በወላይታ ዞን በነበረው ግጭት በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተሰማ
ነሐሴ 04 2012ዓ.ም (ቢቢሲ አማሪኛ)
በወላይታ ዞን ከተነሳው የክልልነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በነበረ እንቅስቃሴ የኮማንድ ፖስቱን መመሪያ ጥሰዋል የተባሉ ግለሰቦች ከተያዙ በኋላ በተከሰተ አለመረጋጋት በሰው ህይወትና አካል ላይ ጉዳት መድረሱ ተገለጸ።
በትናንትናው ዕለት የወላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ አክቲቪስቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች ዞኑን በክልል ለማደራጀት ከተቋቋመው ሴክሬታሪያት ጋር ስብሰባ ላይ ባሉበት ወቅት በጸጥታ ኃይሎች መያዛቸውን ተከትሎ ጉዳት መድረሱ ተሰምቷል።
በትናንትናው ዕለት በነበረው ግጭት ተጎድተው ወደ ሶዶ ክርስትያን ሆስፒታል ለሕክምና ከመጡ ሰዎች መካከል አንድ ሰው የሕክምና እርዳታ ቢደረግለትም መትረፍ እንዳልቻለ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የሆስፒታሉ ባልደረባ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
አምስት ሰዎች የተለያየ የጉዳት መጠን ደርሶባቸው በሆስፒታሉ ሕክምና ማግኘታቸውን እና በአሁኑ ሰዓትም ተኝተው እየታከሙ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል።
እኚሁ ግለሰብ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት እነዚህ ሰዎች ወደ ሆስፒታላችን የመጡ ይሁን እንጂ፣ በትናንትናው እለት ሊጋባ ትምህርት ቤት አካባቢ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን አውቃለሁ ሲሉ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ለግጭቱ ምክንያት በሆነው የጸጥታ ኃይሎች እርምጃ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች በአጠቃላይ 26 መሆናቸውን የገለጸው የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንና የደቡብ ክልል ሰላምና ጸጥታ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰዎች ከተለያዩ ቡድኖች ጋር በትብብር ይሰራሉ ሲል ከሷል።
በመግለጫው ላይ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰዎች የኮማንድ ፖስቱን ትዕዛዝ በመተላለፍ ሕገወጥ ስብሰባዎች እንዲሁም ሰልፎችን እንዳደረጉ ተገልጿል።
የወላይታ ዞን ምክር ቤት ሰኔ 15/2012 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እንዲቋቋም ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
የክልሉን መንግሥት ለማደራጀት የሚያስችል ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤትም እንዲቋቋም እና የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እንዲከናወኑም በዚሁ ወቅት ወስኖ ነበር።
በዞኑ የተቋቋመው የክልል ምስረታ ሴክሬታሪያት ካውንስል አማካሪ ቦርድ አባላት፣ በሕግ ኮሚቴው የተዘጋጀውን የሕገ መንግሥት ረቂቅ ላይ እንዲወያዩ ስብሰባ መጠራቱን የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ማቲዎስ ባልቻ እና የወላይታ ወጣት (የለጋ) የሆነው ዳንኤል ታደነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቦርዱ የተቋቋመው ከመንግሥት አካላት፣ በግል ሥራ ላይ ከተሰማሩ፣ ከወጣቶች፣ ከንግድ ማኅበራት፣ ከተቃዋሚዎች፣ ከአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ምሁራን እንደሆነ የሚናገሩት ግለሰቦቹ በትናንትናው ዕለትም በአዳራሽ ስብሰባው የተካሄደው ለእነዚሁ የቦርድ አባላት የሕገ መንግሥት ረቂቁን አቅርቦ ውይይት ለማድረግ እነደነበር ለቢቢሲ አስረድተዋል።
“ስብሰባው የተዘጋጀው በሕገመንግሥት ረቂቅ ላይ ለመወያየት ብቻ መሆኑን ነው የማውቀው” ሲሉ የሚያስረዱት አቶ ማቲዎስ በዕለቱ ሌላ አጀንዳ ስለመነሳቱ በስፍራው ስላልነበሩ አለመስማታቸውን ተናግረዋል።
የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ማቲያስ የድርጅታቸው አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጎበዜ አበራም በቁጥጥር ከዋሉት መካከል አንዱ መሆናውን በመግለጽ፣ ትናንት በነበረው አለመረጋጋት አንድ ሰው መሞቱንና የቆሰሉ መኖራውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
የወላይታ የለጋ አባል የሆኑት አቶ ዳንኤል ታደነ በበኩላቸው ትናንትና የግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር መዋል ተከትሎ በከተማዋ አለመረጋጋት ተከስቶ እንደነበር ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
አቶ ዳንኤል አክለውም በትናንትናው አለመረጋጋት የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን አረጋግጠው ዛሬ ግን ያለውን ሁኔታ “ውጥረት የሚታይበት” ሲሉ ተናግረዋል።
ትናንት ጉዳት የደረሰባው ሰዎች ምን ያህል እንደሆኑ በትክክል መረጃዎችን አለማጠናቀራቸውነ የሚገልፁት አቶ ማቲዎስ በበኩላው “ዛሬ እንቅስቃሴ እንደልብ ስለለሌለ” መረጃ ማደራጀት አለመቻላቸውን ተናግረዋል።
አቶ ዳንኤል አክለውም ማለዳ ላይ እርሳቸው ከሚኖሩበት ስፍራ ራቅ ብሎ በሚገኝ አካባቢ ጎማ የሚያቃጥሉ ወጣቶች እንደነበሩ አሁን ግን ሰላም መሆኑን ገልፀዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የወላይታ ሶዶ ነዋሪዎች ከከተማዋ መውጣትም ሆነ መግባት እንደማይቻል ተናግረዋል። አረካ አካባቢ ማለዳ ተቃዋሞ ለማድረግ ሙከራ ቢደረግም መበተኑንን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በሶዶ ከተማ አልፎ አልፎ ተኩስ እንደሚሰማ የተናገሩት ነዋሪዎች ዛሬም ከፀጥታ አካል በተተኮሰ ጥይት የሞቱ ሰዎች መኖራቸውን እንደሰሙ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
የሶዶ ከተማ ነዋሪዎችም ሆኑ የተቃዋሚ ፓርቲ አባሉ ሶዶ ከተማ ዛሬ በብዛት እንቅስቃሴ እንደማይታይባት ተናግረው፣ በብዛት የመከላከያ አባላት ሲንቀሳቀሱ እንደሚታይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ ዳንኤል ከዚህ ቀደም እርሳው በተገኙበት ጉባዔ ላይ ጠቅላይ ሚነስትር ዐብይ “ጥያቄው የካድሬ ጥያቄ ካልሆነ፤ ሕገመንግሥታዊ ጥያቄ ነው። ጥያቄያችሁ ሕግን ተከትሎ ምላሽ እንዲያገኝ ጥረት አደርጋለሁ” ማለታቸውን በማስታወስ አሁንም በእነዚህ ሰዎች ቁጥጥር ስር መዋል የተነሳ ጥያቄው ተዳፍኖ እንደማይቀር ያላቸውን እምነት ይናገራሉ።
አቶ ማቲዎስ በበኩላቸው ሕዝቡ መሪዎቹ በመታሰራቸው በተለያየ አካባቢ ተቃውሞውን ለማሰማት እየሞከረ ነው ሲሉ ያለውን ሁኔታ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
በዞኑ ስለተፈጠረውና ስለደረሰው ጉዳት ከደቡብ ፖሊስ ለማጣራት ብንደውልም የሕዝብ ግንኙነት ባልደረባዎች የተጠናከረ መረጃ እንዳልደረሳቸው በመግለጽ መልሰን እንድንደውል ነግረውናል።
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ አለማየሁ ባውዲ ለደቡብ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች የተለያዩ ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ አገር ለማፍረስ ከሚን ቀሳቀሱ አካላት ጋር ተቀናጅተው በመስራት ላይ ነበሩ ሲሉ በቁጥጥር ስር የዋሉትን ሰዎች ከሰዋል።