በትግራይ ውጊያ እንዲሰማሩ ለተሰናባች የመከላከያ ሰራዊት አባላት በነፍስ ወከፍ 60,000 ብር ማባበያ እና የመኖሪያ ቤት መሥራያ ቦታ እንደሚሰጣቸው በብልፅግናው አመራር ቃል ተገባ፡፡
ህዳር 14 2013ዓ.ም
ዛሬ በወላይታ ሶዶ በሚገኘው የጉታራ ሁለገብ ማዕከል የብልፅገና አመራሮች በወላይታ ለሚገኙ በክብር ተሰናባች የመከላከያ ሰራዊት አባላት ብልፅግና በትግራይ ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ላይ እያካሄደ ለሚገኘው ጦርነት ለመዝመት ፈቃደኛ ለሆኑ ተሰናባች የመከላከያ ሰራዊት አባላት በነፍስ ወከፍ 60,000 ብር ማባበያ እና የመኖሪያ ቤት መሥራያ ቦታ እንደሚሰጣቸው ቃል ተገባ፡፡
በስብሰባው ላይ የተገኙ በክብር ተሰናባች የመከላከያ ሠራዊት አባላት ለወላይታ ሚዲያ ሐውስ እንዳረጋገጡት ስብሰባውን በመምራት ላይ ለሚገኙ የብልፅግና አመራሮች የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርቦላቸዋል፡፡ ተሰናባች የመከላከያ ሰራዊት አባላት “በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት መፈታት ያለበት በውይይት ነው”፣ “እኛ የሰለጠንነው ለሀገር እንጂ ለፖለቲካ ፓርቲ በመወገን መስማማት ያልቻሉትን ለመውጋት አይደለም” ፣ “ጦርነቱ ሀገርቱን የበለጠ ለእርስበርስ ግጭት ይዳርጋል የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናንም ያውካል” ፣ “አስቀድሞ ተሰናባች የመከላከያ ሰራዊት አባላትን በስም ማጥፋት የወነጀሉ የደቡብ ክልል አመራሮች በህግ ይጠየቁ” ፣ “በዚህ ጦርነት አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ የሌለበት በመሆኑ ወላይታን ከማንኛውም ጥቃት ለመጠበቅ እዚህ መሆናችን ተመራጭ ነው ” እና ሌሎች ሀሳቦች ከተሰናባች የመከላከያ ሰራዊት አባላት ለውይይት ቀርበው ሳሉ አወያዮቹ “የመንግስት መመሪያ ነው መከበር አለበት” በማለት ስብሰባውን በመቋጨት ለቅስቀሳ በሶዶ ከተማ በአስቸኳይ ጊዜ ስራ ስምሪት ላይ ያሉ ተሸከሪካሪዎችን መጠቀም መጀመራቸውን እንዲሁም በስብሰባው ላይ የተገኙትን በጎ ፈቃደኛ ብለው ምዝገባ መጀመራቸውን አረጋግጠውልናል፡፡
ከጉዳይ ጋር በተያያዘ ያነጋገርናቸው የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎችና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ቤተሰቦች እንደሚሉት “የብልፅግና ፓርቲ አባላትና አመራሮች እያደረጉ ያሉት ቅስቀሳ እጅግ እንዳሳዘናቸውና ዉጊያ ካማራቸው የብልፅግና ፓርቲ አባላትና አመራሮች ራሳቸው መዝመት እንዳለባቸው ገልፀው በቅስቀሳው ተታለው ወደ ጦርነት ቀጠናው የሚያመሩ ተሰናባች የመከላከያ ሠራዊት አባላት ካሉም የመመለስ ተስፋ እንደሌላቸውና ቤተሰቦቻቸው እንዲበተኑ ውሳኔ እንዳሳለፉ መታወቅ አለበት” ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ድህነትና መዋቅራዊ የመንግስት በደል ያጎሳቆለውን አከባቢ ለዚህ ዓይነት ርካሽ የፖለቲካ መጠቀሚያ የሚያደርጉ የብሔሩ ተወላጆች የሕሊና እና የሃይማኖች ታማኝነታቸው ወዴት ነው? ሲሉ እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች ጠይቀዋል፡፡
በኪንዶ ኮይሻ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ ተሰናባች የመከላከያ ሰራዊት አባል ስለተሰጣቸው የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ከትግራይ ውጊያ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተጠይቀው “እኛ ህጋዊ መስፈርት አሟልተን ለተደራጀን በክቡር ተሰናባች የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት የመኖሪያ ቤት መስሪያ የከተማ ቦታ ከበሌ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ተሰጠን ሆኖም ይህንን ወቅት ጠብቀው ርክክብ ማድረጋቸው ጥርጣሬን እንደፈጠረባቸው ገልፀው ችግሮችን በጦርነት ሳይሆን በዉይይት መፍታት” ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በጉተራ ስብሰባ ተሳታፊ ያልነበሩ ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ አንድ የብልፅግናው አመራር “ተሰናባች የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ለማሳመን በሰሜን ዕዝ እና ማይካድራ ላይ የወላይታ ብሔር ተወላጆች ሞተዋል” የሚለውን እንዲሁም “የወላይታ ክልል ጥያቄ እንዲመለስ ተሰናባች የመከላከያ ሠራዊት አባላት እንዲዘምቱ” የቅስቀሳ መመሪያ መተላለፉ ሌላኛው አሳዛኝ ድርጊት መሆኑን አጋልጠዋል፡፡