“ሳሶ ሞቶሎሚ”
በተመስገን ወ/ፃዲቅ
ሞቶሎሚ የሚባል ሀያሉ ንጉስ በዎላይታ ከ1195 እስከ 1272 ለ77 አመታት ነግሷል:: ንጉሱ በዎላይታ ሶስት የቤተ-መንግስት ማዕከላት ነበሩት:: እነዚህም
1ኛ በኪንዶ ዜጌቴ አካባቢ
2ኛ በቦሎሶ ዛባ ተራራ ላይ የነበረው አፋማ ቤተመንግስት
3ኛ በዳሞታ ተራራ ላይ አናት ያለው ጣዛ
ቤተመንግስት(ጋሩዋ) በመባል ይታወቃሉ፤ንጉስ ሳሶ ሞቶሎሚ የዎላይታ ንጉስ በነበሩበት ዘመን የዎላይታ ቆዳ ስፋት በተለያዩ አቅጣጫዎች እንዳሰፉ ይነገራል:: በዳሞታ ተራራ ካላቸው ቤተመንግስት ተነስቶ በመዝመት በርካታ አካባቢዎችን በቁጥጥር ስራቸው እንዳዋሉ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገድል የሚናገረውን ጨምሮ የተለያዩ የታሪክ መጽሐፍት ጠቅሰዋል:: በርግጥ የንጉስ ሞቶሎሚ ታሪክ የሕዝቦች መልካም ታሪካቸው በሚገባ እንዳይፃፍና እንዳይነገር ግልፅም እንዳይወጣ ታፍኖ ተይዟል::
የሳሶ ልጅ ሞቶሎሚ ንጉስ ተብሎ ዘውድ የደፋው አሁን ከዳልቦ ሐሙስ ገበያ ወደ ደቡብ አቅጣጫ ከገበያው አምስት ኪ.ሜ ርቀት ላይ ባለው በዛላ ሻሻ ቀበሌ ነገሪታ ጎሊያ በሚባል ቦታ ባለው መናገሻ ነበር::
በዎላይታ የነገስታት ታሪክ ሞቶሎሚ የገነባው ሰራዊት በሀያልነቱ ይታወቃል::በዳሞታ ተራራ ዙሪያ ባሉት ገደላ ገደሎችና ዋሻዎች ተጠልሎ ከዛ እየወጣ ይሰለጥን ነበር:: በታሪክ እንደሚነገረው የሞቶሎሚ ሰራዊት ገደል መዝለል፣ሸርተቴ፣የውሃ ሙላት ማለፍ፣የጦርነት ታክቲክ የፈረስ ግልቢያ፣አክሮባት፣እርግጫና ጡጫ፣ ተራራው ላይ እንዲሁም በሜዳ ልምምድ ያደርግ ነበር::
ንጉስ ሞቶሎሚ በዚህ በሰለጠነ ሰራዊታቸው በሸዋ ሰሜናዊ አቅጣጫ እስከ ጎጃም ደጋ ድረስ፣በሸዋ አገር ከጅሩ ወደ ግራ ታጥፈው ሞቶሎሚ ሰፈር የሚባለውን ጨምሮ ቡልጋ ፀላልሽ ወረዳ በዘመቻ እንደደረሱ ይነገራል::የንጉስ ሞቶሎሚ መካነ መቃብር በቡልጋ እንደሚገኝ ልብ ይሏል::