የወላይታ አስተዳዳሪን ጨምሮ 19 ሰዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ
ነሐሴ 06 2012ዓ.ም (ዶቸ ቬለን)
ባለፈው እሁድ በሶዶ ከተማ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ መካከል የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ ዳጋቶ ኩምቤን ጨምሮ 19 ሰዎች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ገደማ የዘለቀው ችሎት ለነገ 9 ሰዓት መቀጠሩን ዶይቼ ቬለ አረጋግጧል። በቦዲቲ ተቃውሞ ለአራተኛ ቀን የቀጠለ ሲሆን የከተማዋ ነዋሪዎች ዛሬ ብቻ ሁለት ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዳጋቶ ኩምቤን ጨምሮ ባለፈው እሁድ በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ባለሥልጣናት እና ልሒቃን ፍርድ ቤት ቀረቡ። ባለሥልጣናቱ ከታሰሩ በኋላ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በቦዲቲ ከተማ ለአራተኛ ቀን መቀጠሉን የዐይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል።
የዞኑ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ አክቲቪስቶች፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ ከተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ የወላይታ ልሒቃን በቁጥጥር ሥር የዋሉት ባለፈው ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. በሶዶ ከተማ በሚገኘው ጉተራ አዳራሽ ነበር።
ጉዳዩን በቅርበት በመከታተል ላይ የሚገኙ አንድ የሶዶ ነዋሪ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል አስራ ዘጠኝ ሰዎች ወላይታ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ መቅረባቸውን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። የሶዶው ነዋሪ እንዳሉት የፍርድ ቤቱ ውሎ እስከ ምሽት አንድ ሰዓት ገደማ የዘለቀ ነው። “በሰላማዊ መንገድ፣ በጥሩ ኹኔታ ገብተው ተስተናግደው እንደወጡ በምስላቸው ማየት እንችላለን እንጂ መነጋገር አልቻልንም” ሲሉ የሶዶው ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን 28 የዞኑን ባለሥልጣናትን ጨምሮ 178 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን በትናንትናው ዕለት ገልጿል። ጉዳዩን ሲከታተሉ የዋሉት የሶዶ ነዋሪ እንዳሉት ግን ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት ግን አስራ ዘጠኝ ብቻ ናቸው።
“የዞኑን ዋና አስተዳዳሪ ጨምሮ በድምር አስራ ዘጠኝ ሰዎች ናቸው የቀረቡት። እከሌ እከሌ ብለን በስም መዘርዘር ባንችልም ከዋና አስተዳዳሪው ጀምሮ አስራ ዘጠኝ ሰዎች ናቸው ፍርድ ቤት የቀረቡት” ብለዋል።
የተቃዋሚው የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ አባላትን ጨምሮ የተለያዩ የዞኑ ነዋሪዎች በማሕበራዊ ድረ-ገፆች ባሰራጩት መልዕክት ባለፈው እሁድ የታሰሩ ሰዎች ፍርድ ቤት መቅረባቸውን አረጋግጠዋል። በዛሬው የፍርድ ቤት ሒደት የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤም ሆኑ አብረዋቸው የቀረቡ በምን እንደተጠረጠሩ በይፋ የተገለጸ ነገር የለም። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የሶዶ ነዋሪም ዝርዝር መረጃ ማግኘት እንዳልቻሉ አስረድተዋል።
“ጥያቄው ምን እንደሆነም በግልፅ የምናውቀው ነገር የለም። በቀላሉ መገናኘት አልተቻለም። የፍርድ ሒደቱ፣ ለእነሱ የቀረበው ጥያቄ፣ እነሱ የመለሱትን በግልጽ ማወቅ የሚቻልበት ሁኔታ አልነበረም” ያሉት የሶዶ ነዋሪ የዛሬው ችሎት ተቋርጦ ለነገ ነሐሴ 7 ቀን 2012 ዓ.ም. 9 ሰዓት መቀጠሩን ገልጸዋል።
የጸጥታ ኃይሎች ለወላይታ ክልል መመሥረት ግፊት በማድረግ ላይ የሚገኙ ልሒቃንን ማሰራቸው የቀሰቀሰው ተቃውሞ ዛሬም በቦዲቲ ለአራተኛ ቀን መቀጠሉን ከከተማው ነዋሪዎች ዶይቼ ቬለ አረጋግጧል። ከአዲስ አበባ 295 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቦዲቲ “ሰው እየወጣ የታሰሩ ወንድሞቻችን፤ የታሰሩ ልጆቻችን ይፈቱ የሚለውን እየጠየቀ ነው” የሚሉ የከተማዋ ነዋሪ ከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ መኖሩንም ገልጸዋል።
በቦዲቲ ከተማ አቅራቢያ ሁለት ሰዎች ከጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት መገደላቸውን እኚሁ የከተማዋ ነዋሪ ተናግረዋል። “ከቦዲቲ አምስት ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ ጋቼኖ በምትባል ከተማ ላይ ሁለት ሰው ሞቷል” ይበሉ እንጂ ዶይቼ ቬለ ከሕክምና እና ከመንግሥት ተቋማት ለማረጋገጥ ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት ሳይሰምር ቀርቷል። በቦዲቲ ከተማ ከባለፈው እሁድ ጀምሮ እስከ ትናንት ድረስ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን የሕክምና ተቋማት ባለሙያዎች፣ የከተማዋ ነዋሪዎች እና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናግረው ነበር።
በዛሬው ዕለት በቦዲቲ መንገድ መዘጋቱን፣ የተሽከርካሪዎች መስተዋቶች በተቃዋሚዎች መሰባበሩን እንስቃሴም መገታቱን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል። ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የመንግሥት ሰራተኛ “እኛ ራሱ የምንበላው ነገር አጥተናል። አንድም ነገር ክፍት ነገር የለም። ሆቴል ዝግ ነው። አስፓልት ላይ ሰው መራመድ አይችልም። መከላከያ ብቻ ነው ያለው” ሲሉ የከተማዋን ኹኔታ አስረድተዋል።
ካለፉት ሁለት ቀናት አኳያ በአንጻራዊነት የመረጋጋት ምልክት እንደሚታይባት የተናገሩ ሌላ የቦዲቲ ነዋሪ “ውስጥ ለውስጥ አንዳንድ ሱቆች ተከፍተዋል፤ መንገድ ዳር ያሉ ንግድ ቤቶች ዝግ ናቸው” ብለዋል። የዐይን እማኙ ዛሬም በከተማው ተቃውሞ እንደነበር “አልተረጋጋም፤ ዛሬም በትንሹ እንቅስቃሴ ነበር” ሲሉ አስረድተዋል።
የወላይታ መቀመጫ የሆነችው ሶዶ ከተማ “ጸጥ ረጭ” ብትልም በነዋሪዎቹ ዘንድ ሥጋት እንዳለ የፍርድ ቤቱን ጉዳይ የሚከታተሉ የዐይን እማኝ ተናግረዋል። “ጸጥታው ሰላም ነው። ሕዝቡ ግን አመራሮቻችን ታሰሩንብ በሚል ሥጋት ከተማው ጸጥ ረጭ ብሏል። ብዙ እንቅስቃሴ አይታይም” ብለዋል።