በወላይታ 178 ሰዎች ታስረዋል – የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን
ነሐሴ 05 2012ዓ.ም (ዶይቸ ቬለን)
በወላይታ 28 የዞን አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ጨምሮ 178 ሰዎች መታሰራቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ። የጸጥታ ኃይሎች እርምጃ “ቀድሞም የነበረ ውጥረቶችን ያባብሱ እንደሆን እንጂ መፍትሔ አይሆኑም” ብሏል።
በወላይታ 28 የዞን አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ጨምሮ 178 ሰዎች መታሰራቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ። ኮሚሽኑ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ የጸጥታ አስከባሪዎች የኃይል እርምጃ ከመውሰድ እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በወላይታ ዞን ተቃውሞ የተቀሰቀሰው “በፌዴሬሽኑ ውስጥ አዲስ የክልል መንግሥት መመስረትን በተናጠል ለማወጅ በፈለጉ በርካታ ከፍተኛ የዞኑ ባለስልጣናት እስርን ተከትሎ” ለመሆኑ ከተለያዩ ምንጮች መረጃ አግኝቺያለሁ ብሏል። እስካሁን በትክክል ባለፈው ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. በሶዶ ከተማ በሚገኘው ጉተራ አዳራሽ የተሰበሰቡ የዞኑ ልሒቃን የወላይታ ክልላዊ መንግሥትን በተናጠል ሊያውጁ እንደነበር የታወቀ ነገር የለም።
ኮሚሽኑ በጸጥታ አስከባሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ 178 ሰዎች በወላይታ ሶዶ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ እንደሚገኙ ገልጿል። ከእነዚህ መካከል 28ቱ የዞኑ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ናቸው።
የልሒቃኑ እስር በቀሰቀሰው ተቃውሞ “በዞኑ ዋና ከተማ በሶዶ አንድ ሰው እንዲሁም በቦዲቲ አምስት ሰዎች መሞታቸውን” የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጿል።
የወላይታ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን የጸጥታ አስከባሪዎች የወሰዱት እርምጃ ከተጠቀሰው እጅግ የላቀ ነው የሚል ዕምነት አላቸው። የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዱዓለም ታደሰ የሟቾች ቁጥር 21 መድረሱን እንዳረጋገጡ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። አቶ አንዱዓለም እንዳሉት ከ105 በላይ ሰዎች ቆስለዋል።
በዛሬው መግለጫው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን “በወላይታ ዞን አንዳንድ ከተሞች ነሐሴ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በተደረጉት ተቃውሞዎች የፀጥታ ኃይሎች በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ የወሰዱት እርምጃ ተመጣጣኝነት አጠያያቂ ነው” ብሏል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ቃል አቀባይ አሮን ማሾ “ሰልፈኞች አሟሟትን እና የጸጥታ ኃይሎች የኃይል አጠቃቀምን አስመልክቶ ፈጣን ምርመራ” ያስፈልጋል ማለታቸውን በኮሚሽኑ የፌስቡክ ገፅ የተሰራጨው መግለጫ ይጠቁማል።
አሮን “የፀጥታ ኃይሎች ሰላማዊ ሰልፎችን በሚቆጣጠሩበት ወቅት የሞት አደጋን የሚያስከትል የኃይል እርምጃ ከመውሰድ ሊቆጠቡ ይገባል፤ እንደነዚህ ያሉ እርምጃዎች ቀድሞም የነበረ ውጥረትን ያባብሱ እንደሆን እንጂ መፍትሔ አይሆኑም” ብለዋል።