የክቡር ዶ/ር ዘብዲዮስ ጨማ አጭር የህይወት ታሪክ

በአዳነ አይዛ

ዶ/ር ዘብዴዮስ ጨማ ከአባታቸው ከአቶ ጨማ ጌራሞና ከእናታቸው ከወ/ሮ ሄጋኔ አሣሮ በቀድሞ የወላይታ አውራጃ በዳሞት ጋሌ ወረዳ ልዩ ስሙ ዋሪቴ ባላቃ በተባለው ቀበሌ በ1930ዓ.ም ተወለዱ፡፡ በልጅነታቸው ለወላጆቻቸው ታዛዥ፣ትሁትና ታማኝ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሲሆን እንደማንኛውም የገጠር ልጅ እንጨት ሰብረው፣ውኃ ቀድተው፣ከብት አግደው …እንዳደጉ ይታወቃል፡፡ ዕድሚያቸው ለትምህርት ሲደርስ በወላጅ እናታቸው አጋዥነት ፊደል ከቆጠሩ በኋላ ከነበሩበት አካባቢ ወደ ሶዶ ከተማ በመምጣት የአንደኛ እና የሁለኛ ደረጃ ትምህርታቸው በቀድሞ ሶዶ ክርስትያን አካዳሚ ት/ቤት እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በይርጋለም ከተማ ተከታትለዋል፡፡

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በ1952ዓ.ም በጊዜው በSIM ሚሽነሪያዎች ይተዳደር በነበረውና በሀገር ደረጃ በርካታ ምሁራንን ባፈራው በቀድሞ የሶዶ ክርስቲያን አካዳሚ በመምህርነት በመቀጠር ወደ ሥራው ዓለም ገብተዋል፡፡ ቀጥለውም በዚህ ተቋም በሥራቸው ምስጉን መምህር ሆነው በመገኘታቸው SIM በሰጧቸው የነጻ ትምህርት ዕድል ከ12ኛ ክፍል ያቋረጡትን ትምህርታቸውን በመቀጠል በ1964ዓ.ም ከቀድሞ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በኢንዳስትሪያል አርትስ ትምህርት በማዕረግ ተመርቀዋል፡፡
በኋላም ወደ ቀድሞ ት/ቤታቸው ወደ ሶዶ ክርስቲያን አካዳሚ በመመለስ በመምህርነትና በርዕሰ መምህርነት እስከ 1967ዓ.ም መጨረሻ ድረስ አገልግለዋል፡፡ ከዚያም ወደ አለታ ወንዶ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በመዛወር በርዕሰ መምህርነት ካገለገሉ በኋላ ወደ ወላይታ ተመልሰው በ1969ዓ.ም በጊዜዉ በአውራጃው ብቸኛውና ትልቁ የትምህርት ተቋም ወደ ሆነው የሶዶ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህር ቤት በመዛወር የት/ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህር ሆነው ተመደቡ፡፡

በዚሁ ትምህርት ቤት እስከ 1979ዓ.ም ድረስ በምክትል ርዕሰ መምህርነትና በርዕሰ መምህርነት አገልግለዋል፡፡ እነዚህ የሥራ ጊዜያት እኝህ ታላቅ ሰው ህዝባቸውን ለማገልገል በውስጣቸው የነበራቸውን ምኞት ያሳኩበትና ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ የወላይታን ባህል ታሪክና ቋንቋ ለማጥናትና ለመመራመር የነበራቸውን ጥልቅ ፍቅር ለመጀመር ዕድል ያገኙባቸው ጊዜያቶች ነበሩ፡፡

በመምህርነት ዓለም በቆዩባቸው ዘመናት በአውራጃው የነ አቶ ቦጋለ ዋለሉ እና የነ አቶ ዋና ዋጌሾን እንዲሁም የዘወትር አድናቂው የሆኑትን የአቶ የገርማሜ ንዋይን ፈለግ በመከተል በአውራጃው ውስጥ በተቋቋሙ ልዩ ልዩ የትምህርት ኮሚቴዎች በመሳተፍ በመደበኛና በኢ-መደበኛ የትምህርት እንቅስቃሴዎች፣ በወላይትኛ ቋንቋ አገልግሎትና በልሎችም ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት የወላይታ አውራጃ ትምህርት ማስፋፊያ ኮሚቴ(ወትማኮ) ፀሓፊ በመሆን ትምህርትን በወላይታ በሚገኙ ሁሉም ቀበሊያት ለማዳረስ ከተቋቋመው ከዚህ ኮሚቴ ጋር በመሆን በጊዜው በአውራጃው የነበሩ 28 ት/ቤቶችን በብዙ እጥፍ ለማሳደግ በተደረገው እንቅስቃሴ ተግባራቸውን በእውቀት በመምራት ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ከ1971 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተደረገው የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ የአውራጀው አስተባባሪ ኮሚቴ ፀሐፊ በመሆን ሰፊው የወላይታ ህዝብ ከመሀይምንት እንዲላቀቅ እስከ ዘመቻው ፍጻሜ ድረስ ከፍተኛ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡ በዚህም በርካታ ሳይማሩ ያስተማሩን ወገኖቻችን ከማሀይምነት እንዲላቀቁ የእስቸው ድርሻ ከፍተኛ ነበር፡፡

የትምህርት ሥራ በተማሪ ቁጠር እና በጥራት እየዘመነ ከመጣበት ከ1970ቹ መጀመሪያ ጀምሮ ትምህርትን በመረጃ መሳሪያ በማስደገፍ ለተማሪዎች ለማዳረስ በመንግስት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የግል የፈጠራ ችሎታቸውን በመጠቀም ከአካባቢው የሚገኙ ጥሬ ዕቃዎችን በመጠቀም በርካታ የማስተማሪያ መርጃ መሳሪያዎችን በማዘጋጀት በከተማና በገጠር ለሚገኙ ት/ቤቶች እንዲዳረስ ያደረጉ ሲሆን፡፡ በየት/ቤቱ የተቋቋሙትን የትምህርት ማበልጸጊያ ማዕከላት በስልጠናና በቁሳቁስ እንዲደራጁ የድርሻቸውን ተወጥቷዋል፡፡

አንድን ነገር መፍጠር መመራመርና ማበልጸግ ከልጅነታቸው ጀምረው የተቸሩት ፀጋ በመሆኑ ከሥራ በኋላ ሁል ጊዜ በትርፍ ሰዓታቸው የአናጽነት፣የኤለትሪክ እንዲሁም ሌሎችንም የፈጠራ ሥራዎችን መስራት ከምንም በላይ የሚያስደስታቸው ተግባር ነበር፡፡ በመምህረነትና በርዕሰ መምህርነት ባገለገሉባቸው ጊዜያት በየዓመቱ በአካባቢው የተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ በአውራጃው የሚገኙ ዘመናዊ የወረቀት ማባዣ ማሽኖች እጥረት ከፍተኛ በመሆኑ እኝህ ታላቅ የፈጠራና የምርምር ሰው ከአካባቢ የሚገኙ ጥሬ ዕቃዎችን በመጠቀም በሰዓቱ ልዩ የፈጠራ ውጤት የተባለለትን ማኗል የወረቀት ማባዣ ማሽን ለመጀመሪያ ጊዜ በመሥራት ወላይታ ውስጥ ለሚገኙ ለሁሉም ትምህርት ቤቶች በነጻ አዳርሰዋል፡፡ ይህም በወቅቱ የአውራጃውን የትምህት እንቅስቃሴ አንድ ደረጃ ከፍ ያደረገ ተግባር ነበር፡፡

ከዚህም ሌላ ዳሞታ አካባቢ የሚገኘውን ጥሬ ዕቃ በመጠቀም በመኖሪያ ቤታቸው ጠመኔ እና የጥቁር ሰሌዳ በማምረት በትምህርት ቤቶች መስፋፋት ምክንያት በወቅቱ ጉልህ ችግር የነበረውን የመጻፊያ ጠመኔ እጥረት በመመልከት የራሳቸውን ፈጠራ በመጠቀም በቀላሉ በማዘጋጀት ለት/ቤቶች እንዲደርስ አድርገዋል፡፡ ከፍ ብሎ በተጠቀሱ ዓመታት በትምህርት ሥራና በሌሎችም ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ለወላይታና ለአካባቢው ህዝብ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በአውራጃውም ሆነ በክ/ሀገር ደረጃ በርካታ መዳሊያዎችና የምስክር ወረቀቶች ተሰጥቷቸዋል፡፡
ዶ/ር ዘብዴዎስ የወላይታን ባህል፣ታሪክና ቅርሶቹን ትውልድ ተሸጋሪ ለማድረግ ገና ከጠዋቱ ጀምሮ አያሌ ተግባራትን ፈጽመዋል፡፡¸በጊዜው የሕዝቡ ባህል ታሪክና ቋንቋ በአካባቢው በነበረው ብሔራዊ ጭቆና ስር በነበረበትና ትውልዱ በማበራዊና ፖለቲካዊ ተጽእኖ ምክንያት የራስን ባህልና ታሪክ ለማሳደግና ለመንከባከብ እድል ባልነበረበት ወቅት እኝህ ሰው ብቻቸውን ስለ ወላይታ ታሪክና ባህል ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ይጮሁ የነበሩ ሲሆን ከእሳቸው የገደል ማሚቶ በስተቀር ማንም ጆሮ ሰጥቶ በማያዳምጥበት ወቅት ተስፋ ሳይቆሩጡ ተፅዕነውን ሁሉ በመቋቋም አያሌ ተግባራትን ለትውልድ አቆይተዋል፡፡

በዚህም መሠረት የወላይታን ወካይ ቅርሶችን በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ማስተዋወቅ የጀመሩት ከ1970ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ነበር፡፡ ዶ/ር ዘብዲዮስ ከወላይታ ባህላዊ ቅረሶች መካከል ከሁሉ በላይ በአሠራር ጥበባቸው እጅግ የሚደመሙበት የአምስቱን የወላይታ ባህላዊ ቤት አሠራር ጥበብ እንደሆነ አብዛኛውን ጊዜ በአንደበታቸው ይገልጹ ነበር፡፡ ይህ የወላይታ ሕዝብ ሀገር በቀል እውቀት የሆነው ባህላዊ የቤት አሠራር በሌላው ዓለም የማይገኝና ህዝቡ በተፈጥሮ የተቸረው ፀጋ በመሆኑ ለዚህ ጥበብ ልዩ አድናቆት ነበራቸው፡፡
ስለሆነም “ጉላንታ” ተብሎ የሚጠራውን የባህላዊ ቤት ዓይነት በ1971ዓ.ም በሃዋሳ ከተማ ሁለት ባህላዊ ቤቶችን ያሰሩ ሲሆን በ1972ዓ.ም ኢትዮጽያ በተስፋፊው የሶማሌ መንግሥት የተከፈተባትን ጦርነት በድል ካጠናቀቀች በኋላ በጦርነቱ ለተሰው ኢትዮጵያዊያን መታሰቢያና ለብሔር ብሔረሰቦች አንድነት መግለጫ በጅጅጋ ከተማ በእሳቸው አስተባባሪነት ይህ ባህላዊ ቤት እንዲሰራ ተደርጓል፡፡ ከዚህም ሌላ በተከታዩ ዓመት ተመሳሳይ ባህላዊ ቤት በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው ብሔራዊ ሙዚዬም ቅጥር ግቢ ውስጥ በአሳቸው አስተባባሪነት ተሠርቶ ከሙሉ የወላይታ የወግ ዕቃዎች ጋር አስረክበዋል፡፡
በተጨማሪም በአሁኑ ሰዓት በሙዚዬምነት አገልግሎት እየሰጠ ያለውን በወላይታ ዞን ባሕህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ግቢ የሚገኘውን ባህላዊ ቤት በ1995ዓ.ም እሳቸው እንዳሰሩ ይታወቃል፡፡ እንዲሁም በቅርቡ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ተሠርቶ ለአገልግሎት የበቃውን ባህላዊ ቤት በእሳቸው ሙሉ ዲዛይን ተደርጉ እንደተሠራ ይታወቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሶዶ ከተማ በሚገኘው የግላቸው በሆነው ቋሚ የቱሪስት ኤግዝቪሽን ማዕከል አምስቱንም የወላይታ ባህላዊ ቤት ዓይነቶችን ያሳነጹ ሲሆን በትውልድ መንደራቸው ሾያ ለሙዚዬምነትና ለቱሪስት መረጃ ማዕከልነት እየዋለ የሚገኘውን ባህላዊ ቤት በግል ወጪያቸው አስገንብተዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ዶ/ር ዘብዲዮስ የወላይታን ህዝብ በሙያቸው ከማገልገላቸው በተጨማሪ የአካባቢው ህዝብ እንደራሴ በነበሩበት ወቅት ከ1981 እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ በጊዜው በነበረው መንግሥት ኃላፊነት ተሰጥቷቸው የአሁኑ የኮንታ ልዩ ወረዳ የቀድሞ ኤላ አውራጃ ዋና አስተዳዳሪ በመሆን አጎራባች የሆነውን የኮንታን ህዝብ በቅንነት አገልግለዋል፡፡ በዚህም በርካታ የልማት ሥራዎችን ያሰሩ ሲሆን የአካባቢው ህዝቡ ለመጀመሪያ ጊዜ የዴዚል መብራት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ እንዲሁም ከጪዳ አስከ አማያ የሚያገናኘውን መንገድ በማሠራት በልማት ፈርቀዳጅነት በአካባቢው ህዝብ ይታወሳሉ፡፡

ዶ/ር ዘብዲዮስ ከመንግሥት ሥራ የጡረታ መውጫቸው በተቃረበባቸው የመጨረሻዎቹ ዓመታት በወላይታ ባህልና ታሪክ ላይ የሰበሰቧቸውን መረጃዎች ወደ ህዝብ ለማድረስ አማራጭ አድርጎ የወሰዱት መንገድ በዞኑ ባህል ቱሪዝም መምሪያ አመልክተው መቀጠርን ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ከ1993 እስከ1996 ዓ.ም በነበሩት ዓመታት በመሥሪያ ቤቱ በባህልና ቅርስ ባለሙያነት በመቀጠር ስለ ወላይታ ብሔር ባህላዊ የቤት አሠራር፣ስባህላዊ የጋብቻ ስርዓት፣ስለ ወላይታ ባህላዊ የሠርግ ሥርዓት፣ስለ ባህላዊ የግጭት አፈታት፣ስለወላይታ ባህላዊ የሀብት ማብሠሪያ ሥርዓት፣በአጠቃላይ የብሔሩ ባህላዊ እሴቶች እንዲሁም ወላይታ ውስጥ ስለሚገኙ ተፈጥሯዊና ባህላዊ ቅርሶች ..ወዘተ “ባካሊያ” በተሰኘው በመምሪያው በየስድስት ወሩ እየታተመ በሚወጣው መጽሔት ላይ አሳትመው ለህዝብ እንዲደርስ ያደረጉ ሲሆን በርካታ ያልታተሙ ጽሁፎቻቸው አሁን ላይ በዘርፉ ለሚደረጉ የምርምር ሥራዎች መነሻ መረጃ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

የባህልና የታሪክ ተመራማሪው ዶ/ር ዘብዲዮስ ጨማ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በወላይታ ታሪክ ባህልና ቋንቋ እንዲሁም በተፈጥሯዊና ባህላዊ መስህቦች በግል ጥረታቸው ጥናትና ምርምር በማድረግ የብሄሩን ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶችን እንዲሁም የወግ ዕቃዎች ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ መሰብሰብ የጀመሩት ከረዥም ዓመታት ጀምሮ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ በርካታ ቅርሶችን በመሰብሰብ በሀገር ደረጃ አሉ ከሚባሉ የግል ሙዜዬሞች ጋር ተወዳዳሪ የሆነ የግል ሙዚዬም በትውልድ መንደራቸው ሾያ በራሳቸው ወጪ አስገንብተው ለአገልግሎት አብቅተዋል፡፡
ዶ/ር ዘብዲዮስ ለመጀመሪያ ጊዜ ወላይታ ውስጥ ከ140 በላይ ቋሚ ቅርሶችና ተፈጥሯዊ መስህቦች የሚገኙበትን ቦታ በራሳቸው ወጪ ደርሰው በመጎብኘት የቦታ ካርታ በማዘጋጀት ቀጣይና ጥልቀት ያለው ጥናት እንዲደረግባቸው ለሚመለከተው አካል አስረክበዋል፡፡ እንዲሁም ከዉጪ ሀገር የአሪኪዮሎጂ ጥናት ባለሙያዎች ጋር በመገናኘትና ጥሪ በማድረግ የሞቸና ቦራጎ ዋሻ፣ትክል ድንጋዮች፣ የአኪሪሳ እና የሀሪሮና ዋሻ የጥንት ሰው የድንጋይ ላይ ጽሁፎችና ስዕሎች ምስጥር እንዲታወቅ በግላቸው ብዙ ጥረዋል፡፡
የሞቼና ቦራጎ ዋሻ አሁን በሚገኝበት የጥናት ደረጃ እንዲደርስ እሳቸው የመጀመሪያውን ተግባር እንደፈጸሙ ይታወቃል፡፡ ከዚህም ሌላ በርካታ ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን በማሰባሰብ በሙዚዬማቸው አደራጅተዋል፡፡ የወላይታ ባህላዊ አልባስ የሆነውን ድንጉዛ ሀዲያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዓመታት በፊት በውጪው ዓለም ያስተዋወቁ የመጀመሪያው ሰው ሲሆኑ ከሁሉም በላይ የወላይታን ብሔር ወካይ ቅርሶችን አሜርካን አገር ዋሽንግተን ዲስ በሚገኘው የጥቁሮች ሙዚዬም ያስቀመጡ የመጀመሪያ ኢትዮያዊ ነበሩ፡፡

ዶ/ር ዘብዲዮስ በብሔሩ ማህበራዊ ታሪክ ላይ ጊዜ ሰጥተው ሰፊ ጥናት ያደረጉ ሲሆን በተለይም በወላይታ ነባር እምነቶች ላይ ለዓመታት ጊዜ ሰጥተው ምርምር አድርገዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ይከተሉት ለነበረው የፕሮተስታንት ኃይማኖት ትልቅ ስፍራ የሚሰጡና በእግዚአብሔር ቃል መሠረት የኃይማኖቱን ህግጋቶች በማክበር እስከ ዕለተ ረፍታቸው ድረስ በኃይማኖታቸው የጸኑ ብርቱ የእምነት ሰው እንደነበሩ የእምነቱ አባቶች ይመሰክራሉ፡፡
በተለይም በ1919ዓ.ም በSIM ሚሺኔሪዎች አማካይነት ወደ አካባቢው የገባው የፕሮቴስታን ኃይማኖት በአካባቢው እንዲስፋፋ ከእምነቱ አባቶችና ከሚሺኔሪዎች ጋር በመሆን ገና ከማለዳው ጀምሮ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሲሆን ኃይማኖቱ በጊዜው በነበረው በመንግሥት ከፍተኛ ተጽዕኖ ውስጥ የነበረ በመሆኑ በወቅቱ ለእምነቱ ተከታዮች ከፍተኛ ጭንቀት የነበረው በከተሞች የመቃብር ቦታና የማምለኪያ ስፍራ የማግኘት ችግርን ለመፍታት የተጓዙበት ርቀት በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ሥፍራ እንዲሰጣቸው አድርጓል፡፡ ይሄውም በገጠር የማምለኪያ ቦታዎችን ከበጎ ፈቃደኛ የኃይማኖቱ ተከታዮች በስጦታና በግዥ በመውሰድ በርካታ ቤተክርስቲያናትን የተሠሩ ቢሆንም በጊዜው የከተማ መሬት በጥቂት ከበርቴዎች የተያዘ በመሆኑ ለፕሮቴስታንት ኃይማኖት መሬት የሚሸጥ ፈቃደኛ የመሬት ከበርቴ ባለመኖሩ ምክንያት ሶዶን ጨምሮ ባሉት የወላይታ ከተሞች የማምለኪያ ቦታም ሆነ የመቃብር ስፍራ ማግኘት እጅግ አዳጋች ነበር፡፡

ይህንን ችግር ለመቅረፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ ህይወታቸውንም ጭምር አሳልፎ ከሰጡ የሀይማኖቱ አባቶችና ሌሎች ወንድሞች ጋር በመሆን በ1967ዓ.ም በሶዶ ከተማ የቤተክርስትያን ማሰሪያ ቦታ እና የእምነቱ ተከታዮች የመቃብር ሥፍር በእሳቸው ፊታውራሪነት ከተወሰኑ የዚህ ኃይማኖት ተከታይ አባል ከነበሩት ወገኖች ጋር በህብረት በተደረገው እንቅስቃሴ ኃይማኖቱ ወደ አካባቢው ከገባበት ከ48 ዓመታት በኋላ እንዲፈቀድ በማድረግ በኃይማኖቱ መስፋፋት ታሪክ ጉልህ ድርሻ አበርክተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በሶዶ ከተማ የመጀመሪያው የፕሮቴስታንት ኃይማኖት ቤተክርስቲያ የሆነውን የቀድመው የሶዶ መሠረተ ትንሳኤ የአሁኑ የስታዲዬም ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር እርዳታ በ1968ዓ.ም ከሌሎች ወንድሞች ጋር በመሆን በእሳቸው ሙሉ መሀንዲስነት ታንጾ በሴኔ ወር 1969 ዓ.ም እንዲመረቅ ተደርጓል፡፡

ዶ/ር ዘብዲዮስ በሚከተሏቸው ኃይማኖት ዙሪያ ከፈጸሟቸው ተግባራት እነዚህ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በኃይማኖቱ መስፋፋት ታሪክ ላይ ጥልቅ ጥናት በማድረግ በ2009ዓ.ም ”የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ታሪክ በወላይታና አካባቢው” በሚል ርዕስ ከወላይታ ህዝብ ታሪክ ጋር አዋዝተው የጻፉትን መጽሐፍ በዚህ ታሪካዊ ቤተክርስቲያን ውስጥ በማስመረቅ ለህዝብ እንዲደርስ አድርገዋል፡፡ ዶ/ር ዘብዲዮስ በአሁኑ ሰዓት የብዙዎች ችግር የሆነውን በባህልና በኃይማኖት መካከል ያለውን ጥምረትና ተደጋጋፊነት በጥልቀት በመረዳት አስታሪቀው የተመራመሩ ብልህ የታሪክ ተመራማሪ ነበሩ ፡፡

ከላይ እንደተገለፀው ዶ/ር ዘብዲዮስ የዘወትር ህልማቸው ከወጣትነት ዕድሚያቸው ጀምሮ የሰበሰቡትን የታሪክ መረጃዎችን በተሻለ ሁኔታ አሳትሞ ትውልድ ያልተበረዘና ያልተከለሰ የህዝብ ታሪክን ከውዥንብር በነጻ ሁኔታ እንዲረዳ ማድረግ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት የሰበሰቡትን መረጃ ከሦስት ዓመት ወዲህ በመተንተንና በማደረጀት ወደ ጽሁፍ በመቀየር አስፈላጊውን የአርትኦት ሥራ አጠናቅቀው ለማሳተም እየተጣጣሩ በነበረበት ወቅት ባደረባቸው የካንሰር ህመም ጉልበት ከድቷቸው አልጋላይ ወደቁ፡፡

ዶ/ር ዘብዲዮስ አልጋ ላይ በነበሩባቸው አጭር ሳምንታት ውስጥ ከበሽታቸው በላይ ያስጨንቃቸውና ያማቸው የነበረው ይህን መጽሐፍ አሳትመው ለህዝብ ሳያደርሱ ነፍሳቸው ከሥጋቸው እንዳትለይ ይጨነቁ ነበር፡፡ በዚህም ሆስፒታል በነበሩበት ወቅት ሊጠይቋቸው የመጡትን የቅርብ ወዳጆቻቸውንና ልጆቻቸውን ሁሉ መጽሐፉ ታትሞ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የወላይታ ልጆች እንዲደርስላቸው ሁሉም ጥረት እንዲያደርጉ ይማፀኘኗቸው ነበር፡፡ በመሆኑም የመጨረሻ እስትንፋሳቸው ሳትቋረጥ በመልካም ልጆቻቸው አማካይነት ይህን ለሃምሳ ዓመታት የጸነሱትን ጽንስ ተገላግለው የልፋታቸው ውጤት የሆነውን መጽሀፋቸውን በዓይናቸው ካዩ በኋላ ሰኔ 4 ቀን 2012ዓ.ም በተወለዱ በ82 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም እስከ ወዲያኛ አሸልበዋል፡፡

ዶ/ር ዘብዲዮስ ለረዥም ዓመታት ለወላይታ ብሔር ባህል ቋንቋና ታሪክን ያለማንም ድጋፍ በግላቸው ለመጠበቅ፣ለማልማት፣ለማሳደግ እንዲሁም የብሔሩ ባህል በዓለም ደረጃ እንዲታወቅ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ልክ የዛሬ ዓመት ሀምሌ 6 ቀን በ2011ዓ.ም የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት በወሰነው መሠረት ዩኒቨርሲቲው ለእኝህ ታላቅ ሰው በታሪኩ የመጀመሪያውን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷቸዋል፡፡

ዶ/ር ዘብዴዮስ ጨማ ገና ከጠዋቱ ጀምሮ ለወላይታ ህዝብ እድገትና ብልጽግና እንዲሁም ለህዝብ ከፍታ፣ሌተቀን በገንዘባቸውና በእውቀታቸው የታገሉ የወላይታ ህዝብ ህያው ተምሳሌት ናቸው፡፡ እኝህ ታላቅ ሰው በዚህ ረዥም ዕድሜ ለህዝቡ የከፈሉትን መስዋዕትነት ትውልድ ሁሉ በበጎ ጎኑ እያስታወሰ ይኖራል፡፡ መልካም ሥራ ሠርተው አልፈዋልና ስማቸው ሁል ጊዜ ከመቃብር በላይ ነው፡፡

የወላይታ ዞን አስተዳደርና የወላይታ ህዝብ እኝህ ታላቅ ሰው ለህዝባቸውና ለአካባቢያቸው በቁርጠኝነት ለበረከቱት አስተዋጽኦ ትውልድ ውለታቸውን እንዳይረሳ ለማድረግ በመንግስት ደረጃ ቋሚ መታሰቢያ እንዲያኖር በባህልና ታሪክ ወዳድ የወላይታ ልጆችና በቤተሰባቸው ስም እንጠይቃለን፡፡

ውድ የዶ/ር ዘብዲዮስ ቤተሰቦች መወለድ ማደግና መሞት የተፈጥሮ ህግ ነው፡፡ ይህን ማንም ልሽረው አይችልም፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ በዚህች ምድር በሚቆይባቸው አጭር ጊዜያት ለህዝብና ለሀገር መልካም ሥራ ሠርቶ ማለፍ ከሁሉ የሚበልጥ ትልቅ ጸጋ ነው፡፡ ስለዚህ ዶ/ር ዘብዲዮስ ይህንን አድርገውታል፡፡ በዚህም ልትኮሩ እንጂ ልታዝኑ አይገባም፡፡ እሳቸው በህይወት በነበሩበት ጊዜ የመጀመሪያና የመጨረሻ ምኞታቸው ወላይታን ወደቀድሞ ልዕልና በመመለስ የወላይታን ህዳሴ ማረጋገጥ ነበር፡፡ ለዚህም እንደ አይነተኛ መፍትሄ አድረገው የወሰዱት ህዝቡ የራሱን እውነተኛ ታሪክ እንዲያውቅ ማድረግ ነበር፡፡

ለዚህም ከወላይታና አጎራባች አካባቢዎች ጀምሮ ሰሜን ሸዋ ቡልጋ ኢቴሳ ድረስ በሚመዘዘው የወላይታ ህዝብ ታሪክ ዙሪያ ከዛሬ 50 ዓመታት በፊት ጀምሮ በድምጽና በፎቶ ግራፍ የሰበሰቧቸው የታሪክ መረጃዎችን ቢቻል የራሳችሁን የግል አርካይብ ማዕከል በማደራጀት፣አለበለዚያም በዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ በሚገኘው አርካይብ ማዕከል በስማቸው በማስቀመጥ መረጃዎቻቸው ለበርካታ ወጣት ተመራማሪዎች አገልግሎት እንደውሉ በማድረግ የእሳቸውን ህልም እንደምታሳኩ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ዶ/ር ዘብዴዎስ ከባለቤታቸው ከወ/ሮ ያሎሜ ትልጌ 4 ወንዶችና 3 ሴቶች በጠቅላላ 7 ልጆችን ያፈሩ ሲሆኑ የ17 የልጅ ልጆች አያትና የ4 ልጆች ቅድመአያት ነበሩ፡፡

እግዚአብሔር አምላክ የእኝህን ታላቅ የህዝብ ልጅ ነፍስ በገነት ያኑርልን፡፡ ለቤተሰቦቻቸው፣ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲሁም ለመላው የወላይታ ህዝብ ታሪክና ባህል ተቆርቃሪዎች መጽናናት እንመኛለን፡፡ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር መፅናናቱን ይስጣችሁ ያበርታችሁ፡፡

Wolaita Today

በክቡር ዶ/ር ዘብዲዮስ ጨማ የተፃፈ በamazon ሽያጭ ላይ ያለ መፅሐፍ ይግዙና አጋርነትዎን ይግለፁ

Wolaita Today