ሰኔ 15/2012 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እንዲቋቋም ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
የክልሉን መንግሥት ለማደራጀት የሚያስችል ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤትም እንዲቋቋምና የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እንዲከናወኑም በዚሁ ወቅት ወስኖ ነበር።
የወላይታ ዞን ከደቡብ ክልል በመውጣት እራሱን ቻለ ክልል ለመሆን ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ከዚህ ጋር በተያያዘ በተከሰተ አለመረጋጋት ነው ተስፋዬ ተፈሪን ጨምሮ ከ15 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሕይወት ያለፈው።